በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራቅ ባሉ ቦታዎች ምሥራቹን መስበክ

ራቅ ባሉ ቦታዎች ምሥራቹን መስበክ

ራቅ ባሉ ቦታዎች ምሥራቹን መስበክ

ሔለን ጆንስ እንደተናገረችው

በ1970ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ አካባቢ ባንጋሎር፣ ሕንድ ውስጥ በአንድ በተጨናነቀ ገበያ መሃል እየሄድኩ ሳለ አንድ ጎሽ ከየት መጣ ሳይባል በቀንዱ ወደ ላይ አንስቶ አፈረጠኝ። አንዲት ሕንዳዊ ባትደርስልኝ ኖሮ ሰባብሮኝ ነበር። ለመሆኑ ሕንድ ውስጥ ምን እያደረኩ ነበር?

የተወለድኩት በ1931 ሲሆን ያደግሁት ካናዳ በምትገኘውና ቫንኩቨር በምትባለው ውብ ከተማ ውስጥ ነው። ወላጆቼ ጥሩ ሥነ ምግባር የነበራቸው ሰዎች ቢሆኑም ቤተ ክርስቲያን አይሄዱም ነበር። እኔ ግን ለመንፈሳዊ ነገሮች ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ ወጣት ሳለሁ የሰንበት ትምህርትና ክረምት ላይ የሚሰጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እከታተል ነበር።

በ1950፣ በ19 ዓመቴ ከቀድሞ ሚስቱ የወለዳቸው አራት ልጆች ያሉትን ፍራንክ ሺለርን አገባሁ። ከሁለት ዓመት በኋላ አንድ ወንድ ልጅ ወለድን። ሃይማኖት እንዲኖረን እንፈልግ ነበር፤ ሆኖም ፍራንክ ከቀድሞ ሚስቱ ጋር ስለ ተፋታ አባል እንዲያደርጉን ከጠየቅናቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ሊቀበሉን ፈቃደኞች አልሆኑም። ፍራንክ፣ ሁኔታው ስላናደደው ከዚያ ወዲህ ስለ ሃይማኖት ለመነጋገር አይፈልግም ነበር።

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማር

በ1954 ታላቅ ወንድሜ የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ የሥራ ባልደረባው ከመጽሐፍ ቅዱስ ስላሳየው ነገር በደስታ ስሜት ነገረኝ። ምንም እንኳ ብዙ ጥያቄዎች ያሉኝና የይሖዋ ምሥክሮች የት እንደሚሰበሰቡ የማውቅ ቢሆንም ፍራንክ ለሃይማኖት ጥሩ አመለካከት ስላልነበረው በስብሰባቸው ላይ ተገኝቼ አላውቅም። ከጊዜ በኋላ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ቤታችን መጡ። ሃይማኖታቸው ስለ ፍቺ ምን እንደሚያስተምር ማወቅ ፈልጌ ነበር፤ እነሱም ለፍቺ የሚያበቃው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት ምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳዩኝ። (ማቴዎስ 19:3-9) ከዚህም በተጨማሪ ቋሚ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስጀምር ጥያቄዎቼ እንደሚመለሱልኝ አረጋገጡልኝ።

ፍራንክ ከዚህ በፊት በሆነው ነገር በጣም ተበሳጭቶ ስለነበር ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዲኖረው አልፈለገም። በ1955 በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ ተገኝቼ ወደ ቤት ስመለስ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩትን በደስታ ስሜት ለፍራንክ እነግረው ጀመር። ፍራንክ፣ “ይህ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም፤ እንዲያውም ይህ እውነት መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ ካሳየሽኝ ከማይረቡ ስብሰባዎቻችሁ መካከል በአንዱ ላይ እገኛለሁ!” በማለት በጩኸት ተናገረ።

መጽሐፍ ቅዱስ ስሰጠው በአክብሮት ተቀበለኝ። የጻፍኳቸውን ጥቅሶች አውጥተን ተመለከትናቸው፤ መጽሐፍ ቅዱሱ ራሱ እንዲናገር ለማድረግ ስለፈለኩ ብዙም አልተናገርኩም። ፍራንክ ምንም አልተከራከረም፤ ቀሪውን ምሽት በዚያ ጉዳይ ላይ የሚያስብ ይመስል ነበር።

