በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፖርቹጋል ቋንቋ የተዘጋጀው የመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ—የጽናት ታሪክ

በፖርቹጋል ቋንቋ የተዘጋጀው የመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ—የጽናት ታሪክ

በፖርቹጋል ቋንቋ የተዘጋጀው የመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ​—የጽናት ታሪክ

“የጸና ሰው ስኬታማ ይሆናል።” ይህ መርሕ የሚገኘው ዥዋው ፌሬራ ዴ አልሜዳ የተባለው ሰው በ17ኛው መቶ ዘመን በጻፈው ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው በራሪ ወረቀት የፊት ገጽ ላይ ነው። በሕይወቱ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ፖርቹጋል ቋንቋ በመተርጎምና በማሳተም ሥራ ተጠምዶ የኖረን ሰው ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ከዚህ የተሻለ አባባል የለም።

አልሜዳ፣ በ1628 በሰሜናዊ ፖርቹጋል በምትገኝ ቶሪ ዴ ታቫሬዝ በተባለች መንደር ውስጥ ተወለደ። ወላጆቹ በልጅነቱ ስለሞቱ ያሳደገው በፖርቹጋል ዋና ከተማ በሊዝበን የሚኖረውና መነኩሴ የሆነው አጎቱ ነበር። አልሜዳ ቄስ ለመሆን ሲዘጋጅ ጥሩ ትምህርት እንዳገኘ ይታመናል፤ ይህ ደግሞ ገና በልጅነቱ ለየት ያለ የቋንቋ ችሎታ እንዲኖረው ረድቶታል።

ይሁን እንጂ አልሜዳ ከፖርቹጋል ባይወጣ ኖሮ ይህን ችሎታውን መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም አይጠቀምበትም ነበር። በወቅቱ የነበረው የተሃድሶ እንቅስቃሴ በሰሜናዊውና በመካከለኛው አውሮፓ በሕዝቡ ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ በስፋት እንዲሰራጭ ቢያደርግም በፖርቹጋል ግን መናፍቆችን ለመቅጣት የተቋቋመው የካቶሊክ ፍርድ ቤት (ኢንኩዊዚሽን) ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር። አንድ ሰው በአገሪቱ በሚነገረው ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ስለያዘ ብቻ እንኳ በዚህ የካቶሊክ ፍርድ ቤት ፊት ይቀርብ ነበር። a

አልሜዳ፣ እንዲህ ዓይነቱን ጨቋኝ ሁኔታ ለመሸሽ ይመስላል በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለ ወደ ኔዘርላንድስ ሄደ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ገና በ14 ዓመቱ በባታቪያ (የአሁኗ ጃካርታ)፣ ኢንዶኔዥያ በኩል አድርጎ ወደ እስያ ጉዞ ጀመረ። በወቅቱ ባታቪያ፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያ የሚገኘው ደች ኢስት ኢንዲያ የተባለው ኩባንያ የአስተዳደር ማዕከል ነበረች።

በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ተርጓሚ

አልሜዳ ወደ እስያ ያደረገውን ጉዞ ሲያገባድድ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ሁኔታ አጋጠመው። ከባታቪያ ተነስቶ ወደ ማላካ (የአሁኗ መላካ)፣ ምዕራባዊ ማሌዢያ በመርከብ ሲጓዝ ዲፈረንስያስ ዴ ላ ክሪስቲያንዳድ (በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉት ልዩነቶች) የሚል በስፔን ቋንቋ የተዘጋጀ የፕሮቴስታንቶች በራሪ ወረቀት አገኘ። ይህ በራሪ ወረቀት የሐሰት መሠረተ ትምህርቶችን ከማውገዙም በላይ የወጣቱን አልሜዳ ትኩረት የሳበውን የሚከተለውን ሐሳብ ይዞ ነበር:- “ለአምላክ ክብር ለመስጠት ተብሎ ቢሆንም እንኳ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ [በሕዝቡ ዘንድ] በማይታወቅ ቋንቋ መጠቀም ቋንቋውን ለማይረዳው አድማጭ ምንም ጥቅም የለውም።”—1 ቆሮንቶስ 14:9

