በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 31

ኢያሱና ገባኦናውያን

ኢያሱና ገባኦናውያን

በከነአን ምድር የሚገኙ ሌሎች ሕዝቦች በኢያሪኮ ላይ የደረሰውን ጥፋት ሰሙ። በመሆኑም የእነዚህ ሕዝቦች ነገሥታት ተባብረው ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት ወሰኑ። ገባኦናውያን ግን ሌላ ነገር ለማድረግ አሰቡ። ያረጀ ልብስ ለብሰው ወደ ኢያሱ ሄዱና እንዲህ አሉት፦ ‘የመጣነው ከሩቅ አገር ነው። ስለ ይሖዋም ሆነ በግብፅና በሞዓብ ምድር ለእናንተ ስላደረገው ነገር ሰምተናል። እባካችሁ ጥቃት እንደማትሰነዝሩብን ቃል ግቡልን፤ እኛም አገልጋዮቻችሁ እንሆናለን።’

ኢያሱ የተናገሩትን ነገር ስላመነ በእነሱ ላይ ጥቃት ላለመሰንዘር ተስማማ። ከሦስት ቀን በኋላ ግን ገባኦናውያን የሩቅ አገር ሰዎች ሳይሆኑ በዚያው በከነአን ምድር የሚኖሩ ሰዎች እንደሆኑ አወቀ። ኢያሱ ገባኦናውያንን ‘ለምንድን ነው ያታለላችሁን?’ በማለት ጠየቃቸው። እነሱም እንዲህ ብለው መለሱ፦ ‘ስለፈራን ነው! አምላካችሁ ይሖዋ ለእናንተ እንደሚዋጋላችሁ እናውቃለን። እባካችሁ አትግደሉን።’ ኢያሱም ቃሉን በመጠበቅ ሳይገድላቸው ቀረ።

ብዙም ሳይቆይ፣ በከነአን ምድር የሚኖሩ አምስት ነገሥታት ወታደሮቻቸውን አሰልፈው ከገባኦናውያን ጋር ለመዋጋት ተነሱ። ኢያሱና ሠራዊቱ ሌሊቱን ሙሉ ተጉዘው ገባኦናውያንን ለማዳን መጡ። በቀጣዩ ቀን ጠዋት ጦርነቱ ተጀመረ። ከነአናውያን በሁሉም አቅጣጫ መሸሽ ጀመሩ። በሸሹበት ቦታ ሁሉ ይሖዋ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸው። ከዚያም ኢያሱ ‘በገባኦን ላይ ፀሐይ ትቁም’ ብሎ ይሖዋን ለመነ። ፀሐይ ከዚያ በፊት ቆማ አታውቅም፤ ታዲያ ኢያሱ ፀሐይ እንድትቆም ይሖዋን የጠየቀው ለምንድን ነው? በይሖዋ ስለታመነ ነው። ፀሐይዋ እስራኤላውያን እነዚያን የከነአን ነገሥታትና ሠራዊታቸውን በሙሉ ድል አድርገው እስኪጨርሱ ድረስ አንድ ሙሉ ቀን ሳትጠልቅ ቆየች።

“ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ግን ከክፉው ነው።”—ማቴዎስ 5:37