ከጊዜ በኋላ፣ በአንድ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ቃል ገብቶ እንደነበር አስታወስኩት። እንደ ማመንታት ብሎ “ደህና፣ ምን እንደሚከናወን ለማየት አንዴ ብቻ እሄዳለሁ” በማለት መለሰልኝ። ስብሰባ በተገኘበት ዕለት ይቀርብ የነበረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ሚስቶች ለባሎቻቸው መገዛት እንዳለባቸው የሚናገር ነበር። (ኤፌሶን 5:22, 23, 33) በቀረበው ሐሳብ በጣም ተገረመ። በዚያው ጊዜ አካባቢ ፍራንክ “በሥራችሁ እርካታ ይኑራችሁ” የሚል ርዕስ ባለው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ተገኘ። ፍራንክ ታታሪ ሠራተኛ ስለነበር የቀረበውን ትምህርት ወደደው። ከዚያ ወዲህ አንድም ስብሰባ አምልጦት አያውቅም። ብዙም ሳይቆይ ፍራንክ በአገልግሎት በቅንዓት መካፈል ጀመረ፤ እኔም ጥሩ እድገት አድርገው እስከመጠመቅ ደረጃ የደረሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እመራ ነበር። እኔ፣ ፍራንክ፣ እናቴና ወንድሜ ራሳችንን ለአምላክ መወሰናችንን ለማሳየት በዚያው ዓመት ተጠመቅን።

የበለጠ ለመሥራት የነበረኝ ፍላጎት

በ1957 በሲያትል፣ ዋሽንግተን፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውሮ ስለማገልገል የሚገልጽ አንድ ንግግር ቀርቦ ነበር። ‘ይሖዋ ሆይ፣ እኔም መሄድ እፈልጋለሁ፤ እባክህ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ እንድንሄድ እርዳን’ በማለት ጸለይኩ። ሆኖም ፍራንክ፣ ቤተሰባችንን የመመገቡና የመንከባከቡ ኃላፊነት አስጨንቆት ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 5:8

በቀጣዩ ዓመት ቤተሰባችን በኒው ዮርክ ከተማ በተመሳሳይ ቀን ላይ በያንኪ ስታዲየም እና በፖሎ ግራውንድስ ተደርጎ በነበረው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኘ። በሕዝብ ንግግሩ ላይ ከ253,000 በላይ ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር! ፍራንክ በተመለከተውና በሰማው ነገር ልቡ ተነክቶ ነበር። በመሆኑም ወደ ቤት ከተመለስን በኋላ ኬንያን አዲሱ መኖሪያችን ለማድረግ ተስማማን፤ ምክንያቱም ኬንያ እንግሊዝኛ ቋንቋ የሚነገርባት ስትሆን ለልጆቻችንም ጥሩ ትምህርት ቤት ማግኘት እንችላለን።

በ1959 ቤታችንን በመሸጥ ጓዛችንን መኪናችን ላይ ጭነን ወደ ሞንትሪያል፣ ካናዳ ጉዞ ጀመርን። ከካናዳ በመርከብ ወደ ለንደን፣ እንግሊዝ ያመራን ሲሆን ከዚያም ሌላ መርከብ በመያዝ ሜድትራንያን እና ቀይ ባሕርን አቋርጠን ሕንድ ውቅያኖስ ገባን። በመጨረሻም በምሥራቅ አፍሪካ የባሕር ጠረፍ ላይ ወደምትገኘው ሞምባሳ፣ ኬንያ ደረስን። በሚቀጥለው ቀን ባቡር ተሳፍረን የኬንያ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ናይሮቢ ሄድን።

በአፍሪካ ውስጥ ያገኘነው በረከት

በዚያን ወቅት በኬንያ የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት ሥራ ታግዶ ስለነበር የምንሰብከው በጥንቃቄ ነበር። እኛን ጨምሮ ከሌሎች አገሮች የመጡ በርካታ ባልና ሚስት በኬንያ ይኖሩ የነበረ ሲሆን ሁላችንም በአገሪቱ እንድንቆይ ተፈቅዶልን ነበር። ስብሰባዎችን በምናደርግበት ወቅት የተሰብሳቢው ቁጥር ከአሥር እንዳይበልጥ ይደረግ ነበር። ይህ ደግሞ እኛም ሆን ልጆቻችን በስብሰባዎች ላይ የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ ይጠይቅብን ነበር።

