በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በብሪታንያና በአየርላንድ በሚነገሩ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ምሥራቹን መስበክ

በብሪታንያና በአየርላንድ በሚነገሩ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ምሥራቹን መስበክ

የይሖዋ ምሥክሮች በብሪታንያ እና በአየርላንድ በሚነገሩ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ለሚጠቀሙ ሰዎች ለመስበክ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው። a በእነዚህ አገሮች ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ አይሪሽ፣ ስኮቲሽ ጌሊክ እና ዌልሽ ይነገራሉ።

በአዲስ መልክ በብዙ ቋንቋዎች የተዘጋጀው jw.org የተባለው ድረ ገጻችን በመስከረም 2012 ተለቅቋል፤ በዚሁ ድረ ገጽ ላይ አይሪሽ እና ዌልሽ ቋንቋዎች የተካተቱ ሲሆን ከነሐሴ 2014 ጀምሮ ደግሞ ስኮቲሽ ጌሊክ ቋንቋ እንዲካተት ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪ በእነዚህ ቋንቋዎች የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች እናትማለን። ታዲያ ለዚህ ጥረት ሰዎች ምን ምላሽ እየሰጡ ነው?

የአንድ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ በስኮቲሽ ጌሊክ የተዘጋጀ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትራክት በደረሰው ጊዜ ወዲያውኑ ድምፁን ከፍ አድርጎ ካነበበው በኋላ ማልቀስ ጀመረ። ስሜቱ እንዲህ በጥልቅ የተነካው ለምንድን ነው? በትርጉሙ ጥራት በጣም ከመገረሙ የተነሳ በአድናቆት ስሜት ተውጦ “ተርጓሚዎቹ እነማን ናቸው? ግሩም የትርጉም ሥራ ነው!” በማለት ተናግሯል።

በስኮቲሽ ጌሊክ ቋንቋ jw.org በተለቀቀ በመጀመሪያው ወር ብቻ ወደ 750 የሚያህሉ ሰዎች ጎብኝተውታል።

በአየርላንድ፣ ጎልዌይ ናሽናል ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምር አንድ ሰው ለሃይማኖት ምንም ፍላጎት እንደሌለው ለአንድ የይሖዋ ምሥክር ተናግሮ ነበር። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ—የያዘው መልእክት ምንድን ነው? የተባለው ብሮሹር በአይሪሽ እንደሚገኝ ሲያውቅ አንድ ቅጂ እንዲላክለት ጥያቄ አቀረበ። ‘ሁሉም ሰው በአፍ መፍቻ ቋንቋው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ማግኘት ይገባዋል’ የሚል አመለካከት ስለነበረው የይሖዋ ምሥክሮች በአይሪሽ ቋንቋ ጽሑፍ ለማዘጋጀት ላደረጉት ጥረት አመስጋኝነቱን ገለጸ።

አንዲት አረጋዊት በዌልሽ ቋንቋ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ብሮሹር ካገኙ በኋላ ደስታቸውን እንዲህ በማለት ገልጸዋል፦ “እውነቱን ለመናገር፣ የሰጣችሁኝ ጽሑፍ በእንግሊዝኛ የተዘጋጀ ቢሆን ኖሮ መቀበሌን እጠራጠራለሁ፤ በገዛ ቋንቋዬ ማግኘት መቻሌ ግን በጣም አስደስቶኛል።”

በነሐሴ 2014 jw.org ላይ በዌልሽ ቋንቋ የሚገኙት ጽሑፎች ብዛት እንዲጨምር ተደርጓል። በመሆኑም በዚያ ወር፣ በዌልሽ የተዘጋጁ ጽሑፎችን ለማንበብ ድረ ገጻችንን የጎበኙ ሰዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሮ ነበር።

“አንድ ዓይነት ቋንቋ እንናገራለን”

ኢየሱስ ለሁለት ደቀ መዛሙርቱ ቅዱሳን መጽሐፍትን በግልጽ ካብራራላቸው በኋላ በደስታ ተውጠው “በመንገድ ላይ ሲያነጋግረንና ቅዱሳን መጻሕፍትን በግልጽ ሲያብራራልን ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረም?” ተባባሉ። (ሉቃስ 24:32 የግርጌ ማስታወሻ) ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በግልጽ ሲብራራላቸው አብዛኛውን ጊዜ በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ለውጥ ያደርጋሉ።

በዌልስ የሚኖር ኤሚር የተባለ አንድ ሰው፣ ሚስቱ የይሖዋ ምሥክር ብትሆንም እሷ በምታደርገው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ አንድም ቀን አብሯት ተካፍሎ አያውቅም። በኋላ ላይ ግን ረስል ከተባለ የይሖዋ ምሥክር ጋር ጓደኛሞች ሆኑ። ኤሚር አመለካከቱን እንዲቀይር የረዳው ነገር ምን እንደሆነ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ረስል፣ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? b የተባለውን መጽሐፍ ይዞልኝ ሲመጣ መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር ለማጥናት ወሰንኩ። መጽሐፉን ሰጥቶ እንዲህ አለኝ፦ ‘ይህ መጽሐፍ በዌልሽ ቋንቋ የተዘጋጀ ነው። በመሆኑም ከዛሬ ጀምሮ መጽሐፉን አብረን እናጠናለን።’” ኤሚር፣ ረስል ባቀረበለት ቀጥተኛ ግብዣ የተስማማው ለምንድን ነው? እንዲህ በማለት ገልጿል፦ “አንድ ዓይነት ቋንቋ እንናገራለን፣ ባሕላችንም ተመሳሳይ ነው፤ እርስ በርስ ደግሞ እንግባባለን።” ኤሚር የአፍ መፍቻ ቋንቋው በሆነው በዌልሽ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና ሐሳቡን በግልጽ መረዳት በመቻሉ ልቡ ‘ይቃጠልበት’ ነበር።

የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሰዎች ልባቸው በጥልቅ እንዲነካ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ለመርዳት ጥረት ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ።

a ብሪታንያ የሚለው ቃል እንግሊዝን፣ ስኮትላንድንና ዌልስን ያጠቃልላል።

b የይሖዋ ምሥክሮች ያዘጋጁት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ ጽሑፍ።