በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኢየሱስ ትንሣኤ ጥያቄ ተነስቶበታል

የኢየሱስ ትንሣኤ ጥያቄ ተነስቶበታል

የኢየሱስ ትንሣኤ ጥያቄ ተነስቶበታል

“ኢየሱስ በሕይወት እንደኖረ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ የሆንነውን ያህል . . . አምላክ ከሙታን አስነስቶታል ብለን በእርግጠኝነት መናገር እንደማንችል በግልጽ ልነግራችሁ እችላለሁ።” ይህን የተናገሩት በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ ናቸው።

ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ያለ ጥርጣሬ አልነበረውም። በጥንቷ ቆሮንቶስ ለሚኖሩት ክርስቲያን ባልደረቦቹ በመንፈስ አነሳሽነት በጻፈው በመጀመሪያ ደብዳቤው በምዕራፍ 15 ላይ “እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ:- መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፣ ተቀበረም፣ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ” በማለት ጽፏል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​3, 4

የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ወንጌልን በመላው የግሪክና የሮም ዓለም ማለትም “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ” እንዲሰብኩ የገፋፋቸው በትንሣኤው ላይ የነበራቸው እምነት ነው። (ቆላስይስ 1:​23) እንዲያውም የክርስትና እምነት መሠረት የኢየሱስ ትንሣኤ ነው።

ሆኖም የኢየሱስን ትንሣኤ መጠራጠር የተጀመረው አሁን አይደለም። የኢየሱስ ተከታዮች በእንጨት ላይ ተሰቅሎ የሞተው ይህ ሰው መሲሕ ነው ብለው መናገራቸው በጠቅላላ በአይሁዳውያን ዘንድ የተጠላ ነበር። እንዲሁም ነፍስ አትሞትም የሚል እምነት በነበራቸው በብዙዎቹ የግሪክ ምሁራን ዘንድ ትንሣኤ የሚለው ቃል ራሱ ተቀባይነት አልነበረውም።​—⁠ሥራ 17:​32-34

ዘመናዊ ተጠራጣሪዎች

በቅርብ ዓመታት ክርስቲያን ነን የሚሉ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ምሁራን አሳትመው ባወጧቸው መጻሕፍትና ጽሑፎች ላይ የኢየሱስ ትንሣኤ የፈጠራ ታሪክ እንደሆነ አድርገው ከመግለጻቸውም በላይ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የጦፈ ክርክር እንዲቀሰቀስ በር ከፍተዋል። የተለያዩ ምሁራን “ታሪካዊውን ኢየሱስ” ለማግኘት ባደረጉት ፍለጋ ባዶ መቃብር እንደተገኘ የሚገልጸውና ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ እንደታየ የሚገልጹት የወንጌል ዘገባዎች ፍጹም ፈጠራ እንደሆኑና በሰማይ ሥልጣን ተጎናጽፏል የሚለውን አባባል ለመደገፍ ከሞተ ከብዙ ጊዜ በኋላ የተቀናበሩ ታሪኮች እንደሆኑ ይከራከራሉ።

ለምሳሌ ያህል፣ የአዲስ ኪዳን ፕሮፌሰርና ሁዋት ሪሊ ሃፕንድ ቱ ጂሰስ​—⁠ኤ ሂስቶሪካል አፕሮች ቱ ዘ ሪዘሬክሽን የተባለው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ጀርመናዊው የሃይማኖት ምሁር ገርት ሉድማን የሰጡትን አስተያየት ተመልከት። የኢየሱስ ትንሣኤ “የዓለም ሳይንሳዊ አመለካከት ያለው” ማንኛውም ሰው ፈጽሞ ሊቀበለው የማይችል “መሠረተ ቢስ እምነት ነው” በማለት ተከራክረዋል።

ፕሮፌሰር ሉድማን ትንሣኤ አግኝቶ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ ተገለጠው ክርስቶስ ሲናገሩ ጴጥሮስ በደረሰበት ከፍተኛ ሐዘንና ኢየሱስን በመካዱ ምክንያት ተሰምቶት ከነበረው የጥፋተኝነት ስሜት የመነጨ ራእይ ነው የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። እንዲሁም እንደ ሉድማን አባባል በአንድ ወቅት ከ500 ለሚበልጡ ሰዎች የታየው ኢየሱስ “የሕዝብ ሲቃ” የፈጠረው እንጂ ራሱ ኢየሱስ አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 15:​5, 6) በአጭሩ በርካታ የሃይማኖት ምሁራን ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በደቀ መዛሙርቱ ውስጥ የመንፈስ ጥንካሬ እንዲሰርጽና የሚስዮናዊነት ቅንዓት እንዲቀጣጠል ያደረጉ በምናብ የተፈጠሩ ክስተቶች ናቸው በማለት ያስቀምጧቸዋል።

እርግጥ ነው፣ ብዙዎች ስለ ምሁራን እሰጥ አገባ ብዙም ደንታ የላቸውም። ይሁን እንጂ ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ የሚሰጠው ማብራሪያ የሁላችንንም ትኩረት ሊስብ የሚገባው ነው። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ ከሞት ካልተነሳ ክርስትና የተመሠረተበት መሠረት ሃሰት ነው ማለት ነው። በሌላው በኩል ደግሞ የኢየሱስ ትንሣኤ በሃቅ ላይ የተመሠረተ እውነተኛ ታሪክ ከሆነ ክርስትና የተመሠረተው በእውነተኛ መሠረት ላይ ነው ማለት ነው። ይህ ደግም ክርስቶስ የተናገራቸውን ብቻ ሳይሆን የገባቸውንም ተስፋዎች ትክክለኛነት ያረጋግጣል። ከዚህም በላይ ትንሣኤ እውን ከሆነ ሞት ማንም የማይደፍረው ድል አድራጊ መሆኑ ቀርቶ ድል ሊደረግ የሚችል ጠላት ይሆናል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​55

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

From the Self-Pronouncing Edition of the Holy Bible, containing the King James and the Revised versions