በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

አንድ ሺህ የመንግሥት አዳራሾች—ቁጥሩ ገና ይጨምራል!

አንድ ሺህ የመንግሥት አዳራሾች—ቁጥሩ ገና ይጨምራል!

የይሖዋ ምሥክሮች ፊሊፒንስ ውስጥ ከመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ጋር በተያያዘ ታሪክ ሠርተዋል፤ ልዩ በሆነ የግንባታ ዝግጅት አማካኝነት የሠሯቸው አዳራሾች ቁጥር ነሐሴ 2013 አንድ ሺህ ደርሷል። በብዙ አገሮች ውስጥ እንደሚገኙ ጉባኤዎች ሁሉ ፊሊፒንስ ውስጥ ያሉ ጉባኤዎችም ለበርካታ ዓመታት የራሳቸውን የመንግሥት አዳራሽ ለመገንባት የሚያስችል አቅምም ሆነ ችሎታ አልነበራቸውም። ለዓመታት ስብሰባ ይደረግ የነበረው በግለሰቦች ቤት ወይም ደግሞ በቀርከሃ በተሠሩ ትናንሽ ቤቶች ውስጥ ነበር።

በፊሊፒንስም ሆነ በሌሎች አገሮች ባለው ቀጣይ የሆነ የይሖዋ ምሥክሮች እድገት የተነሳ ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል የገንዘብ አቅማቸው ውስን በሆኑ አገሮች ውስጥ የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባት የሚያስችል ዝግጅት በ1999 ዘርግቷል። ዝግጅቱ እንደሚከተለው ነው፦ በአካባቢው ያሉ ወንድሞች የቻሉትን ያህል መዋጮ ያደርጋሉ፤ በሌሎች አገሮች ያሉ ወንድሞች የሚያደርጉት መዋጮም በዚህ ላይ ይጨመራል። በግንባታ ሥራ ሥልጠና ያገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በቡድን ተደራጅተው ጉባኤዎች የራሳቸውን መንግሥት አዳራሽ እንዲገነቡ ይረዷቸዋል። ይህ ዓለም አቀፍ ዝግጅት ኅዳር 2001 በፊሊፒንስ ሥራ ላይ ውሏል።

አንድ ሺህኛው የመንግሥት አዳራሽ የተሠራው በቡላካን ማሪላው ነው፤ ኢሉሚናዶ የሚሰበሰበው እዚህ በተገነባው አዳራሽ ውስጥ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “እውነተኛ ክርስቲያናዊ ወንድማማችነትን መመልከት ችያለሁ። ወንድ ሴት፣ ልጅ አዋቂ ሳይል በርካታ የበጎ ፈቃድ ሠራተኞች ነበሩ። የፀሐዩን ንዳድ ችለን በኅብረት ሠርተናል። ሙሉ ቀን መሥራት አድካሚ ቢሆንም አብረን ያከናወንነው ሥራ በጣም አስደስቶናል።”

እነዚህ የበጎ ፈቃድ ሠራተኞች ያከናወኑት ሥራ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችንም ትኩረት ስቧል። ለሥራው የሚያስፈልገውን አሸዋና ጠጠር በመኪናው ሲያመላልስ የነበረ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “እንደ ጉንዳን ናችሁ፤ ቁጥራችሁ በጣም ብዙ ነው! ሁሉም ሰው ይሠራል። እንዲህ ዓይነት ነገር አይቼ አላውቅም።”

የተገነባው አዲስ የመንግሥት አዳራሽ

ሠራተኞቹ የሕንፃውን መዋቅር ማቆም ከጀመሩ ከስድስት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አዳራሹን ገንብተው ጨርሰዋል። የጉባኤው አባላት የመንግሥት አዳራሹን በፍጥነት ገንብተው በመጨረሳቸው የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ አስፈላጊ ሥራ ላይ ሙሉ በሙሉ ትኩረት ማድረግ ችለዋል።—ማቴዎስ 24:14

ኤለን የተባለች ሌላ የጉባኤው አባል ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “የድሮው መንግሥት አዳራሽ አነስተኛ በመሆኑ አብዛኞቻችን ደጅ ለመቀመጥ እንገደድ ነበር። አዲሱ የመንግሥት አዳራሽ ግን በጣም ቆንጆና ይበልጥ ምቹ ነው፤ በመሆኑም ሁላችንም በስብሰባዎች ላይ ከሚሰጠን መመሪያና ማበረታቻ የተሻለ ጥቅም ማግኘት እንችላለን።”