በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተሳካላቸው ቤተሰቦች

የተሳካላቸው ቤተሰቦች

የተሳካላቸው ቤተሰቦች

አሁን ደባሎች አይደለንም

ፊሊፕ ሁለተኛ ሚስቱን ከማግባቱ በፊት ልጁ ኤሊስ የቤቱን ሥራዎች በሙሉ እንደ እናት ሆና ታከናውን ነበር። ፊሊፕ ሉዊዝን ካገባ በኋላ የ20 ዓመቷ ኤሊስና የእንጀራ እናቷ ጥሩ ግንኙነት ይኖራቸው ይሆን?

ሉዊዝ፦ መጀመሪያ ላይ መግባባት በጣም ከብዶን ነበር። እኔ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ስለምወድ የቤቱ እመቤት መሆኔ እንዲታወቅልኝ ፈልጌ ነበር።

ኤሊስ፦ ሉዊዝ ቤቱን እንደ አዲስ ያደራጀችው ሲሆን ብዙ ዕቃዎቻችንን አውጥታ ጥላብናለች። አንድ ቀን፣ ዕቃ ሳስተካክል አንዳንዶቹን ዕቃዎች ሉዊዝ የት እንደምታስቀምጣቸው ስላላወቅሁ አለቦታቸው አስቀመጥኳቸው። ይህ ደግሞ ሉዊዝን ስላበሳጫት ኃይለ ቃል ተነጋገርን፤ በዚህም የተነሳ ለአንድ ሳምንት አኮረፍኳት።

ሉዊዝ፦ እንዲያውም በአንድ ወቅት ኤሊስን “ከዚህ በኋላ ምን ማድረግ እንደምንችል ባላውቅም እኔ ግን በዚህ ሁኔታ መኖር አልችልም” አልኳት። አመሻሹ ላይ መጥታ ይቅርታ ጠየቀችኝ። እኔም እቅፍ አደረግኋት፤ ከዚያም ተላቀስን።

ኤሊስ፦ ሉዊዝ ግድግዳው ላይ ተሰቅለው የነበሩ አንዳንድ ፎቶግራፎቼን አላነሳቻቸውም፤ አባቴም እኔ ያስቀመጥኳቸውን የሳሎን መብራቶች እዚያው ተዋቸው። እነዚህን ነገሮች በነበሩበት ቦታ መተዋቸው ትንሽ ነገር ቢመስልም ለእኔ ግን አሁንም ቤቴ እንደሆነ እንዲሰማኝ አድርጓል። በተጨማሪም ትንሹ ወንድሜ ከእኛ ጋር በሚሆንበት ጊዜ ሉዊዝ ለምታደርግለት እንክብካቤ አመስጋኝ ነኝ። ሉዊዝና አባቴ ከተጋቡ ሁለት ዓመት ያለፈ ሲሆን አሁን የቤተሰባችን አባል እንደሆነች አድርጌ ማሰብ ጀምሬያለሁ።

ሉዊዝ፦ አሁን እኔና ኤሊስ ደባሎች ሳንሆን ጥሩ ጓደኛሞች እንደሆንን ይሰማኛል።

‘አንድነት ይበልጥ አስፈላጊ ነው’

አንቶንና ማሬሊዝ ከስድስት ዓመታት በፊት ሲጋቡ እያንዳንዳቸው ሦስት ልጆች ነበሯቸው።

አንቶን፦ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን፣ ከከተማ ወጣ ብሎ እንደ መንሸራሸር ባሉ እንቅስቃሴዎች የምንካፈል ሲሆን ከእያንዳንዱ ልጅ ጋር በግለሰብ ደረጃ ጊዜ እናሳልፋለን። እርስ በርስ ተላምደን ቤተሰብ እንደሆንን እስኪሰማን ድረስ ጥቂት ዓመታት የወሰደብን ቢሆንም የሚያጋጥሙን አብዛኞቹ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሁን መፍትሔ አግኝተዋል።

ማሬሊዝ፦ ልጆቹን “የአንተ” ወይም “የአንቺ” አሊያም “የእኔ” ብሎ ከመለያየት ይልቅ “የእኛ” ማለቱ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማናል። በአንድ ወቅት አንቶን፣ ልጄን አላግባብ እንደቀጣውና ለራሱ ልጅ ግን በመኪናው ውስጥ ተወዳጅ የሆነውን ቦታ እንደሰጣት ስለተሰማኝ ተበሳጭቼ ተናግሬው ነበር። ይሁን እንጂ የቤተሰብ አንድነት ጋቢና ከመቀመጥ ይበልጥ አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ። ሁሉንም ልጆች በተመሳሳይ መንገድ መያዝ ባንችልም አድልዎ ላለማድረግ እንጥራለን።

አዲሶቹ የቤተሰባችን አባላት ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው ስል በቀድሞ ትዳሬ ውስጥ ስላሳለፍናቸው አስደሳች ጊዜያት ከመናገር እቆጠባለሁ። ከዚህ ይልቅ አሁን ላለን ቤተሰብ አመስጋኝ መሆኔን እገልጻለሁ።

