በመካከለኛው ምሥራቅ መንፈሳዊ ብርሃን ፈነጠቀ
የሕይወት ታሪክ
በመካከለኛው ምሥራቅ መንፈሳዊ ብርሃን ፈነጠቀ
ናጂብ ሳሌም እንደተናገረው
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ በመካከለኛው ምሥራቅ ማብራት የጀመረው የአምላክ ቃል ብርሃን እስከ ምድር ዳር ደርሶአል። በ20ኛው መቶ ዘመንም ይህ ብርሃን ተመልሶ በዚሁ የምድር ክፍል ማብራት ጀምሮአል። እስቲ ይህ እንዴት እንደሆነ ልንገራችሁ።
አሚየን በተባለ ሰሜናዊ ሊባኖስ ውስጥ በሚገኝ ትንሽ ከተማ በ1913 ተወለድኩ። በተከታዩ ዓመት አንደኛው የዓለም ጦርነት ፈንድቶ ስለነበር 1913 በዓለም ዙሪያ አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነበት የመጨረሻ ዓመት ነበር። ጦርነቱ በ1918 ሲያበቃ የመካከለኛው ምሥራቅ እንቁ በመባል ትታወቅ የነበረችው ሊባኖስ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ገጥሟት ነበር።
በ1920 የፖስታ አገልግሎት እንደገና በሊባኖስ ሲጀምር በውጭ አገር ከሚኖሩ ሊባኖሳውያን ደብዳቤዎች ይደርሱን ጀመር። ከእነዚህ ውስጥ አብዱላ እና ጆርጅ ጋንቶስ የተባሉ አጎቶቼ ይገኙበታል። እነርሱም ለአያቴ ማለትም ለአባታቸው ለሃቢብ ጋንቶስ ደብዳቤ በመጻፍ ስለ አምላክ መንግሥት ይነግሩት ነበር። (ማቴዎስ 24:14) አያቴ ልጆቹ የጻፉለትን ለከተማው ሰዎች መናገሩ ብቻ የፌዝ ዒላማ አደረገው። ሰዎቹ የሀቢብ ልጆች አባታቸው ቤቱን ሸጦ አህያ እንዲገዛና ስብከት እንዲጀምር እያበረታቱት ነው የሚል ወሬ በመላ ከተማዋ አዳረሱ።
መጀመሪያ የፈነጠቀ ብርሃን
በተከታዩ ዓመት ማለትም በ1921 ብሩክሊን ኒው ዮርክ ዩ ኤስ ኤ የሚኖረው ሚሼል አቡድ ለጉብኝት ወደ ሊባኖስ ትሪፖሊ መጣ። በዚያን ጊዜ አቡድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ሆኖ ነበር። በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩት በዚህ ስም ነበር። አብዛኞቹ የወንድም አቡድ ወዳጆችና ዘመዶች ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ ባይሰጡም ሁለት ታዋቂ ግለሰቦች ማለትም
ፕሮፌሰር ኢብራሂም አታያ እና የጥርስ ሐኪም የሆነው ሃና ሻማስ ምላሽ ሰጥተዋል። እንዲያውም ዶክተር ሻማስ መኖሪያ ቤቱንና ክሊኒኩን ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ክፍት አድርጎ ነበር።ወንድም አቡድና ወንድም ሻማስ እኔ የምኖርበትን አሚየንን ሲጎበኙ ገና ትንሽ ልጅ ነበርኩ። ጉብኝታቸው በጥልቅ ስለነካኝ ወንድም አቡድ ወደ አገልግሎት ሲወጣ ከእርሱ ጋር አብሬ መውጣት ጀመርኩ። ወንድም አቡድ በ1963 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ለ40 ዓመታት የማንነጣጠል የአገልግሎት ጓደኛሞች ሆነናል።
ከ1922 እስከ 1925 ባሉት ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ የእውነት ብርሃን ሰሜናዊ ሊባኖስ በሚገኙ ብዙ መንደሮች በሰፊው ተሰራጭቶ ነበር። ከ20 እስከ 30 የሚያክሉ ሰዎች በአሚዩን እንደሚገኘው ቤታችን ባሉ የግለሰብ ቤቶች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ለማድረግ ይሰበሰቡ ነበር። ቀሳውስት ስብሰባዎቻችንን ለመረበሽ በማሰብ የቆርቆሮ ጣሳዎችን የሚደበድቡና የሚጮኹ ልጆች ይልኩ ስለነበር አንዳንድ ጊዜ ስብሰባዎቻችንን በጥድ ጫካ ውስጥ ማድረግ አስፈልጎን ነበር።