በዚህ ጽሑፍ ላይ ለማስተላለፍ የተፈለገው ነጥብ ለአልሜዳ ግልጽ ነበር:- ሃይማኖታዊ ስህተቶችን ለማጋለጥ ቁልፉ መጽሐፍ ቅዱስን ሁሉም ሰው ሊረዳው በሚችለው መንገድ ማዘጋጀት ነው። አልሜዳ፣ ማላካ ሲደርስ ሃይማኖቱን ለውጦ የደች ተሃድሶ ሃይማኖት ተከታይ በመሆን ወዲያውኑ የተወሰኑ የወንጌሎችን ክፍሎች ከስፔን ወደ ፖርቹጋል ቋንቋ መተርጎም ጀመረ፤ ትርጉሞቹንም “እውነትን ለማወቅ ልባዊ ፍላጎት እንዳላቸው ላሳዩ ሰዎች” ያሰራጭ ነበር። b

ከሁለት ዓመት በኋላ አልሜዳ ታላቅ ሥራ ለማከናወን ይኸውም ሙሉውን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ከላቲኑ ቩልጌት ወደ ፖርቹጋል ቋንቋ ለመተርጎም ተዘጋጀ። ትርጉሙን ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ያጠናቀቀ ሲሆን ይህም ለአንድ የ16 ዓመት ልጅ በጣም የሚደነቅ ሥራ ነበር! ትርጉሙም እንዲታተምለት በባታቪያ ወደሚገኙት የደች ዋና አስተዳዳሪ በድፍረት ላከው። በባታቪያ የነበረው የተሃድሶ ቤተ ክርስቲያን የአልሜዳን ትርጉም ወደ አምስተርዳም የላከው ይመስላል፤ ሆኖም ሥራው በኃላፊነት የተሰጣቸው አረጋዊ አገልጋይ በዚህ መሃል በመሞታቸው የአልሜዳ ትርጉም ጠፋ።

በ1651 በሲሎን (የአሁኗ ስሪ ላንካ) የሚገኘው የተሃድሶ ጉባኤ የትርጉም ሥራውን ግልባጭ እንዲያዘጋጅ አልሜዳን ጠየቀው፤ በዚህ ወቅት አልሜዳ ዋናው ቅጂ ከቤተ ክርስቲያኑ ቤተ መዛግብት እንደጠፋ አወቀ። ይህ ወጣት በዚህ ተስፋ ሳይቆርጥ እንደምንም አንድ ቅጂ (ምናልባትም የመጀመሪያውን ረቂቅ) አገኘ፤ ከዚያም በቀጣዩ ዓመት የወንጌሎችንና የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ የታረመ ቅጂ ሠርቶ አጠናቀቀ። በዚህም ምክንያት በባታቪያ የሚገኘው የተሃድሶ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር አካል ለአልሜዳ 30 ጊልደር በሽልማት መልክ ሰጠው። ከአልሜዳ የሥራ ባልደረቦች አንዱ ይህ ሽልማት አልሜዳ “ላከናወነው ታላቅ ሥራ የተሰጠ እዚህ ግባ የማይባል ገንዘብ” እንደሆነ ጽፏል።

አልሜዳ ለሥራው እውቅና ባይሰጠውም የጀመረውን በመቀጠል በ1654 ሙሉውን የአዲስ ኪዳን የታረመ ቅጂ አቀረበ። በዚህ ወቅት የትርጉም ሥራው እንዲታተም እንደገና ሐሳብ ቢቀርብም በአንዳንድ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉ ጥቂት በእጅ የተገለበጡ ቅጂዎች ከመዘጋጀታቸው በስተቀር ይህ ነው የሚባል ተግባር አልተከናወነም።