ኬንያ ከገባን በኋላ ብዙም ሳይቆይ መኖሪያ ቤት ያገኘን ሲሆን ፍራንክም አንድ ሥራ አገኘ። ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ያገኘኋት የመጀመሪያዋ ሴት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የጀመረች ከመሆኑም በላይ ከጊዜ በኋላ አቅኚ (የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ሆናለች። በተጨማሪም በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የነበረች ጉዲ የምትባል አንዲት የሲክ ሃይማኖት ተከታይ አስጠና ነበር። ይህች ወጣት ቤተሰቧና የሲክ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ጫና ቢያደርጉባትም በአቋሟ ጸንታለች። ጉዲ ለል ከቤት ከተባረረች በኋላ የይሖዋ ምሥክር ከሆነ አንድ ቤተሰብ ጋር አብራ መኖር ጀመረች። ጉዲ ራሷን ለይሖዋ ወስና ከተጠመቀች በኋላ አቅኚ ሆነች። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ከጊልያድ የሚስዮናውያን ትምህርት ቤት ለመመረቅ በቅታለች።

ቤተሰባችን አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጥመውት ነበር። ትልቁ ልጃችን፣ ሩማቲክ ፊቨር የሚባል ኃይለኛ ትኩሳትና ቁርጥማት ያለው በሽታ የያዘው ከመሆኑም በላይ ፍራንክ መኪና እየጠገነ ሳለ በተነሳ እሳት ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰበት፤ በዚህም ምክንያት ሥራውን አጣ። ከጊዜ በኋላ ፍራንክ 1,000 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው የታንጋኒካ (የዛሬዋ ታንዛንያ) ዋና ከተማ በሆነችው በዳሬ ሰላም ሥራ አገኘ። በመሆኑም ጓዛችንን በአንድ መኪና ላይ ጭነን ረጅሙን ጉዞ ተያያዝነው። በዚያን ወቅት ዳሬ ሰላም ውስጥ አንድ ትንሽ ጉባኤ የነበረ ሲሆን እነሱም በጥሩ ሁኔታ ተቀበሉን።

ምንም እንኳ በወቅቱ በታንዛንያ የስብከቱ ሥራ የታገደ ቢሆንም እገዳው ያን ያህል ጥብቅ አልነበረም። በ1963 ሚልተን ሄንሸል ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በመወከል ሊጎበኘን መጣ። ወንድም ሄንሸል በአገሪቱ ውስጥ ካሉት አዳራሾች ሁሉ ምርጥ በሆነው ኩሬምጄ በተባለው አዳራሽ ውስጥ ንግግር እያቀረበ ሳለ አለባበሳቸው ሲታይ ድሃ የሚመስሉ አንድ አረጋዊ ሰው አጠገቤ ቁጭ አሉ። ሰላምታ ከሰጠኋቸው በኋላ መጽሐፍ ቅዱሴንና የመዝሙር መጽሐፌን አብረውኝ እንዲከታተሉ አደረኩ። ስብሰባው እንዳለቀ በሌላም ጊዜ እንዲገኙ ጋበዝኳቸው። ግለሰቡ እንደወጡ የአገሩ ተወላጅ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች እየተጣደፉ ወደ እኔ መጡ።

“እኚህ ሰው ማን እንደሆኑ ታውቂያለሽ? የዳሬ ሰላም ከንቲባ እኮ ናቸው!” በማለት ነገሩኝ። ቀደም ሲል ስብሰባውን እንደሚበትኑ በመናገር ወንድሞችን አስፈራርተዋቸው ነበር። አጠገቤ መጥተው የተቀመጡት ድሃ በመሆናቸው ምክንያት እንደምጠየፋቸው አስበው ስለነበር ይህን ሰበብ አድርገው ስብሰባውን መበተን እንደሚችሉ ተሰምቷቸው ነው። ሆኖም ባዩት ደግነትና አሳቢነት በጣም ስለተነኩ ስብሰባው ያለ ምንም እንቅፋት እንዲቀጥል ፈቅደዋል። በስብሰባው ላይ 274 ሰዎች ተገኝተው የነበረ ሲሆን 16 ሰዎች ተጠምቀዋል!