ወጣት በነበርኩበት ወቅት ለአገልግሎቱና በእያንዳንዱ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ለመገኘት የነበረኝ ቅንዓት ጢሞቴዎስ የሚል ቅፅል ስም አትርፎልኛል። የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ “እነዚያ ስብሰባዎች” ብሎ በሚጠራቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘቴን እንዳቆም አስጠነቀቀኝ። ይህንን እንደማላደርግ ስገልጽ ከትምህርት ቤት ተባረርኩ።
መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገርላቸው አካባቢዎች መመሥከር
በ1933 ከተጠመቅሁ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክሮች አቅኚነት ብለው በሚጠሩት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመርኩ። በቁጥር ጥቂት ብንሆንም ስብከታችንን እናከናውን የነበረው ሰሜናዊ ሊባኖስ በሚገኙ በአብዛኞቹ መንደሮች ብቻ ሳይሆን በቤሩትና ከቤሩት ወጣ ብለው በሚገኙ ቦታዎች እንዲሁም እስከ ደቡባዊ ሊባኖስ በሚደርሱት ክልሎች ውስጥ ነበር። በእነዚያ የመጀመሪያ ዓመታት እንደ ኢየሱስ ክርስቶስና እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ተከታዮቹ ብዙውን ጊዜ የምንጓዘው በእግር ወይም በአህያ ነበር።
በ1936 ለብዙ ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ የኖረ ዩሴፍ ራሃል የተባለ አንድ ሊባኖሳዊ ምሥክር ለጉብኝት ወደ ሊባኖስ መጥቶ ነበር። ራሃል ያመጣውን የድምፅ መሣሪያና ሁለት የሸክላ ማጫወቻ በ1931 በተሠራ ፎርድ መኪና ላይ ጭነን የመንግሥቱን መልእክት ራቅ ወዳሉት የሊባኖስና የሶሪያ ክልሎች ለማድረስ ተንቀሳቀስን። የድምፅ ማጉያው እስከ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ይሰማ ስለነበር ሰዎች ከሰማይ የመጣ ያሉትን ይህንን ድምፅ ለመስማት በቤቶቻቸው ጣሪያ ላይ ወጥተው ነበር። በመስክ ያሉት ደግሞ ሥራቸውን ጥለው ለማዳመጥ መጥተዋል።
በ1937 ክረምት ላይ ከዩሴፍ ራሃል ጋር ካደረግናቸው የመጨረሻ ጉዞዎች መካከል ወደ አሌፖ ሶርያ ያደረግነው ይገኝበታል። ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከመመለሱ በፊት ወደ ፍልስጤም ተጉዘናል። እዚያም ሃይፋና ኢየሩሳሌም የተባሉትን ከተሞች ጨምሮ በአገሪቱ የሚገኙትን የተለያዩ መንደሮች ጎብኝተናል። ካነጋገርናቸው ሰዎች መካከል አንዱ ቀድሞ ደብዳቤ እንጻጻፍ የነበረው ኢብራሂም ሺሃዲ ነው። ኢብራሂም የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቱን አዳብሮ ስለነበር እኛ ለጉብኝት በሄድንበት ወቅት አብሮን ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ጀመረ።—ሥራ 20:20
ቀደም ሲል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በደብዳቤ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስ ያጠና ከነበረው ቀናተኛ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ፕሮፌሰር ካሊል ኮብሮሲ ጋር ለመገናኘት ጓጉቼ ነበር። በሊባኖስ ያሉትን ምሥክሮች አድራሻ እንዴት ሊያገኝ ቻለ? ሃይፋ በሚገኝ አንድ የእቃ መሸጫ መደብር ውስጥ የሚሸጠው ሰው ካሃሊ የገዛቸውን አንዳንድ እቃዎች የይሖዋ ምሥክሮች ከሚያዘጋጁአቸው ጽሑፎች ላይ በተገነጠለ ወረቀት ጠቅልሎ ይሰጠዋል። ይህ ወረቀት የእኛን አድራሻ ይዞ ነበር። አንድ ላይ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍን ሲሆን በኋላም በ1939 ትሪፖሊ መጥቶ ተጠምቋል።