‘ምስጋናን ማስቀደም’

ፍራንስስና ሲሲሊያ ከተጋቡ አራት ዓመት ሆኗቸዋል። ሲሲሊያ ሦስት ትልልቅ ልጆች ያሏት ሲሆን ፍራንስስ ደግሞ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ልጅ አለው።

ፍራንስስ፦ በቀላሉ የምቀረብ ለመሆንና ቶሎ ቅር ላለመሰኘት እጥራለሁ። አብረን የመመገብ ልማድ ያለን ሲሆን ይህን ጊዜ አንድ ላይ ለመጨዋወት እንጠቀምበታለን። በተጨማሪም ሁሉም ልጆች የተለያዩ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማከናወናቸው መላውን ቤተሰብ ስለሚጠቅም የየራሳቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ አበረታታቸዋለሁ።

ሲሲሊያ፦ ከሁሉም ልጆቻችን ጋር ጊዜ የማሳልፍ ሲሆን የሚያስጨንቃቸውንና ቅር የሚያሰኛቸውን ነገር ሲናገሩ አዳምጣቸዋለሁ። በቤተሰብ ሰብሰብ ብለን በምንጨዋወትበት ጊዜ ምስጋናን ለማስቀደምና ማሻሻያ ሊደረግበት የሚገባውን ነገር ከዚያ በኋላ ለማንሳት እንጥራለን። ስህተት በምሠራበት ጊዜ ስህተቶቼን አምኜ በመቀበል ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ።

በእንጀራ አባትና በእንጀራ እናት ማደግ

የሃያ ዓመት ወጣት የሆነው ዩኪ አባቱን ለመጨረሻ ጊዜ ያየው የአምስት ዓመት ልጅ እያለ ነበር። ከጊዜ በኋላ እናቱ፣ ቶሞኖሪ የተባለ ሰው አገባች፤ ይሁንና ዩኪ አሥር ዓመት ሲሆነው እናቱ ሞተች። ከአምስት ዓመት በኋላ ደግሞ የእንጀራ አባቱ፣ ሚሆኮ የተባለች ሴት ሲያገባ ዩኪ ከእንጀራ አባትና ከእንጀራ እናት ጋር መኖር ጀመረ።

ዩኪ፦ የእንጀራ አባቴ እንደገና ለማግባት ሲወስን “የእንጀራ እናት አያስፈልገኝም፤ በሕይወቴ ውስጥ ሌላ ለውጥ እንዲፈጠር አልፈልግም” ብዬ አሰብኩ። ሁኔታውን ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበርኩም፤ እሷንም አልቀርባትም ነበር።

ሚሆኮ፦ ባለቤቴ የእንጀራ ልጁን እሱ እንደሚወደው አድርጌ እንድወደው ጫና ባያደርግብኝም እኔ ግን ከዩኪ ጋር ለመቀራረብ ቆርጬ ነበር። መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቹን፣ መዝናኛውንና ሁልጊዜ ማታ ማታ አብረን ከተመገብን በኋላ የምናደርገውን ውይይት ጨምሮ ዩኪ የለመደውን ፕሮግራም ላለመቀያየር የተቻለንን ሁሉ አድርገናል። በተጨማሪም እናቱን በሞት ማጣቱ ስላስከተለበት ሐዘን ከነገረኝ ወዲህ ከበፊቱ በተሻለ መንገድ ስሜቱን መረዳት ችያለሁ።

ባረገዝኩ ጊዜ የዩኪ ነገር ስላሳሰበን በቤተሰቡ ውስጥ ያለውን ቦታ እንደሚያጣ ሆኖ እንዳይሰማው ለማድረግ እንጥር ነበር። ዩኪ ሕፃኑን እንዲመግበውና እንዲያጥበው እንዲሁም ሽንት ጨርቁን እንዲቀይርለት ያደረግን ሲሆን ስለሚያበረክተው እገዛ በሌሎች ፊት እናመሰግነው ነበር። ትንሹ ኢትሱኪም ዩኪን በጣም ይወድደዋል። “አባባ” ወይም “እማማ” ማለት ከመጀመሩ በፊት ኒኒ (ታላቅ ወንድም) ይል ነበር።

ዩኪ፦ የእንጀራ ልጅ እንደመሆኔ መጠን የብቸኝነትና የባይተዋርነት ስሜት የሚሰማኝ መሆኑ ያለ ነገር ነው። ያለሁበትን ሁኔታ ለሌሎች ለማስረዳት ብሞክርም ብዙ ጊዜ ስሜቴን አይረዱልኝም። ሆኖም የእምነት አጋሮቼ ድጋፍ ስላልተለየኝ ደስተኛ ነኝ። አሁን ከእንጀራ እናቴ ጋር በተያያዘ የነበረኝ ስጋት ተወግዷል። ጥሩ ምክር የምትሰጠኝ ሲሆን እኔም የልቤን አውጥቼ እነግራታለሁ።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ተስፋ አትቁረጡ! የእንጀራ ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦችም ደስተኛና ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