ታንዛንያ በነበርንበት ጊዜ አገሪቷ ነፃነቷን አገኘች። ከዚያ ወዲህ ከውጭ አገር ዜጎች ይልቅ የአገሪቱ ተወላጅ ለሆኑ ሥራ ፈላጊዎች ቅድሚያ ይሰጥ ጀመር። በዚህም የተነሳ አብዛኛዎቹ የውጭ ዜጎች አገሪቱን መልቀቅ ግድ ሆኖባቸዋል፤ ፍራንክ ግን ተስፋ ሳይቆርጥ ሥራ ለማግኘት ጥረት ማድረጉን ቀጠለ። በመጨረሻም በናፍጣ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን መጠገን የሚችል ልምድ ያለው መካኒክ ያስፈልግ ስለነበር ጥረቱ ተሳካለት። በዚህ ምክንያት አራት ተጨማሪ ዓመት ለመቆየት ችለናል። የፍራንክ የሥራ ኮንትራት ሲያልቅ ወደ ካናዳ የተመለስን ሲሆን የመጨረሻዎቹ ልጆቻችን አድገው ትዳር እስኪመሠርቱ ድረስ እዚያው ቆየን። ከዚያ በኋላ ገና ወጣት እንደሆንን ይሰማን ስለነበር የበለጠ ለመሥራት ጉጉት አደረብን።

ወደ ሕንድ ሄድን

በ1970 ቦምቤይ (የዛሬዋ ሙምባይ) የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በሰጠው ማበረታቻ መሠረት በወቅቱ 1.6 ሚሊዮን የሕዝብ ብዛት ወደነበራት ወደ ባንጋሎር ሄድን። ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ከጎሽ ቀንድ ለጥቂት ያመለጥኩት እዚህ ከተማ ነበር። በወቅቱ ባንጋሎር ውስጥ 40 አስፋፊዎች የሚገኙበት አንድ የእንግሊዝኛ ጉባኤና ከከተማው ራቅ ብሎ የሚገኝ አንድ የታሚል ቋንቋ ቡድን ነበር። ፍራንክ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ረገድ እድገት አድርገው ከጊዜ በኋላ የጉባኤ ሽማግሌዎች ለመሆን የበቁ በርካታ ወንዶችን አስጠንቷል። እኔም ብሆን የይሖዋ አገልጋዮች እስከ መሆን ደረጃ የደረሱ ቤተሰቦችን አስጠንቻለሁ።

በጣም ድሃ የሆኑ ሰዎች በሚኖሩበት ሰፈር ውስጥ የምትኖር ግሎሪያ የምትባል አንዲት ሴት ነበረች። ለመጀመሪያ ጊዜ ቤቷ ሄጄ ሳነጋግራት ወደ ውስጥ እንድገባ ጋበዘችኝ። ቤቷ ውስጥ ምንም ቁሳቁስ ስላልነበረ ወለሉ ላይ ተቀመጥን። አንድ መጠበቂያ ግንብ ትቼላት ስለነበረ ከመጽሔቱ ውስጥ ራእይ 4:11 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ቆርጣ በማውጣት ግድግዳው ላይ በየቀኑ ልታየው በምትችልበት ቦታ ለጠፈችው። በጥቅሱ ውስጥ ‘ይሖዋ ሆይ፣ ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል’ የሚሉት ቃላት ይገኙበታል። ይህች ሴት ከአንድ ዓመት በኋላ ተጠመቀች።

ፍራንክ በሕንድ የመጀመሪያ የሆነውን የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ግንባታ በበላይነት እንዲከታተል ቦምቤይ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ለአንድ ዓመት እንዲሠራ ተጋበዘ። የስብሰባ አዳራሹ የሚሠራው በቅርንጫፍ ቢሮው ሕንጻ ላይ አንድ ፎቅ በመጨመር ነበር። በወቅቱ በሕንድ የነበረው አጠቃላይ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከ3,000 ብዙም የማይበልጥ ሲሆን በቅርንጫፍ ቢሮው የሚያገለግሉት ደግሞ ወደ 10 የሚጠጉ ነበሩ። በ1975 የነበረንን ገንዘብ እየጨረስን ስለመጣን ወደ ካናዳ መመለስ ግድ ሆነብን፤ በዚህ ወቅት በጣም ከምንወዳቸው ጓደኞቻችን በመለየታችን በጣም አዝነን ነበር።

