በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

ከወረርሽኙ በፊት የተከናወኑ የግንባታ ሥራዎች

ከወረርሽኙ በፊት የተከናወኑ የግንባታ ሥራዎች

ኅዳር 1, 2020

 በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየተጠመቁ በመሆኑ፣ ለይሖዋ አምልኮ የምንጠቀምባቸው ተጨማሪ ሕንፃዎች በየጊዜው ያስፈልጉናል። ይህን ፍላጎት ለማሟላት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአካባቢ ንድፍና ግንባታ ዲፓርትመንቶች በ2020 የአገልግሎት ዓመት ከ2,700 የሚበልጡ የአምልኮ ቦታዎችን ለመገንባት ወይም ለማደስ ዕቅድ አውጥተው ነበር። a

 የሚያሳዝነው በኮቪድ-19 ሳቢያ እነዚህ ዕቅዶች ተስተጓጉለዋል። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለበሽታው እንዳይጋለጡ ለማድረግና መንግሥት የጣላቸውን ገደቦች ለማክበር ሲባል የበላይ አካሉ የሕትመት ኮሚቴ በዓለም ዙሪያ ያሉ አብዛኞቹ የግንባታ ሥራዎች ለጊዜው እንዲቋረጡ አደረገ። ያም ቢሆን በ2020 የአገልግሎት ዓመት ከ1,700 በላይ የአምልኮ ቦታዎች ተገንብተዋል እንዲሁም እድሳት ተደርጎላቸዋል። በተጨማሪም ከ100 በላይ ትላልቅ የቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ሥራዎች ተጠናቅቀዋል። ከተጠናቀቁት ግንባታዎች ሁለቱ ወንድሞቻችን የጠቀሟቸው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

 የካሜሩን ቅርንጫፍ ቢሮ። በዱዋላ የሚገኘው የቀድሞው ቅርንጫፍ ቢሮ በጣም ትንሽ ከመሆኑም ሌላ ከበድ ያለ እድሳት ያስፈልገው ነበር። የሕትመት ኮሚቴው ቅርንጫፍ ቢሮውን ለማደስ አስቦ ነበር፤ ሆኖም ለእድሳት የሚያስፈልገው ወጪ ከሕንፃው ዋጋ እንደሚበልጥ ታወቀ። ከዚህም ሌላ አዲስ መሬት ገዝቶ ቅርንጫፍ ቢሮ ለመገንባት አሊያም ሌላ ሕንፃ ገዝቶ ለማደስ ታስቦ ነበር፤ ሆኖም ሁለቱም አማራጮች አልተሳኩም።

 ይህ በእንዲህ እንዳለ ወንድሞቻችን፣ መንግሥት ከዱዋላ በስተ ሰሜን መንገድ ለመሥራት እንዳሰበ አወቁ፤ መንገዱ የሚያልፈው ለትላልቅ ስብሰባዎች በምንጠቀምበት አንድ አዳራሽ በኩል ነው። ይህ መንገድ አዳራሹን ይበልጥ ተደራሽ የሚያደርገው ከመሆኑም ሌላ ሕንፃው መሠረተ ልማት እንዲያገኝ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። እነዚህ ሁኔታዎች የቅርንጫፍ ቢሮውን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ የሚያሟሉ ነበሩ። በመሆኑም የበላይ አካሉ ከትላልቅ ስብሰባ አዳራሹ መሬት የተወሰነው ክፍል ላይ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲገነባ ፈቃድ ሰጠ።

ወንድሞችና እህቶች በአዲሱ የካሜሩን ቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ሲካፈሉ

 የግንባታውን ሥራ ያከናወኑት፣ ወንድሞቻችንና ሕንፃ ተቋራጮች በኅብረት ሆነው ነው፤ ይህ አሠራር ጊዜና ገንዘብ ቆጥቧል። እንዲያውም ሥራው ከታሰበለት በጀት በሁለት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ባነሰ ወጪ መጠናቀቅ ችሏል! የቤቴል ቤተሰብ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ወደ አዲሱ ሕንፃ መዛወር ችሏል።

የካሜሩን ቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት ተጠናቅቋል

 በካሜሩን የሚገኙ ቤቴላውያን የተሻለ መኖሪያ እና የሥራ ቦታ በማግኘታቸው ተጠቅመዋል፤ አዲሱን ቅርንጫፍ ቢሮ ከይሖዋ እንዳገኙት ስጦታ አድርገው ይመለከቱታል። አንድ ባልና ሚስት “ይበልጥ በትጋት ለመሥራት ተነሳስተናል፤ ይህን ስጦታ አቅልለን መመልከት አንፈልግም” ብለዋል።

