በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሥነ ምግባር እያዘቀጠ ሄዷል

ሥነ ምግባር እያዘቀጠ ሄዷል

ሥነ ምግባር እያዘቀጠ ሄዷል

“እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ ደርሶ አያውቅም” ሲሉ የቀድሞው የጀርመን ቻንስለር ሔልሙት ሽሚት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በቅርቡ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት የፈጸሟቸውንና የጋዜጦች ርዕሰ ዜና የሆኑትን ዓይን ያወጡ የእምነት ማጉደል ወንጀሎች በተመለከተ የተሰማቸውን ሐዘን መግለጻቸው ነበር። “በስስት ምክንያት የሥነ ምግባር ደንቦች ጠፍተዋል።”

ብዙዎች ከእርሳቸው አባባል ጋር ይስማማሉ። የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በጥብቅ የተመሠረቱና በሰፊው ተቀባይነት በማግኘት ለረዥም ጊዜ ትክክልና ስህተት የሆነውን ለመለየት እንደ መመሪያ ተደርገው ይታዩ የነበሩ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ዛሬ ወደ ጎን ገሸሽ ተደርገዋል። ሁኔታው በክርስትና ስም በሚታወቁት አገሮች እንኳ ሳይቀር ተመሳሳይ ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ምግባር ጠቃሚ ነውን?

በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ የተመሠረተው ሥነ ምግባር ሐቀኝነትንና የአቋም ጽናትን ይጨምራል። ይሁን እንጂ ማታለል፣ ሙስናና ማጭበርበር በእጅጉ ተስፋፍተዋል። አንዳንድ የወንጀል መርማሪዎች “በፖሊሶች የተያዙትን አደገኛ ዕፆች ለወንጀለኞቹ ለመመለስ ወይም ማስረጃዎቹን ለማጥፋት በአንድ ጊዜ ብቻ እስከ 100, 000 የእንግሊዝ ፓውንድ ይቀበላሉ ተብሎ እንደሚታሰብ” የለንደኑ ዘ ታይምስ ዘግቧል። በኦስትሪያ ከኢንሹራንስ ክፍያዎች ጋር በተያያዘ የሚፈጸመው ማጭበርበር በጣም የተለመደ እንደሆነ ይነገራል። በቅርቡ

“በጀርመን ሳይንስ ውስጥ አንድ በጣም አሳፋሪ የማጭበርበር ወንጀል” መፈጸሙን ተመራማሪዎች ሲደርሱበት የጀርመን የሳይንስ ማኅበረሰብ እጅግ ተደናግጦ ነበር። ፕሮፌሰርና “ከጀርመን ዕውቅ የሥነ ባሕርይ ተመራማሪዎች መካከል የሆኑ” አንድ ሰው ከፍተኛ መጠን ያላቸው የሐሰት ወይም የፈጠራ ሥራዎችን በማቅረባቸው ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ምግባር ዘላቂ ጥምረት እንዲሆን በታሰበው በትዳር ውስጥ ታማኝ መሆንንም ይጨምራል። ይሁን እንጂ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ባልና ሚስቶች በፍቺ ይለያያሉ። “‘ወግ አጥባቂ’ በሆነችው በስዊዘርላንድ እንኳ ሳይቀር ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ጋብቻዎች በመፍረስ ላይ ናቸው” በማለት ክራይስት ኢን ዳ ጌጋገንቫርት (የዘመኑ ክርስቲያን) የተባለው የካቶሊክ ጋዜጣ ሪፖርት አድርጓል። ኔዘርላንድ ውስጥ ከሚመሠረቱት ትዳሮች መካከል 33 በመቶ የሚሆኑት በፍቺ ያከትማሉ። ጀርመን ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የታዩትን ማህበራዊ ለውጦች ያስተዋሉ አንዲት ሴት ያሳሰባቸውን ጉዳይ አስመልክተው እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “በአሁኑ ጊዜ ትዳር ኋላቀርነትና ጊዜ ያለፈበት ነገር እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። ሰዎች በቀሪ የሕይወት ዘመናቸው ሁሉ አብሯቸው የሚኖር ሰው ማግባት አቁመዋል።”

በሌላው በኩል ደግሞ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምራቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አስተማማኝ እንደሆኑና በዚህ በእኛ ዘመናዊ ዓለም ውስጥም ጠቃሚ እንደሆኑ ተገንዝበዋል። ነዋሪነታቸው በስዊዝ ጀርመን ጠረፍ ላይ የሆነ አንድ ባልና ሚስት ከመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ደንቦች ጋር ተስማምተው መኖራቸው ደስተኞች እንዳደረጋቸው ተገንዝበዋል። እነርሱ እስከሚያውቁት ድረስ “ለሁሉም የሕይወት ዘርፎች የሚጠቅም አንድ ብቸኛ መመሪያ አለ። እርሱም መጽሐፍ ቅዱስ ነው።”

አንተስ ምን ይመስልሃል? መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ መመሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል? መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥነ ምግባር በዛሬው ጊዜ ተግባራዊ መሆን ይችላል?