በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ፈጽሞ የማይረሳ ጉዞ

ፈጽሞ የማይረሳ ጉዞ

በየዓመቱ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በኒው ዮርክ ስቴት ውስጥ የሚገኙትን የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮና የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃዎች ይጎበኛሉ። እነዚህ ስፍራዎች ቤቴል በመባል ይጠራሉ፤ ቤቴል፣ “የአምላክ ቤት” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ስም ነው። የተለያዩ ጎብኚዎች ጽሑፎች ሲታተሙ ለማየት፣ ሥራችን የተደራጀው እንዴት እንደሆነ ለመመልከትና በዚያ የሚያገለግሉ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ይመጣሉ። በተለይም ደግሞ በቅርቡ ቤቴልን የጎበኘ አንድ ሰው እንዲህ ለማድረግ ሲል ብዙ መሥዋዕትነት ከፍሏል።

ማርሴለስ የይሖዋ ምሥክር ሲሆን የሚኖረው በአንከሬጅ፣ አላስካ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ነበር፤ a ማርሴለስ ከጥቂት ዓመታት በፊት በአንጎሉ ውስጥ ደም በመርጋቱ ምክንያት መናገር የሚችለው ጥቂት ቃላትን ብቻ ነው። የሚንቀሳቀሰው በተሽከርካሪ ወንበር ከመሆኑም ሌላ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቹን ለማከናወን የሰው እገዛ ያስፈልገዋል። እነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩበትም ማርሴለስ ቤቴልን የመጎብኘት ከፍተኛ ጉጉት ነበረው። በቅርቡ ይህን ምኞቱን እውን ማድረግ ችሏል።

ማርሴለስ ይህን የጉዞ ዕቅዱን ማሳካት እንዲችል እርዳታ ሲያደርግለት የቆየው ወዳጁ ኮሪ እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ሁኔታው ደጋግሞ ይጠይቀኝ ነበር። ጉዳዩ ከምን እንደደረሰ ለማወቅ ሳይሰለች በየጊዜው ይደውልልኝ ነበር። ማርሴለስ መናገር የሚችለው ጥቂት ቃላትን፣ እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ ‘አዎ’ ወይም ‘አይ’ የሚሉትን ብቻ ነበር፤ ስለሆነም ስልክ በሚደውልበት ጊዜ የፈለገውን ነገር ለመረዳት በርካታ ጥያቄዎችን መጠየቅ ነበረብኝ።” የስልክ ውይይታቸው ይህን ይመስል ነበር፦

“ቤት እንድመጣልህ ትፈልጋለህ?”

“አይ።”

“ሐኪም እንድጠራልህ ትፈልጋለህ?”

“አይ።”

“የደወልከው ወደ ቤቴል ስለምታደርገው ጉዞ ለማወቅ ነው?”

“አዎ።”

“ከዚያም ጉዞውን በተመለከተ ያወጣነው ዕቅድ ምን ላይ እንደደረሰ እነግረዋለሁ። ግቡ ተሳክቶለት ማየት እጅግ እናፍቅ ነበር።”

ማርሴለስ የጉዞ ዕቅዱን ለማሳካት በርካታ መሰናክሎችን ማለፍ ይጠበቅበት ነበር። ገቢው አነስተኛ በመሆኑ 5,400 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ርቀት ተጉዞ ኒው ዮርክ ለመድረስ የሚያስችለውን የትራንስፖርት ወጪ ለመክፈል ለሁለት ዓመት ገንዘብ ማጠራቀም ነበረበት። እንዲሁም ካለበት የጤና እክል የተነሳ እሱን የመርዳት ብቃት ያለው ሰው የግድ አብሮት መጓዝ ያስፈልገው ነበር። በመጨረሻም ጉዞውን ለማድረግ የሐኪሙን ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅበት የነበረ ሲሆን ፈቃዱን ያገኘው ጉዞውን የሚያደርግበት ጊዜ ሊደርስ ጥቂት ቀናት ብቻ ሲቀረው ነበር።

ማርሴለስ ኒው ዮርክ ሲደርስ በብሩክሊን፣ በፓተርሰንና በዎልኪል ያሉትን ሕንፃዎች ጎብኝቷል። እጅግ ግዙፍ የሆኑት ማተሚያ ማሽኖች መጻሕፍትና መጽሐፍ ቅዱሶች ሲያትሙ ከመመልከቱም ሌላ ሥራችን ምን ያህል የተደራጀ እንደሆነ ይበልጥ መገንዘብ ችሏል። በተጨማሪም “መጽሐፍ ቅዱስና መለኮታዊው ስም” እንዲሁም “ለይሖዋ ስም የቆሙ ሕዝቦች” የሚሉትን ኤግዚቢሽኖች ተመልክቷል። እግረ መንገዱንም በርካታ አዳዲስ ወዳጆችን ማፍራት ችሏል። በእርግጥም ይህ ፈጽሞ የማይረሳ ጉዞ ነበር!

ብዙዎች ቤቴልን ከጎበኙ በኋላ ምን እንደተሰማቸው ሲጠየቁ ለመግለጽ ቃላት እንደሚያጥራቸው ይናገራሉ። ማርሴለስ ግን ቤቴልን ለመጎብኘት ያን ሁሉ መሥዋዕት መክፈሉ ትክክለኛ ውሳኔ ስለመሆኑ ጥያቄ ሲቀርብለት “አዎ፣ አዎ፣ አዎ!” በማለት መልስ ሰጥቷል፤ ማርሴለስ ስሜቱን መግለጽ የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው።

አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ቤቴልን መጥታችሁ ብትጎበኙ ልክ እንደ ማርሴለስ አስደሳች ጊዜ ማሳለፋችሁ አይቀርም። በዓለም ዙሪያ ያሉት ቅርንጫፍ ቢሮዎቻችን ለጎብኚዎች ክፍት ናቸው። ታዲያ አንተስ ለምን መጥተህ አትጎበኘንም?

a ማርሴለስ ይህ ጽሑፍ ለመታተም በዝግጅት ላይ እያለ ግንቦት 19, 2014 ሕይወቱ አልፏል።