በ1937 ደግሞ ፔትሮስ ላጋኮስና ባለቤቱ ትሪፖሊ
ደረሱ። በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ሦስታችን ከቤት ወደ ቤት በማንኳኳት የመንግሥቱን መልእክት በአብዛኛው የሊባኖስና የሶርያ ክልሎች አዳርሰናል። ወንድም ላጋኮስ በ1943 ሲሞት ምሥክሮቹ መንፈሳዊውን ብርሃን ወደ አብዛኞቹ የሊባኖስ የሶርያና የፍልስጤም ከተሞችና መንደሮች ይዘው ሄደው ነበር። አንዳንድ ጊዜ ወደ 30 ሆነን ራቅ ወዳሉ ክልሎች ለመሄድ ከሌሊቱ 9:00 ሰዓት እንነሳና በመኪና ወይም በአውቶቡስ እንጓዝ ነበር።በ1940ዎቹ ውስጥ ኢብራሂም አታያ መጠበቂያ ግንብን ወደ አረብኛ ቋንቋ ተረጎመ። ከዚያ በኋላ አራት በእጅ የተጻፉ ቅጂዎች አዘጋጅና ፍልስጤም፣ ሶርያና ግብጽ ለሚገኙ ምሥክሮች እልክላቸው ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በስብከቱ ሥራችን ላይ የተነሳው ተቃውሞ እጅግ ከፍተኛ ነበር። ሆኖም በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አፍቃሪዎች ጋር ግንኙነት ማድረጋችንን ቀጥለን ነበር። እኔ የከተሞቹንና በአካባቢው ያሉትን መንደሮች ካርታ ከሳልኩ በኋላ የመንግሥቱን ምሥራች ወደነዚህ ቦታዎች የማድረስ ግብ አወጣን።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ገና ውድመት እያስከተለ በነበረበት በ1944 የአቅኚነት አገልግሎት አጋሬ የሆነው የሚሼል አቡድ ልጅ የሆነችውን ኢቭሊንን አገባሁ። ብዙም ሳይቆይ አንዲት ሴትና ሁለት ወንዶች ልጆች ወለድን።
ከሚስዮናውያን ጋር መሥራት
ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የመጀመሪያዎቹ የጊልያድ ምሩቃን ሊባኖስ ደረሱ። በዚህም ምክንያት በሊባኖስ የመጀመሪያው ጉባኤ የተቋቋመ ሲሆን እኔ ደግሞ የቡድን አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ። ከዚያም በ1947 ናታን ኤች ኖር እና ጸሐፊው ሚልተን ጂ ሄንሼል ሊባኖስን የጎበኙ ሲሆን ጉብኝቱ ወንድሞችን በከፍተኛ ሁኔታ አበረታትቷል። ብዙም ሳይቆይ ተጨማሪ ሚስዮናውያን የተመደቡልን ሲሆን ሚስዮናውያኑ አገልግሎታችንን በማደራጀትና የጉባኤ ስብሰባዎችን በመምራት ረገድ ከፍተኛ እርዳታ አበርክተውልናል።
ሶርያ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ ራቅ ያለ ቦታ ስንጓዝ ከአንድ የአካባቢው ጳጳስ ተቃውሞ ገጥሞን ነበር። ጽዮናዊ ጽሑፎች ያሰራጫሉ በማለት ክስ መሠረተብን። የሚያስገርመው ከ1948 ቀደም ብሎ አብዛኞቹ ቀሳውስት ያወጡልን ስም “ኮሙኒስት” ናቸው የሚል ነበር። በዚህ ጊዜ አሥረው ለሁለት ሰዓታት ጥያቄ የጠየቁን ሲሆን አጋጣሚው ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት አስችሎናል።
በመጨረሻም ክሱን ያዳመጡት ዳኛ እንዲህ በማለት ተናገሩ:- “ጳጳሱ በእናንተ ላይ ክስ በመመስረቱ ባወግዘውም በዚህ አጋጣሚ ከእናንተ ጋር ስላስተዋወቀኝ ላመሰግነው እፈልጋለሁ።” ከዚያም ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ ጠየቁን።
ከአሥር ዓመታት በኋላ ወደ ቤሩት በአውቶቡስ ስጓዝ አጠገቤ ተቀምጦ ከነበረው የእርሻ መሃንዲስ ጋር መነጋገር ጀመርኩ። ስለ እምነታችን ስነግረው ለጥቂት ደቂቃዎች ካዳመጠ በኋላ ይህንን የሚመስል ነገር ሶርያ ካለ አንድ ጓደኛው እንደሰማ ገለጸልኝ። ይህ ጓደኛው ማን ነበር? ከአሥር ዓመታት በፊት ጉዳያችንን ያዳመጡት ዳኛ ነበሩ!
