የፊሊፒንስ ፎቶ ጋለሪ 1 (ከየካቲት 2014 እስከ ግንቦት 2015)
የይሖዋ ምሥክሮች በኬሶን ሲቲ በሚገኘው የፊሊፒንስ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ያሉትን ሕንፃዎች እያደሱ ከመሆኑም ሌላ አዳዲስ ሕንፃዎችን እየገነቡ ነው። ለፊሊፒንስ የሚዘጋጁት ጽሑፎች በአሁኑ ጊዜ የሚታተሙት በጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በመሆኑ ቀደም ሲል የሕትመት ሥራ ይሠራበት በነበረው ሕንፃ የሚጠቀሙት የትርጉም፣ የአካባቢ ንድፍ/ግንባታ፣ የኮምፒውተርና የጥገና ክፍሎች ናቸው። ይህ የፎቶ ጋለሪ ከየካቲት 2014 እስከ ግንቦት 2015 ባለው ጊዜ በቀድሞው የማተሚያ ሕንፃና በሌሎች ሕንፃዎች ላይ የተሠሩትን አንዳንድ ሥራዎች ያሳያል። ሥራው እስከ ጥቅምት 2016 ድረስ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የካቲት 28, 2014—ሕንፃ 7
ጊዜያዊ ሠራተኞች አዳዲስ ፋይበርግላሶችን (ከሕንፃው ሙቀት እንዳይወጣ የሚከላከሉ የሕንፃ መሣሪያዎች) ከእርጥበት ለመከላከል በላስቲክ እያሸጉ ነው። ሠራተኞቹ ቆዳቸው ጉዳት እንዳይደርስበት ሰውነታቸውን የሚሸፍን መከላከያ ይለብሳሉ።

ሚያዝያ 2, 2014—ሕንፃ 7
ሠራተኞች የፊሊፒኖ የምልክት ቋንቋ ቀረጻ የሚደረግበትን ስቱዲዮ ኮርኒስ ሥራ እያጠናቀቁ ነው። በጣሪያው ላይ የሚገኙት የአራት ማዕዘን ቅርጽ ያላቸው ቀዳዳዎች በስቱዲዮው ውስጥ የተጣራ አየር በእኩል መጠን እንዲዳረስ የሚያስችሉ መሣሪያዎች (HVAC diffusers) ይገጠሙባቸዋል።

ጥቅምት 21, 2014—በኬሶን ሲቲ የሚከናወነው ግንባታ
ማዕከላዊ የውኃ መስመር ለመዘርጋት ቁፋሮ እየተደረገ ነው። አዲሱ የውኃ መስመር በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ ለሚገኙ ሕንፃዎች በሙሉ አገልግሎት ይሰጣል።

ታኅሣሥ 19, 2014—ሕንፃዎችን (1፣ 5 እና 7) የሚያገናኝ ድልድይ
ይህ መከለያ ያለው አዲስ ድልድይ የመመገቢያ አዳራሹ የሚገኝበትን ሕንፃ 1ን ጨምሮ ሁሉንም ዋና ዋና ሕንፃዎች ያገናኛል። ድልድዩ በተለይ ከ300 በላይ ለሆኑት በሕንፃ 7 ላይ የሚሠሩ ሰዎች ጠቃሚ ነው።

ጥር 15, 2015—ሕንፃ 5
ሃምሳ ቶን የሚመዝን ክሬን (የከባድ ዕቃ ማንሻ) የጣሪያ ክዳን ለመሥራት የሚያገለግል ዕቃ እያነሳ ነው። የአካባቢው የሕንፃ ተቋራጮች የተለያየ ክብደት ያላቸውን ክሬኖች ያንቀሳቅሳሉ።

ጥር 15, 2015—ሕንፃ 5ሀ (ሕንፃዎቹን የሚያገናኝ ቤት)
መቶ ሃያ አምስት ሜትር ካሬ ስፋት ያለው ይህ ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ ደረጃ፣ ሊፍትና ሁለት መጸዳጃ ቤቶች አሉት። መጸዳጃ ቤቱና ደረጃው እዚህ ሕንፃ ላይ መሆናቸው ከአጠገቡ በሚገኘው ሕንፃ 5 ላይ ተጨማሪ ቦታ እንዲገኝ አስችሏል። ሊፍቱ ሕንፃ 5 ውስጥ ሳይሆን በዚህ ሕንፃ ውስጥ መደረጉ በቪዲዮ ወይም በድምፅ ቅጂ ወቅት የሊፍቱ ድምፅ እንዳይረብሽ ያስችላል።

ጥር 15, 2015—ሕንፃ 5ሀ (ሕንፃዎቹን የሚያገናኝ ቤት)
ሠራተኞች ጥላ ሥር ሆነው ፌሮ እያሰሩ ነው። የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት በጥር ወር በአማካይ 29 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ገደማ ሲሆን በሚያዝያ ወር ደግሞ 34 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ገደማ ይደርሳል።

መጋቢት 5, 2015—ሕንፃ 5
ሠራተኞች የጣሪያውን ውቅር ለማጠናከር ጣውላ ይጠቀማሉ። ሕንፃ 5ን ለመገንባት 800 ገደማ የሚሆኑ ጠንካራ እንጨቶች ጥቅም ላይ ውለዋል።

መጋቢት 17, 2015—ሕንፃ 5
ሠራተኞች አነስ ላለ ፕሮጀክት የሚያስፈልጋቸውን ሲሚንቶ እያቦኩ ነው። ከ100 በላይ ሠራተኞች ለግንባታ ሥራው ድጋፍ እያደረጉ ነው፤ እነዚህ ሠራተኞች የመጡት ከስፔን፣ ከኒውዚላንድ፣ ከአውስትራሊያ፣ ከካናዳ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከጃፓንና ከሌሎች አገሮች ነው።