የካቶሊክ ፍርድ ቤት አወገዘው

አልሜዳ በቀጣዩ አሥር ዓመት በተሃድሶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፓስተር ሆኖ በማገልገልና በሚስዮናዊነት ሥራ ተጠምዶ ነበር። በ1656 ፓስተር ሆኖ እንዲያገለግል ተሾመ። ከዚያም በመጀመሪያ በሲሎን ያገለገለ ሲሆን በዚህች አገር በዝሆን ተረግጦ ከመሞት ለጥቂት አመለጠ። ቀጥሎም በሕንድ ከመጀመሪያዎቹ የፕሮቴስታንት ሚስዮናውያን አንዱ ሆኖ አገልግሏል።

አልሜዳ ወደ ፕሮቴስታንት እምነት ተቀይሮ በባዕድ አገር የሚያገለግል ሰው በመሆኑ ይጎበኛቸው ከነበሩት የፖርቹጋል ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች ውስጥ አብዛኞቹ እንደ ከሃዲ ይመለከቱት ነበር። በቀሳውስቱ መካከል የሚታየውን ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት በቀጥታ በማውገዙና የቤተ ክርስቲያኗን መሠረተ ትምህርቶች በማጋለጡ ከካቶሊክ ሚስዮናውያን ጋር ብዙ ጊዜ ይጋጭ ነበር። ይህ ግጭት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ በ1661 በጎኣ፣ ሕንድ የሚገኝ የካቶሊክ ፍርድ ቤት አልሜዳ መናፍቅ እንደሆነ በመግለጽ የሞት ፍርድ በየነበት። እሱ በሌለበት ምስሉን ሠርተው በእሳት አቃጠሉት። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የደች ዋና አስተዳዳሪ፣ አልሜዳ ተከራካሪ መሆኑ ስላሳሰባቸው ሳይሆን አይቀርም ወደ ባታቪያ አስጠሩት።

አልሜዳ ቀናተኛ ሚስዮናዊ የነበረ ቢሆንም በፖርቹጋል ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስፈልግ በፍጹም አልዘነጋም። እንዲያውም ቀሳውስቱም ሆኑ ምዕመናኑ መጽሐፍ ቅዱስን አለማወቃቸው ያስከተለው ውጤት ቅዱስ ጽሑፉን ወደ ፖርቹጋል ቋንቋ ለመተርጎም ያደረገውን ውሳኔ ይበልጥ አጠናከረለት። በ1668 በተዘጋጀ አንድ ሃይማኖታዊ ትራክት መቅድም ላይ አልሜዳ ለአንባቢዎቹ እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በቋንቋችሁ በማዘጋጀት ማንም ሊያበረክትላችሁ ከሚችለው የላቀ ስጦታ እንዲሁም እጅግ ውድ የሆነ ሀብት በመስጠት አክብሮቴን እንደማሳያችሁ . . . ተስፋ አደርጋለሁ።”

አልሜዳና ትርጉሙን የሚያርመው ኮሚቴ

በ1676 አልሜዳ፣ የመጨረሻው የአዲስ ኪዳን ረቂቅ እንዲታረም በባታቪያ ለሚገኘው የተሃድሶ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር አካል አቀረበ። ገና ከመጀመሪያው በአልሜዳና በአራሚዎቹ መካከል የነበረው ግንኙነት ሻክሮ ነበር። ያን ሉድቪክ ስዌሌንክሬብል የተባሉት የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ እንደገለጹት የደች ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት የአልሜዳ የሥራ ባልደረቦች አንዳንድ ጥቃቅን የትርጉምና የአጻጻፍ ልዩነቶችን መረዳት አስቸግሯቸው ሊሆን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ አልሜዳ በተጠቀመበት ቋንቋ ረገድ ውዝግብ ተነስቶ ነበር። መጽሐፍ ቅዱሱ ሕዝቡ በሚጠቀምበት ቋንቋ ይተርጎም ወይስ ብዙዎች ለመረዳት በሚከብዳቸው የጠራ የፖርቹጋል ቋንቋ ቢዘጋጅ ይሻላል? በዚህ ላይ ደግሞ አልሜዳ ሥራው ተጠናቅቆ ለማየት የነበረው ጉጉት ብዙ ጊዜ ግጭት እንዲፈጠር ያደርግ ነበር።