ወንድሞችና እህቶች ከወረርሽኙ በፊት በአዲሱ ቢሯቸው ሲሠሩ

 የቶሆላባል የርቀት የትርጉም ቢሮ፣ ሜክሲኮ። የቶሆላባል የትርጉም ቡድን ለበርካታ ዓመታት ሥራውን ያከናውን የነበረው በሜክሲኮ ሲቲ አቅራቢያ በሚገኘው የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ነበር። ይሁንና የቶሆላባል ቋንቋ በዋነኝነት የሚነገረው ከቅርንጫፍ ቢሮው 1,000 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በሚገኙት በአልታሚራኖ እና በላስ ማርጋሪታስ ነው! በዚህም የተነሳ የቶሆላባል ቋንቋ ተርጓሚዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በቋንቋው ላይ የሚደረጉትን ለውጦች ማወቅ አስቸጋሪ ሆኖባቸው ነበር። ከዚህም ሌላ ቅርንጫፍ ቢሮው ለቶሆላባል ቋንቋ ትርጉምና ቅጂ ሊያግዙ የሚችሉ ብቃት ያላቸው ወንድሞችና እህቶችን ለማግኘት ተቸግሮ ነበር።

ወንድሞችና እህቶች በርቀት የትርጉም ቢሮ ግንባታ ሥራ ሲካፈሉ

 በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ የበላይ አካሉ የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ የትርጉም ክፍሉ የቶሆላባል ቋንቋ ወደሚነገርበት አካባቢ እንዲዛወር አሰበ። በመሆኑም ቅርንጫፍ ቢሮው አዲስ ሕንፃ ገዝቶ ለማደስ ወሰነ። እንዲህ ማድረግ አዲስ ሕንፃ ከመገንባትም ሆነ ቢሮዎች ከመከራየት ይረክሳል።

 አንድ ተርጓሚ ያገኘውን ጥቅም ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ ተርጓሚ ሆኜ በሠራሁባቸው አሥር ዓመታት ውስጥ ቋንቋዬን የሚናገር አንድም ቤተሰብ በአቅራቢያዬ አግኝቼ አላውቅም። የአሁኑ ቢሯችን የሚገኘው ቶሆላባል በዋነኝነት በሚነገርበት ቦታ ነው። በየቀኑ የቶሆላባል ቋንቋ ተናጋሪዎችን አገኛለሁ። ይህም አዳዲስ ቃላት እንድማር የረዳኝ ከመሆኑም ሌላ የሥራዬን ጥራት አሻሽሎታል።”

የቶሆላባል የትርጉም ቢሮ ከእድሳት ሥራው በፊት እና በኋላ

ለ2021 የአገልግሎት ዓመት የታሰቡ ሥራዎች

 ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነ በ2021 የአገልግሎት ዓመት 75 የርቀት የትርጉም ቢሮዎችን እና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ሕንፃዎችን ለመገንባት ታቅዷል። ከስምንት ትላልቅ የቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታዎች ጋር በተያያዘ እየተከናወነ ያለው ሥራም ይቀጥላል፤ ይህም በራማፖ፣ ኒው ዮርክ የሚካሄደውን ግንባታ እንዲሁም የአርጀንቲና እና የጣሊያን ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ወደ ሌላ አካባቢ የማዛወር ሥራን ይጨምራል። በተጨማሪም ከ1,000 በላይ አዳዲስ የስብሰባ አዳራሾች ያስፈልጉናል፤ በአሁኑ ወቅት የምንጠቀምባቸው ከ6,000 በላይ የአምልኮ ቦታዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ስላልሆኑ ሊቀየሩ ይገባል፤ እንዲሁም እድሳት የሚያስፈልጋቸው 4,000 የስብሰባ አዳራሾች አሉ።

 ለዚህ ሁሉ የግንባታና የእድሳት ሥራ የሚሆነውን ገንዘብ የምናገኘው ከየት ነው? የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ላዛሮ ጎንዛሌዝ፣ የቶሆላባል የርቀት የትርጉም ቢሮ ግንባታን በተመለከተ የሰጠው ሐሳብ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል። እንዲህ ብሏል፦ “በእኛ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ወንድሞች የገንዘብ አቅማቸው ውስን ነው። ስለዚህ የዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበር ድጋፍ ባናገኝ ኖሮ በዚህ አገር ለሚኖሩ ወንድሞች የትርጉም ቢሮዎች መገንባት ከአቅማችን በላይ ይሆንብን ነበር። በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ወንድሞቻችን ያደረጉት መዋጮ፣ ተርጓሚዎች የሚተረጉሙት ቋንቋ በሚነገርበት አካባቢ መኖር እንዲችሉ አስተዋጽኦ አድርጓል። ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር በልግስና ለሚያደርግልን ድጋፍ ከልብ እናመሰግናለን።” በእርግጥም እነዚህ የግንባታ ሥራዎች መሳካት የቻሉት እናንተ ለዓለም አቀፉ ሥራ በምታደርጉት መዋጮ ነው፤ አብዛኞቹ መዋጮዎች የሚደረጉት በ​donate.jw.org አማካኝነት ነው።

a የአካባቢ ንድፍና ግንባታ ዲፓርትመንቶች በቅርንጫፍ ቢሯቸው ክልሎች ውስጥ ለሚካሄዱ የስብሰባ አዳራሾች ግንባታ ዕቅድ ያወጣሉ እንዲሁም ሥራውን ያስፈጽማሉ። በዋናው መሥሪያ ቤት የሚገኘው ዓለም አቀፍ ንድፍና ግንባታ ዲፓርትመንት ደግሞ በዓለም ዙሪያ ከሚካሄዱ የግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል የትኛው ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ይወስናል፤ እንዲሁም ሥራውን ያስተባብራል።