እንደ ገና ወደ አፍሪካ ተመለስን

አሁን አሥር ዓመታት አልፈዋል፤ በመሆኑም ፍራንክ የጡረታ አበል ማግኘት የሚችልበት ዕድሜ ላይ ደረሰ። ስለዚህ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በመገንባቱ ዓለም አቀፍ ፕሮግራም ውስጥ ለመሳተፍ ራሳችንን በፈቃደኝነት አቀረብን። ኢጌዱማ፣ ናይጄሪያ ውስጥ ግንባታ በመካሄድ ላይ ስለነበር ወደዚያ እንድንሄድ የሚጠይቅ አንድ ደብዳቤ ደረሰን። ኢጌዱማ እያለን ፍራንክ በአቅራቢያው ባለች አንዲት መንደር ውስጥ የሚኖር አንድ ሰው ያስጠና ሲሆን ሰውየው ከጊዜ በኋላ እድገት አድርጎ ናይጄሪያ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ አባል ሆኗል።

በመቀጠልም በቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ላይ ለመሥራት ወደ ዛየር አመራን። ብዙም ሳይቆይ በዛየር የስብከቱ ሥራችን ታግዶ ፓስፖርታችንን ተነጠቅን። ፍራንክ ሥራ ላይ እያለ የልብ ሕመም አጋጥሞት ስለነበር እገዳው ለማገገም የሚያስችል ጊዜ አስገኝቶለታል። ቆየት ብሎ ሁሉም የግንባታ ሠራተኞች ሥራውን ትተው መሄድ ግድ ሆነባቸው፤ እኛም ወደ ጎረቤት አገር ወደ ላይቤሪያ ተላክን። እዚያም ፍራንክ፣ ሞኖሮቪያ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ አንድ ጀነሬተር እንዲጠግን ተጠየቀ። በ1986 ቪዛችን ጊዜ ስላለፈበት እንደገና ወደ ካናዳ መመለስ ነበረብን።

በመጨረሻ ወደ ኢኳዶር አመራን

ከጥቂት ጊዜያት በኋላ አንዲ ኪድ የሚባል አንድ የቅርብ ወዳጃችን ኢኳዶር እንደሄደና በስብከቱ ሥራ አስደሳች እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ሰማን። በጉባኤ ውስጥ ያለው ሽማግሌ እሱ ብቻ በመሆኑ በስብሰባ ወቅት አብዛኞቹን ክፍሎች የሚያቀርበው እሱ ነበር። አንዲ ባቀረበልን ግብዣ መሠረት በ1988 ኢኳዶር የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሮ የጎበኘን ከመሆኑም በላይ በእነሱ ጥያቄ እዚያው ቀረን።

ለመኖሪያ የሚሆን ምቹ ቤት ያገኘን ቢሆንም ስፓንኛ መማር ነበረብን፤ በወቅቱ ፍራንክ 71 ዓመቱ ነበር። የስፓንኛ ቋንቋ ችሎታችን ውስን ቢሆንም በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ 12 ሰዎች እንዲጠመቁ መርዳት ችለናል። ፍራንክ በኢኳዶር የቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ላይ እንዲሠራ ተጠየቀ። በተጨማሪም፣ በጉዋያኪል የመጀመሪያ ከሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የአንዷን ባለቤት መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንቷል። ለ46 ዓመታት ሲቃወም የነበረው ይህ ሰው ጓደኛችንና መንፈሳዊ ወንድማችን ሆኗል።