በአራሚዎቹ መካከል በተፈጠረው ውዝግብ አሊያም ለሥራው ትኩረት ባለመስጠታቸው የተነሳ ሥራው ተንጓተተ። ከአራት ዓመታት በኋላ እንኳ አራሚዎቹ በሉቃስ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፎች ላይ ይነታረኩ ነበር። አልሜዳ ይህን ያህል መዘግየታቸው ስላበሳጨው አራሚዎቹ ሳያውቁ ትርጉሙ እንዲታተምለት ወደ ኔዘርላንድስ ላከው።

የተሃድሶ ቤተ ክርስቲያኑ የአስተዳደር አካል፣ ትርጉሙ እንዳይታተም ጥረት ቢያደርግም የአልሜዳ አዲስ ኪዳን በ1681 በአምስተርዳም ታተመና በቀጣዩ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ቅጂዎች ባታቪያ ደረሱ። አልሜዳ፣ በኔዘርላንድስ የሚገኙት አራሚዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሙ ላይ ማስተካከያ እንዳደረጉ ሲያውቅ ምን ያህል አዝኖ ሊሆን እንደሚችል አስብ! አልሜዳ፣ አራሚዎቹ የፖርቹጋልን ቋንቋ ስለማያውቁት “መንፈስ ቅዱስ ሊያስተላልፍ የፈለገውን ሐሳብ የሚሸፍን ግራ የሚያጋባና እርስ በርሱ የሚጋጭ ትርጉም” እንደጨመሩ ተመለከተ።

የደች መንግሥትም በትርጉም ሥራው ባለመደሰቱ የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉ እንዲወገድ ትእዛዝ አስተላለፈ። እንደዚህም ሆኖ አልሜዳ፣ በጣም ከባድ የሆኑት ስህተቶች በእጅ መስተካከል እንደሚችሉ በመናገር የመንግሥት ባለ ሥልጣናቱን ጥቂት ቅጂዎችን እንዲያስቀሩ አሳመናቸው። የታረመው መጽሐፍ ቅዱስ እስኪዘጋጅ ድረስ እነዚህ ቅጂዎች ጥቅም ላይ ውለው ነበር።

በባታቪያ የነበሩት አራሚዎች የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ማረማቸውን ለመቀጠል እንደገና ተሰባሰቡ፤ እንዲሁም አልሜዳ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ተርጉሞ ሲጨርስ መጻሕፍቱን ለማረም ተዘጋጁ። የተሃድሶ ቤተ ክርስቲያኑ የአስተዳደር አካል፣ አልሜዳ ትዕግሥት አጥቶ አንድ እርምጃ እንዳይወስድ በመፍራት የትርጉም ሥራው ተጠናቅቆ የተፈረመበት ቅጂ በቤተ ክርስቲያኑ ካዝና ውስጥ እንዲቀመጥ ወሰነ። ይሁን እንጂ አልሜዳ በዚህ ውሳኔ አልተስማማም።

በዚህ ጊዜ አልሜዳ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሲለፋ መቆየቱና ቆላማ በሆነ አካባቢ መኖሩ በጤንነቱ ላይ ጉዳት አስከትሎ ነበር። በ1689 ጤንነቱ እያሽቆለቆለ በመሄዱ አልሜዳ የቤተ ክርስቲያን ሥራዎችን አቁሞ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመተርጎሙ ሥራ ላይ ትኩረት አደረገ። የሚያሳዝነው ግን በ1691 የሕዝቅኤልን መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፍ እየተረጎመ እያለ በሞት አንቀላፋ።

ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ የተጠናቀቀው የአዲስ ኪዳን ሁለተኛ እትም በ1693 ለሕትመት በቃ። በዚህ ጊዜም ቢሆን ችሎታ የሌላቸው አራሚዎች ሥራዎቹን አበላሽተውበት ነበር። ጊለየርም ሉዊስ ሳንቶስ ፌሬራ፣ ኣ ቢብሊያ ኦም ፖርቱጋል (በፖርቹጋል ቋንቋ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “አራሚዎቹ . . . ግሩም በሆነው የአልሜዳ ትርጉም ላይ የጎላ ለውጥ አድርገዋል፤ በመጀመሪያው እትም ላይ አራሚዎቹ ሳይነካኩት ያለፉትን ሐሳብ ሁለተኛውን እትም ያረሙት ሰዎች በመቀያየር ትርጉሙን ያበላሹት ከመሆኑም በላይ ውበቱን አጥፍተውታል።”

በፖርቹጋል ቋንቋ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ተጠናቀቀ

አልሜዳ ከሞተ በኋላ በፖርቹጋል ቋንቋ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲታረምና እንዲታተም ግፊት የሚያደርግ ሰው በባታቪያ አልነበረም። በኋላም ቢሆን በትራንኩባር፣ ደቡባዊ ሕንድ ያገለግሉ የነበሩትን የዴንማርክ ሚስዮናውያን ጥያቄ ለማሟላት ሲል በ1711 የአልሜዳ አዲስ ኪዳን ሦስተኛ እትም እንዲዘጋጅ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው በለንደን የሚገኝ ክርስቲያናዊ እውቀትን የሚያስፋፋ ማኅበር ነበር።

ይኸው ማኅበር በትራንኩባር የሕትመት ሥራ እንዲከናወን ወሰነ። ይሁን እንጂ የሕትመት ቁሳቁሶችንና በፖርቹጋል ቋንቋ የተተረጎሙትን ለሕትመት የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሶች ይዛ ወደ ሕንድ ትጓዝ የነበረችው መርከብ በፈረንሳይ የባሕር ሽፍቶች የተያዘች ሲሆን ከጊዜ በኋላ በሪዮ ዴ ጄኔሮ፣ ብራዚል ተገኘች። ሳንቶስ ፌሬራ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የተፈጠረውን ሁኔታ ለመረዳት አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ብዙዎች እንደ ተአምር ቢቆጥሩትም የሕትመት ቁሳቁሶቹን የያዙት ሣጥኖች በመርከቧ ዕቃ መጫኛ ታችኛው ክፍል ውስጥ ምንም ሳይሆኑ የተገኙ ሲሆን በዚሁ መርከብ ወደ ትራንኩባር አቅንተዋል።” በትራንኩባር የነበሩት የዴንማርክ ሚስዮናውያን የቀሩትን የአልሜዳ መጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በጥንቃቄ አርመው አሳተሟቸው። በፖርቹጋል ቋንቋ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ ጥራዝ አልሜዳ መጽሐፍ ቅዱስን የመተርጎም ሥራውን ከጀመረ ከ110 ዓመታት ገደማ በኋላ በ1751 ታተመ።

ዘላቂ ቅርስ

አልሜዳ፣ ተራው ሕዝብ እውነትን በራሱ ቋንቋ መረዳት እንዲችል በፖርቹጋል ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ተገንዝቦ ነበር። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብትቃወመውም፣ የሥራ ባልደረቦቹ ለሥራው ግዴለሽ ቢሆኑም፣ ማለቂያ የሌለው የሚመስል የእርማት ችግር ቢያጋጥመውም እንዲሁም ጤንነቱ እያሽቆለቆለ ቢሄድም ግቡ ላይ ለመድረስ ሳይታክት በሕይወቱ ሙሉ ጥረት አድርጓል። እንዲህ ያለ ጽናት በማሳየቱም ተክሷል።

