በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በግዞት ወደ ባቢሎን ስለተወሰዱት አይሁዳውያን የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ትክክለኛ ነው?

በግዞት ወደ ባቢሎን ስለተወሰዱት አይሁዳውያን የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ትክክለኛ ነው?

 ከ2,600 ዓመታት በፊት አይሁዳውያን ወደ ባቢሎን በግዞት ተወስደው ነበር፤ በዚያም ለ70 ዓመት ገደማ ቆይተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በግዞት የተወሰዱት አይሁዳውያን በባቢሎን የሚኖራቸውን ሕይወት በተመለከተ አምላክ ምን ትንቢት እንደተናገረ ይገልጻል፤ እንዲህ ይላል፦ “ቤት ሠርታችሁ በዚያ ኑሩ። አትክልት ተክላችሁ ፍሬውን ብሉ። ሚስት አግብታችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ውለዱ፤ . . . በግዞት ተወስዳችሁ እንድትኖሩባት ላደረግኳት ከተማም ሰላምን ፈልጉ።” (ኤርምያስ 29:1, 4-7) የአይሁዳውያኑ ሕይወት በእርግጥ ይህን ይመስል ነበር?

 ተመራማሪዎች በጥንቷ ባቢሎን ወይም በአቅራቢያዋ እንደተገኙ በሚታመኑ ከ100 የሚበልጡ የሸክላ ጽላቶች ላይ ምርምር አድርገዋል። ጽላቶቹ በርካታ አይሁዳውያን ግዞተኞች ባሕላቸውንና ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ለባቢሎናውያን እየተገዙ በሰላም እንደኖሩ ይጠቁማሉ። እነዚህ ጽላቶች የተዘጋጁት ከ572 እስከ 477 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ይገመታል፤ ጽላቶቹ የኪራይ ውል፣ የብድር ስምምነት እንዲሁም የንግድና ሌሎች የሒሳብ መዝገቦችን የያዙ ናቸው። አንድ ማመሣከሪያ እንደገለጸው “እነዚህ ሰነዶች ግዞተኞቹ በገጠራማ አካባቢ እንደሚኖር እንደ ማንኛውም ሰው መሬት ያርሱ፣ ቤት ይገነቡ፣ ግብር ይከፍሉ ብሎም ንጉሡን ያገለግሉ እንደነበር ያሳያሉ።”

በይሁዳ ሰፈር የተገኘ ጽላት

 በተጨማሪም እነዚህ ሰነዶች “አል ያሁዱ” ወይም “ይሁዳ ሰፈር” በመባል በሚጠራ አካባቢ ውስጥ የሚኖሩ በርካታ አይሁዳውያን እንደነበሩ ያረጋግጣሉ። አንድን አይሁዳዊ ቤተሰብ እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ በስም የሚገልጹ ጽላቶች ተገኝተዋል፤ አንዳንዱ ስም የተጻፈው በጥንታዊ የዕብራይስጥ ፊደላት ነው። ጽላቶቹ ከመገኘታቸው በፊት ምሁራን በባቢሎን ስለነበሩት አይሁዳውያን ግዞተኞች ሕይወት የነበራቸው ግንዛቤ እጅግ ውስን ነበር። የእስራኤል ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን የአመራር ቦርድ አባል የሆኑት ዶክተር ፊሊፕ ቩካሳቮቪች እንዲህ ብለዋል፦ “በስተ መጨረሻ በእነዚህ ጽላቶች አማካኝነት ሰዎቹን መተዋወቅ ማለትም ስማቸውን፣ የኖሩበትን ዘመንና ቦታ እንዲሁም ያከናወኗቸውን ነገሮች ማወቅ ችለናል።”

ግዞተኞቹ አይሁዳውያን በባቢሎን አንጻራዊ ነፃነት ነበራቸው

 በግዞት የሄዱት አይሁዳውያን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ አንጻራዊ ነፃነት ነበራቸው። ዶክተር ቩካሳቮቪች አይሁዳውያኑ “በአል ያሁዱ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ሌሎች ከተሞችም ይኖሩ” እንደነበር ገልጸዋል። አንዳንዶቹ የተለያዩ ሙያዎችን መማር ችለው ነበር፤ እነዚህ ሙያዎች ከጊዜ በኋላ ኢየሩሳሌምን መልሰው ሲገነቡ ጠቅመዋቸዋል። (ነህምያ 3:8, 31, 32) የአል ያሁዱ ጽላቶች የግዞቱ ዘመን ካበቃ በኋላም በርካታ አይሁዳውያን በባቢሎን ለመቅረት እንደወሰኑ ያረጋግጣሉ። ይህም የአምላክ ቃል እንደተናገረው አይሁዳውያን ባቢሎን ውስጥ በአንጻራዊ ሁኔታ ሰላማዊ ሕይወት ይመሩ እንደነበረ ያሳያል።