ከባድ ሐዘን ደረሰብኝ

ሰላማዊ ውቅያኖስ አጠገብ ባለች አንኮን በምትባል ትንሽ ከተማ አቅራቢያ መኖር የጀመርን ሲሆን በዚህ ቦታ አንድ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ በመገንባቱ ሥራ እርዳታ ለማበርከት ችለናል። የሚያሳዝነው፣ ፍራንክ ኅዳር 4, 1998 የአገልግሎት ስብሰባ ላይ የመጨረሻውን ንግግር ከሰጠ በኋላ ልብ ድካሙ ተነስቶበት በዚያው ምሽት ሞተ። በዚህ ወቅት መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ብዙ ድጋፍ አድርገውልኛል! በሚቀጥለው ቀን መንግሥት አዳራሹ አጠገብ ካለው መንገድ ማዶ በሚገኝ የመቃብር ሥፍራ ተቀበረ። የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለውን ሥቃይ በቃላት መግለጽ ያስቸግራል።

የቤተሰብና ሕግ ነክ ጉዳዮችን ለማስፈጸም አሁንም እንደገና ወደ ካናዳ መመለስ ነበረብኝ፤ በዚህ ጊዜ ግን ወደዚያ የሄድኩት ብቻዬን ነበር። ሐዘን ቢደርስብኝም ይሖዋ አልረሳኝም። እንደገና ተመልሼ ከሄድኩ በደስታ እንደሚቀበሉኝ የሚገልጽ ደብዳቤ ከኢኳዶር ቅርንጫፍ ቢሮ ደረሰኝ። በዚህ መሠረት ወደ ኢኳዶር የተመለስኩ ሲሆን ቅርንጫፍ ቢሮው አጠገብ አንድ ትንሽ አፓርታማ አገኘሁ። ቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ መሥራቴ እንዲሁም በመስክ አገልግሎት ራሴን ማስጠመዴ የደረሰብኝን ሐዘን እንድቋቋም ረድቶኛል፤ ያም ሆኖ ግን የብቸኝነት ስሜት ያጠቃኝ ነበር።

በሥራው ወደ ፊት መግፋት

ከጊዜ በኋላ ጁኒየር ጆንስ ከሚባል ወንድም ጋር ተዋወቅኩ። ጁኒየር በ1997 ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ኢኳዶር የመጣው በአቅኚነት ለማገልገል ነበር። አንድ ዓይነት ግብ የነበረን ከመሆኑም በላይ በጋራ የሚያስደስቱን ነገሮች ነበሩ። እኔና ጁኒየር ጥቅምት 2000 ተጋባን። ጁኒየር የግንባታ ሥራ ልምድ ስለነበረው በአንዲስ ተራሮች ላይ በምትገኝ ኩኒካ በምትባል አንዲት ከተማ ውስጥ የተጀመረውን ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሥራ እንድናጠናቅቅ ተጋበዝን። ከዚያም በሚያዝያ 30, 2006 የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ጄፈሪ ጃክሰን ከኒው ዮርክ በመምጣት 6,554 ተሰብሳቢዎች በተገኙበት የውሰናውን ንግግር ሰጠ።

የመንግሥቱ የስብከት ሥራ እንደ አፍሪካ፣ ሕንድ እና ደቡብ አሜሪካ ባሉ ርቀው በሚገኙ ቦታዎች እጅግ በሚያስገርም ሁኔታ እድገት ያደርጋል ብሎ ማን አስቦት ያውቃል? አሁን፣ እኔም ሆንኩ ጁኒየር ጡረታ የመውጣት ሐሳብ የለንም። በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍኳቸው ከ50 የሚበልጡ ዓመታት በፍጥነት ከማለፋቸው የተነሳ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ትላንት የጀመርኩ ያህል ሆኖ ይሰማኛል። አዲሱ ዓለም ሲመጣ አሁን የምንኖርበት ጊዜ የትላንትናን ያህል በፍጥነት ያለፈ እንደሚመስለን እርግጠኛ ነኝ።—ራእይ 21:3-5፤ 22:20

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ያገለገልንባቸው ቦታዎች

ካናዳ → እንግሊዝ → ኬንያ → ታንዛንያ

ካናዳ → ሕንድ

ካናዳ → ናይጄሪያ → ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ (ዛየር) → ላይቤሪያ

ካናዳ → ኢኳዶር

[ሌሎች ቦታዎች]

ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ

[ሥዕል]

ሕንድ ውስጥ ከፍራንክ ጋር ወደ ትልቅ ስብሰባ ስንሄድ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ጁኒየር ጆንስ ጋር