በ1950ዎቹ ኢራቅ የሚገኙትን ምሥክሮች የጎበኘሁ ሲሆን ከእነርሱ ጋር ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ተካፍያለሁ። በተጨማሪም ለብዙ ጊዜያት ወደ ዮርዳኖስና ወደ ዌስት ባንክ ተጉዤአለሁ። በ1951 ወደ ቤተ ልሔም ከተጓዙት አራት ምሥክሮች መካከል አንዱ ነበርኩ። እዚያም ሆነን የጌታን እራት አክብረናል። በዓሉ ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ በቦታው የተገኙት በሙሉ አውቶቡስ ተሳፍረው ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ የሄዱ ሲሆን ከመካከላቸው 22 የሚያክሉት ለይሖዋ ያደረጉትን ውሳኔ በውኃ ጥምቀት አሳይተዋል። በዚያ አካባቢ ተቃውሞ ሲያጋጥመን ሁልጊዜ እንዲህ እንላቸው ነበር:- “የመጣነው የዚሁ አገር ተወላጅ የሆነ ሰው የመላዋ ምድር ገዥ እንደሚሆን ልንነግራችሁ ነው! ታዲያ ለምን ትበሳጫላችሁ? እንዲያውም ደስ ሊላችሁ ይገባል!”
በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር መስበክ
በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ ሰዎች በጥቅሉ ሲታይ ቅን ልብ ያላቸው፣ ትሑቶችና እንግዳ ተቀባዮች ናቸው። ብዙዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች በጉጉት ያዳምጣሉ። በእርግጥም “የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ [ከሕዝቡ] ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ከማወቅ ራእይ 21:3, 4
የበለጠ አእምሮን የሚያነቃቃ ምን ነገር ይኖራል?—ሥራችንን የሚቃወሙ አብዛኞቹ ሰዎች የያዝነውን መልእክትና የሥራችንን ምንነት እንደማይገነዘቡ ተረድቻለሁ። የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ሰዎች እኛን በተሳሳተ መንገድ እንዲረዱን ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም! በዚህም ምክንያት በሊባኖስ የሚገኙት ምሥክሮች ከ1975 ጀምሮ ለ15 ዓመታት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁመዋል።
በአንድ ወቅት ቀናተኛ የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚ ለነበረ አንድ ቤተሰብ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እመራ ነበር። ይህ ቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በመማር ረገድ ያሳየው ጥሩ እድገት ቀሳውስቱን በማስቆጣቱ አንድ ምሽት ላይ አንድ የአካባቢው ሃይማኖታዊ ቡድን አባላቶቹን በማነሳሳት የቤተሰቡ ሱቅ እንዲወረር አደረገ። በዚህ ወቅት ቢያንስ 10, 000 የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ሸቀጣ ሸቀጥ አቃጥለዋል። በዚያው ምሽት መጥተው እኔንም አፍነው ወሰዱኝ። ሆኖም እውነተኛ ክርስቲያኖች ብትሆኑ ኖሮ እንዲህ ያለውን አረመኔያዊ ድርጊት አትፈጽሙም ነበር ብዬ ለመሪያቸው ስነግረው ወዲያው መኪናውን አቁመው እንዲያወርዱኝ አዘዘ።
በሌላ ጊዜ ደግሞ አራት ወታደሮች አፍነው ወስደውኝ ነበር። ብዙ ካስፈራሩኝ በኋላ ተኩሶ እንደሚገድለኝ ዝቶ የነበረው መሪያቸው ድንገት ሐሳቡን ለውጦ በነፃ ተለቀቅሁ። በአሁኑ ጊዜ ከእነዚህ አራት ሰዎች ውስጥ ሁለቱ በግድያና በስርቆት ወንጀል ተከስሰው እስር ቤት የገቡ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ ተገድለዋል።