አልሜዳ ይሰብክባቸው ከነበሩት የፖርቹጋል ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች አብዛኞቹ ቁጥራቸው ከማነሱም በላይ አንዳንዶቹ ጠፍተዋል፤ የአልሜዳ መጽሐፍ ቅዱስ ግን እስካሁን ድረስ አለ። በ19ኛው መቶ ዘመን የብሪታንያና የባሕር ማዶ አገራት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር እንዲሁም የአሜሪካ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የአልሜዳ መጽሐፍ ቅዱስ እትሞችን በፖርቹጋልና በብራዚል የባሕር ጠረፍ ላይ በሚገኙ ከተሞች አሰራጭተዋል። በዚህም የተነሳ የፖርቹጋል ቋንቋ በሚናገሩ አገራት ውስጥ በጣም ከታወቁትና በስፋት ከተሰራጩት መካከል አልሜዳ ከተረጎመው የመጀመሪያው ቅጂ የተወሰዱ መጽሐፍ ቅዱሶች ይገኙበታል።

እንደ አልሜዳ ያሉ የቀድሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ለብዙዎች ባለውለታ እንደሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ከሁሉም በላይ ምስጋና የሚገባው ለፍጥረታቱ ሐሳቡን የገለጸው እንዲሁም “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ” የሚፈልገው ይሖዋ አምላክ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ቃሉን እስካሁን ጠብቆ ያቆየልንና ለእኛ ጥቅም ሲል የሰጠን እሱ ነው። በሰማይ ከሚኖረው አባታችን ያገኘነውን ይህንን “እጅግ ውድ የሆነ ሀብት” ምንጊዜም ከፍ አድርገን በመመልከት በትጋት እናጥናው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ከ16ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ በኋላ ባሉት ዓመታት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ ኢንዴክስ ኦቭ ፎርቢድን ቡክስ (የተከለከሉ መጻሕፍት ማውጫ) የተባለ ጽሑፍ በማሳተም በሕዝቡ ቋንቋ በተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶች መጠቀምን አጥብቃ ከለከለች። ይህም “በቀጣዮቹ 200 ዓመታት ካቶሊኮች ምንም ዓይነት የትርጉም ሥራ እንዳያከናውኑ አድርጓል” በማለት ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ገልጿል።

b የአልሜዳ መጽሐፍ ቅዱስ የቀድሞ እትሞች፣ ፓድሬ (አባ) አልሜዳ ብለው ይጠሩት ስለነበር አንዳንዶች የካቶሊክ ቄስ ሆኖ አገልግሏል የሚል እምነት አላቸው። ይሁን እንጂ የአልሜዳን መጽሐፍ ቅዱስ ያዘጋጁት የደች ሰዎች እንዲህ ያደረጉት በስህተት ነበር፤ ቃሉ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታይ ለሆነ ፓስተር ወይም አገልጋይ የሚሠራበት መጠሪያ መስሏቸው ነበር።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መለኮታዊው ስም

አልሜዳ፣ ቴትራግራማተን በመባል የሚታወቁትን የዕብራይስጥ ፊደላት ሲተረጉም መለኮታዊውን ስም መጠቀሙ ታማኝ ተርጓሚ እንደሆነ ያሳያል።

[ምንጭ]

Cortesia da Biblioteca da Igreja de Santa Catarina (Igreja dos Paulistas)

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የአትላንቲክ ውቅያኖስ

ፖርቹጋል

ሊዝበን

ቶሪ ዴ ታቫሬዝ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባታቪያ በ17ኛው መቶ ዘመን

[ምንጭ]

From Oud en Nieuw Oost-Indiën, Franciscus Valentijn, 1724

[በገጽ 18,19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1681 የታተመው የመጀመሪያው በፖርቹጋል ቋንቋ የተዘጋጀ አዲስ ኪዳን የፊት ገጽ

[ምንጭ]

Courtesy Biblioteca Nacional, Portugal