በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

በሽታ ፈጽሞ የማይኖርበት ጊዜ! (ጥር 2007) አንዳንድ ሰዎች “ውጤት ለሌላቸው፣ አልፎ ተርፎም ጎጂ ለሆኑ ሕክምናዎችና መድኃኒቶች ሲሉ ገንዘባቸውን ብሎም ጊዜያቸውን ያባክናሉ” በማለት የገለጻችሁት ሐሳብ አማራጭ የሕክምና ዓይነቶችን አስመልክቶ የተናገራችሁት ይመስላል። ይህን እንድል ያደረገኝ መጽሔቱ ከእነዚህ የሕክምና ዓይነቶች መካከል የአንዳንዶቹን ውጤታማነትና አስተማማኝነት አስመልክቶ ጥያቄዎችን ማንሳቱ ነው። ንቁ! ይህን ሐሳብ ያሰፈረው ዘመናዊ ሕክምና ይበልጥ አስተማማኝና ውጤታማ ስለሆነ በዚያ መጠቀምን ለማበረታታት ነው? የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላላ የኦዲት ቢሮ እንዳለው ከሆነ ከአስተማማኝነትም ሆነ ከውጤታማነት አኳያ ዘመናዊ ሕክምና የተሻለ አለመሆኑን ለማመን የሚያስችሉ በርካታ ምክንያቶች አሉ።

ጂ. ኬ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

የንቁ! መጽሔት አዘጋጆች ምላሽ:- በአንድ ወቅት አስተማማኝና ውጤታማ ናቸው ተብለው ሰፊ ተቀባይነት ያገኙ በርካታ የሕክምና ዓይነቶች ከጊዜ በኋላ አደገኛ መሆናቸው ታይቷል። ይህ ሁኔታ በሁለቱም ማለትም በዘመናዊውም ሆነ አማራጭ በሚባሉት የሕክምና ዓይነቶች ላይ ታይቷል። ይህንን በተመለከተ ትክክለኛው አካሄድ፣ ልትወስደው ያሰብከው ሕክምና የትኛውም ይሁን ስለሚያስገኘው ጥቅምና ስለሚያስከትለው አደጋ ጥሩ ግንዛቤ ማግኘት ብሎም ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የማይጋጭ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። ይህ ደግሞ የግል ውሳኔ ነው። ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደገለጽነው “ንቁ!” ይህ ሕክምና ይሻላል የሚል ሐሳብ አይሰጥም። ክርስቲያኖችም ቢሆኑ ሕክምናን በተመለከተ ሌሎች የሚያደርጉትን ምርጫ ከመንቀፍ አሊያም በውሳኔያቸው ላይ ከመፍረድ ይቆጠባሉ። መጽሔቱ እንደገለጸው አማራጭም ሆነ ዘመናዊ የሕክምና ዓይነቶች ለሰው ዘር የጤና ችግሮች መፍትሔ አያመጡም። ማንም ሰው የማይታመምበትን ጊዜ የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው።—ራእይ 21:3, 4

‘እንደ ሚዳቋ የምዘልበት’ ጊዜ ይመጣል (ነሐሴ 2006) የፍራንቼስኮ አባቴማርኮ ትዕግሥትና ትሕትና ቆም ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል። ወንድም ፍራንቼስኮ ይሖዋን ማገልገል እንዲችል ይታገል የነበረው ካለበት አካላዊ ጉዳት ጋር ብቻ አልነበረም፤ የሚሰሙትን አሉታዊ ስሜቶችም ማሸነፍ ነበረበት። የእሱ ተሞክሮ፣ ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ይሖዋን አቅማችን የፈቀደውን ያህል ማገልገል እንደምንችል አስገንዝቦኛል። ከዚህም ባሻገር የአምላክን ቃል ተግባራዊ ማድረጉ በሕይወቱ ውስጥ አስገራሚ ለውጦች እንዲያደርግ እንዴት እንደረዳው ማወቄ አበረታቶኛል።

ኤን. ጂ.፣ ካምቦዲያ

ፍራንቼስኮ በርካታ ችግሮችን መቋቋም ነበረበት። ይሁንና እውነትን እንደሰማ እነዚህን ችግሮቹን ተስፋ ሳይቆርጥ ተጋፍጧል። ፍራንቼስኮ ቁርጥ አቋም በመውሰድ ረገድ ግሩም ምሳሌ ነው! የእሱ ታሪክ እንደ እኔ ሁሉ ሌሎችንም ለሥራ እንደሚያነሳሳ ተስፋ አደርጋለሁ።

ኤም. ዲ.፣ ደቡብ አፍሪካ

ይህን ታሪክ በጣም ወድጄዋለሁ! ወንድም ፍራንቼስኮ አባቴማርኮን በአካል አግኝቼ የእሱ ተሞክሮ ለይሖዋ በማቀርበው አገልግሎት ይበልጥ እንድገፋበት እንዴት እንዳበረታታኝ ብነግረው ደስ ባለኝ ነበር።

ጄ. ቢ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ወንድም ፍራንቼስኮ፣ በቅንዓትና በጽናት ረገድ ለተውከው ግሩም ምሳሌ ላመሰግንህ እወዳለሁ። በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንደ ሚዳቋ እንደምትዘል እርግጠኛ ነኝ። ከልብ የሚወዱህና ስለ አንተ የሚጸልዩ ወንድሞችና እህቶች እንዳሉህ ብታውቅ ደስ ይለኛል።

ኤስ. ጂ.፣ ሩሲያ