ለመመሥከር የሚያስችሉ ሌሎች አጋጣሚዎች
በአብዛኛው ከአንዱ አገር ወደ ሌላው አገር በአውሮፕላን የመብረር አጋጣሚ አግኝቼአለሁ። በአንድ ወቅት ከቤሩት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ስጓዝ ከቀድሞው የሊባኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቻርልስ ሜሌክ ጎን ተቀመጥኩ። ከመጽሐፍ ቅዱስ የማነብለትን እያንዳንዱን ጥቅስ በማድነቅ በጥንቃቄ ካዳመጠ በኋላ ትሪፖሊ ውስጥ ኢብራሂም አታያ የተባለ መምህር እንደነበረው ነገረኝ! ኢብራሂም አታያ እውነትን የሰማው ከአማቴ ነበር። ሚስተር ሜሌክ፣ ኢብራሂም ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት እንዲያድርበት እንደረዳው ተናገረ።
በሌላ በረራ ወቅትም እንዲሁ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፍልስጤም ተወካይ ከሆነ ግለሰብ ጎን ተቀምጬ ስለነበር የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመናገር የሚያስችል አጋጣሚ አገኘሁ። በኋላም ኒው ዮርክ ከሚኖረው የወንድሙ ቤተሰብ ጋር ያስተዋወቀኝ ሲሆን ብዙውን ጊዜም እየሄድኩ እጠይቃቸው ነበር። በአንድ ወቅት ኒው ዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሕንጻ ውስጥ የሚሠራ ዘመዴን ለመጠየቅ ቢሮው ስሄድ ሦስት ሰዓታት የፈጀ ውይይት አደረግን። ይህ አጋጣሚ ስለ አምላክ መንግሥት ለመመስከር አስችሎኛል።
በአሁኑ ጊዜ ዕድሜዬ 88 ዓመት ሲሆን አሁንም የጉባኤ ኃላፊነቶቼን በመወጣት ረገድ ንቁ ተሳትፎ አደርጋለሁ። ባለቤቴ ኢቭሊንም ከጎኔ ሆና ይሖዋን እያገለገለች ነው። ሴቷ ልጃችን ቤሩት በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግል አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ያገባች ሲሆን ሴቷ ልጃቸውም ምሥክር ናት። የመጨረሻው ወንድ ልጃችንና ባለቤቱ ምሥክሮች ሲሆኑ ሴቷ ልጃቸውም እውነት ውስጥ ነች። በትልቁ ልጃችን ልብ ውስጥም ክርስቲያናዊውን እምነት ለመትከል ጥረት አድርገናል። አንድ ቀን ተመልሶ ይህንን እውነት እንደሚይዝ ተስፋ አደርጋለሁ።
በ1933 በመካከለኛው ምሥራቅ የመጀመሪያው አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ። ያለፉትን 68 ዓመታት ይሖዋን በአቅኚነት ከማገልገል የበለጠ በሕይወቴ ምንም የተሻለ ነገር ማድረግ አልችልም ነበር። አሁንም ቢሆን ይሖዋ በሚያቀርበው መንፈሳዊ ብርሃን መጓዜን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርጌአለሁ።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ናጂብ በ1935
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1940 በሊባኖስ ተራሮች ላይ የድምፅ ማጉያ ከተገጠመላት መኪና ጋር
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከላይ ያለው ፎቶግራፍ ከበስተ ግራ ጫፍ ወደ ቀኝ በቅደም ተከተል:- ናጂብ፣ ኢቭሊን፣ ሴት ልጃቸው፣ ወንድም አቡድና የናጂብ ትልቁ ወንድ ልጅ በ1952
ከታች (የፊተኛው መስመር):- ወንድም ሻማስ፣ ኖር፣ አቡድ እና ሄንሼል ትሪፖሊ በሚገኘው በናጂብ ቤት በ1952
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ናጂብና ባለቤቱ ኢቭሊን