በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

አንዲት ክርስቲያን ሴት ከመንፈሳዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ራሷን መሸፈን የሚኖርባት መቼ ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ “ራስዋን ሳትሸፍን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ማንኛዋም ሴት የእርስዋን ራስ ታዋርዳለች” ሲል ጽፏል። ለምን? “የሴትም ራስ ወንድ ነው” በሚለው በራስነት መሠረታዊ ሥርዓት የተነሳ ነው። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መጸለይ ወይም ማስተማር የወንድ ኃላፊነት ነው። በመሆኑም አንዲት ክርስቲያን ሴት በባልዋ ወይም በአንድ የተጠመቀ ወንድ መፈጸም ያለባቸውን ከአምልኮ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ስታከናውን ራስዋን መሸፈን ይኖርባታል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 11:3-10 አ.መ.ት 

አንዲት ክርስቲያን ሴት ራሷን እንድትሸፍን የሚያስገድድ ሁኔታ በትዳሯ ውስጥ ሊያጋጥማት ይችላል። ለምሳሌ ያህል ቤተሰቡ አንድ ላይ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያጠናበት ወይም ምግብ በሚመገብበት ጊዜ ማስተማር ወይም ቤተሰቡን ወክሎ ጸሎት ማቅረብ የሚኖርበት ባልየው ነው። ይሁን እንጂ ባልየው የማያምን ከሆነ ሚስትየዋ ይህን ኃላፊነት ልታከናውን ትችላለች። ስለዚህ ለራስዋና ለሌሎች ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ስትጸልይ ወይም ባልዋ ባለበት ልጆቿን መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና ራሷን መሸፈኗ ተገቢ ነው። ባልዋ በማይኖርበት ጊዜ ግን ራስዋን መሸፈን አያስፈልጋትም፤ ምክንያቱም አምላክ ልጆቹን የማስተማር ኃላፊነት የሰጠው ለእርሷም ጭምር ነው።​—⁠ምሳሌ 1:8፤ 6:20

በቤተሰቡ ውስጥ ይሖዋ አምላክን የሚያገለግል ራሱን ወስኖ የተጠመቀ አንድ ልጅ ቢኖርስ? ልጁ የክርስቲያን ጉባኤ አባል እንደመሆኑ ትምህርት ማግኘት የሚኖርበት ወንዶች ከሆኑት የጉባኤው አባላት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:12) አባቱ የሚያምን ከሆነ ልጁን ሊያስተምረው የሚገባው እሱ ነው። ይሁን እንጂ አባትየው በማይኖርበት ጊዜ የተጠመቀውን ልጅ ጨምሮ ልጆቿን መጽሐፍ ቅዱስ ስታስተምር ራስዋን መሸፈን ይኖርባታል። የተጠመቀው ልጅ በእንዲህ ዓይነቱ ጥናት ላይ ወይም በምግብ ሰዓት እንዲጸልይ የማድረጉ ውሳኔ ለእርስዋ የተተወ ነው። ብቃት እንደሚጎድለው ከተሰማት ራስዋ ለመጸለይ ልትመርጥ ትችላለች። በዚህ ወቅት የምትጸልይ ከሆነ ራሷን መሸፈን አለባት።

ክርስቲያን ሴቶች በአንዳንድ የጉባኤ እንቅስቃሴዎች ሲካፈሉ ራሳቸውን መሸፈን ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል በሳምንቱ ቀናት በሚደረገው የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ላይ እህቶች ብቻ ሊገኙና በመካከላቸው የተጠመቀ ወንድ ላይኖር ይችላል። በጉባኤ ስብሰባ ላይም ቢሆን የተጠመቀ ወንድ የማይኖርባቸው አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ጉባኤው ባዘጋጀው አንድ ስብሰባ ላይ ወይም በመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ላይ አብዛኛውን ጊዜ በወንዶች የሚከናወኑ ኃላፊነቶችን አንዲት እህት እንድታከናውን በሚደረግበት ጊዜ ራስዋን መሸፈን ይኖርባታል።

