መስከረም 11, 2019
ቼክ ሪፑብሊክ
የይሖዋ ምሥክሮች የተሻሻለውን አዲስ ዓለም ትርጉም በቼክ እና በስሎቫክኛ ቋንቋዎች አወጡ
የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም በቼክ እና በስሎቫክኛ ቋንቋዎች መውጣቱ መስከረም 7, 2019 ተገለጸ። የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ስቲቨን ሌት መጽሐፍ ቅዱሶቹ መውጣታቸውን ያበሰረው በኦስትራቫ፣ ቼክ ሪፑብሊክ በተደረገ ልዩ የሆነ ስብሰባ ላይ ነበር። ይህ ልዩ ስብሰባ በቼክ ሪፑብሊክና በስሎቫኪያ ወደሚገኙ ከ200 የሚበልጡ አካባቢዎች የተላለፈ ሲሆን አጠቃላይ የተሰብሳቢዎች ቁጥር 25,284 ነበር።
ሁለቱንም መጽሐፍ ቅዱሶች የተረጎሙት ቡድኖች የትርጉም ሥራውን ለማከናወን ከአራት ዓመት በላይ ወስዶባቸዋል። የተሻሻሉት ትርጉሞች ያላቸው ዋነኛ ጥቅም ለመረዳት ቀላል መሆናቸው ነው። የስሎቫክኛ ቋንቋ የትርጉም ቡድን አባል የሆነ አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮቹን ሲያነቡ እንደሚመሰጡ እርግጠኛ ነኝ። ጽሑፉ ጥሩ ፍሰትና ለዛ ያለው ነው፤ ይህም አንባቢው የታሪኩን መጨረሻ ለማወቅ እንዲጓጓና ማንበብ ማቆም እንዲከብደው ያደርጋል።”
በቼክ ሪፑብሊክ ከ15,000 በላይ፣ በስሎቫኪያ ደግሞ ከ11,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ፤ ሁሉም ከእነዚህ ትርጉሞች ጥቅም እንደሚያገኙ እንተማመናለን። የቼክ ቋንቋ የትርጉም ቡድን አባል የሆነ አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም አጫጭር ዓረፍተ ነገሮችና ዘመናዊ ቋንቋ በመጠቀም በበኩረ ጽሑፉ ውስጥ ያለውን መልእክት በግልጽ ያስተላልፋል። እውነት ቤት ለብዙ ዓመታት የቆዩ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ በቅርቡ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሰዎችና ወጣቶችም በቀላሉ ሊረዱት ይችላሉ።”
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉ ወይም በከፊል በ184 ቋንቋዎች ተተርጉሟል፤ ከእነዚህ መካከል በ2013 በወጣው እትም ላይ ተመሥርተው ተሻሽለው የወጡ 29 ቋንቋዎችም ይገኙበታል። አንባቢዎች በአምላክ ቃል እውነት ልባቸው እንዲነካ በማድረግ ረገድ እነዚህ አዳዲስ መጽሐፍ ቅዱሶች የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ተስፋ እናደርጋለን።—ሉቃስ 24:32