አንዲት ክርስቲያን ሴት በቃል ወይም በምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮችን ስታስተረጉም ወይም በጉባኤ ስብሰባ ላይ እየተጠና ካለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ላይ በሕዝብ ፊት ስታነብብ ራስዋን መሸፈን ይኖርባታል? አይኖርባትም። እህቶች እነዚህን ኃላፊነቶች ሲያከናውኑ ስብሰባውን እየመሩ ወይም እያስተማሩ አይደለም። በተመሳሳይም ሠርቶ ማሳያዎችን የሚያቀርቡ፣ ተሞክሮዎችን የሚናገሩ፣ ወይም በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የተማሪ ክፍል የሚያቀርቡ እህቶች ራሳቸውን እንዲሸፍኑ አይጠበቅባቸውም።

በጉባኤው ውስጥ የማስተማሩ ሥራ መከናወን ያለበት በተጠመቁ ወንዶች ቢሆንም ከጉባኤ ውጭ በሚደረገው በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ ወንዶችም ሴቶችም የመካፈል ኃላፊነት አለባቸው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ስለዚህ አንዲት ክርስቲያን ሴት የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር ወንድ ባለበት ለሌሎች ሰዎች ስለ አምላክ ቃል ስትመሰክር ራስዋን መሸፈን አያስፈልጋትም።

ሆኖም ጊዜ ተይዞለት በቋሚነት በሚደረግ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ አንድ ራሱን ወስኖ የተጠመቀ ወንድ ሲገኝ ግን ሁኔታው የተለየ ይሆናል። ይህ በአስጠኚው የሚመራ ቀደም ሲል ፕሮግራም የተያዘለት የትምህርት ክፍለ ጊዜ ነው። በዚህ መሠረት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የጉባኤ ስብሰባ ክፍል እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። አንድ የተጠመቀ ምሥክር ባለበት አንዲት እህት እንዲህ ያለ ጥናት የምትመራ ከሆነ ራስዋን መሸፈኗ ተገቢ ነው። ጸሎት ማቅረብ ያለበት ግን ራሱን ለአምላክ የወሰነው ወንድም ነው። የመናገር ችሎታ ማጣትን የመሰሉ በአንዳንድ ያልተለመዱ ምክንያቶች የተነሳ መናገር የማይችል እስካልሆነ ድረስ ራሱን የወሰነ ወንድም ባለበት አንዲት እህት መጸለይ አይኖርባትም።

አንዲት ክርስቲያን እህት መጽሐፍ ቅዱስን ስታስጠና አንድ ያልተጠመቀ የመንግሥቱ አስፋፊ አብሯት የሚገኝበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። ከፈለገች አስፋፊው ጥናቱን እንዲመራ ልትጋብዘው ትችላለች። ይሁን እንጂ አስፋፊው የተጠመቀችውን እህት ወክሎ ለይሖዋ ጸሎት ማቅረብ ስለማይችል በጥናቱ ላይ እሷ መጸለይዋ ተገቢ ነው። በዚህ ወቅት ጥናቱን ስትመራም ሆነ ስትጸልይ ራሷን መሸፈን አለባት። አስፋፊው ገና ያልተጠመቀ ቢሆንም እንኳን በስብከቱ ሥራ ላይ በሚያደርገው ተሳትፎ የተነሳ በውጭ ያሉ ሰዎች የሚመለከቱት የጉባኤው አባል እንደሆነ አድርገው ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ “በመላእክትም ምክንያት፣ ሴት በሥልጣን ሥር መሆንዋን የሚያሳይ ምልክት በራስዋ ላይ ታድርግ” [አ.መ.ት ] ሲል ጽፏል። አዎን፣ ክርስቲያን ሴቶች ለዘላለም ለይሖዋ ለሚገዙት በሚልዮን ለሚቆጠሩ ታማኝ መላእክት መልካም ምሳሌዎች የመሆን መብት አግኝተዋል። አምላካዊ የሆኑ ሴቶች አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ሁሉ ራሳቸውን መሸፈናቸው ምንኛ ተገቢ ነው!

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራስን መሸፈን የራስነት ሥልጣን ማክበርን የሚያሳይ ምልክት ነው