በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራሴን የምስተው ለምንድን ነው?

ራሴን የምስተው ለምንድን ነው?

ራሴን የምስተው ለምንድን ነው?

ሐኪሙ በአንድ መሣሪያ ተጠቅሞ በዓይኔ ውስጥ ያለውን የግፊት መጠን ለመለካት የዓይኔን ብሌን መንካት አስፈልጎት ነበር። በዚህ ጊዜ ቀደም ሲል እንደሚያጋጥመኝ ያለ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ገባኝ። አንዲት ነርስ ለምርመራ ደም ከሰውነቴ ስትወስድም ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጥመኛል። ራሴን እስታለሁ። እንዲያውም አንዳንዴ ስለ አደጋዎች ማውራት ብቻ እንኳ ራሴን እንድስት ያደርገኛል።

ከብሪታንያ የተገኘ አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው እኔን ጨምሮ 3 በመቶ የሚያህለው የዓለም ሕዝብ ብዙውን ጊዜ ከላይ እንደተጠቀሱት ባሉ ሁኔታዎች ወቅት ራስን የመሳት ችግር ያጋጥመዋል። አንተም እንዲህ ዓይነት ችግር ካለብህ ብዙም ባይሳካልህም እንኳ ራስህን ላለመሳት ጥረት አድርገህ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም በሰዎች ፊት ላለመውደቅ ስትል ወደ መጸዳጃ ቤት ለመሄድ ሞክረህ ይሆናል። እንዲህ ማድረጉ ግን ጥሩ አይደለም። ያሰብክበት ቦታ ሳትደርስ ድንገት ልትወድቅና ጉዳት ሊደርስብህ ይችላል። ብዙ ጊዜ ራስን የመሳት ችግር ስለሚያጋጥመኝ መንስዔው ምን እንደሆነ ለማወቅ ወሰንኩ።

አንድ ጎበዝ ዶክተር ካማከርኩኝና አንዳንድ መጻሕፍትን ካገላበጥኩ በኋላ ይህ ዓይነቱ ችግር ቬዞቬጋል ሪአክሽን እንደሚባል አወቅሁ። * ይህ ሁኔታ በአንዳንድ ወቅቶች ለምሳሌ ያህል ከተቀመጥክበት ስትነሳ ደም በትክክል እንዲዘዋወር የሚያደርገው የሰውነት ሥርዓት በአግባቡ መሥራት ባለመቻሉ ምክንያት የሚከሰት ችግር እንደሆነ ይታሰባል።

ደም እንደመመልከት ወይም የዓይን ምርመራ እንደማድረግ ባሉ አንዳንድ አጋጣሚዎች አተነፋፈስን፣ የምግብ መፈጨትንና የልብ ምትን የመሳሰሉ ሂደቶችን የሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት ቆመህ ወይም ተቀምጠህ እያለ ልክ በምትተኛበት ወቅት እንደሚሆነው ይሆናል። በመጀመሪያ ከመጨነቅህ የተነሳ ልብህ በጣም ይመታል። ከዚያም የልብ ምትህ ወዲያውኑ ይቀንስና እግርህ አካባቢ የሚገኙት የደም ሥሮች ይሰፋሉ። በዚህም ምክንያት እግርህ አካባቢ ያለው ደም ይበዛና ራስህ ውስጥ የሚገኘው የደም መጠን ይቀንሳል። ስለዚህ አንጎልህ በቂ ኦክስጅን ስለማያገኝ ራስህን ትስታለህ። እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዳያጋጥምህ መከላከል የምትችለው እንዴት ነው?

ምናልባት ለምርመራ ደም ስትሰጥ ዞር ልትል ወይም ልትተኛ ትችላለህ። ከላይ እንደተገለጸው ራስህን ከመሳትህ በፊት የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ስለምታይ ከመውደቅህ በፊት አንዳንድ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችል ጊዜ ይኖርሃል። ብዙ ዶክተሮች እንዲህ ባለው ወቅት ተኝተህ እግርህን ወንበር ወይም ግድግዳ ላይ መስቀልህ ጥሩ እንደሆነ ሐሳብ ይሰጣሉ። እንዲህ ማድረግህ በእግርህ አካባቢ ያለው ደም ወደ ሌሎች የሰውነትህ ክፍሎች እንዲሰራጭ ስለሚያደርግ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል ያስችልሃል። ከዚያም በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ይሻልሃል።

ይህ ሐሳብ እኔን እንደረዳኝ ሁሉ አንተንም ከረዳህ የቬዞቬጋል ሪአክሽን ምልክቶችን ለይተህ ማወቅ ትችላለህ። ከዚያም አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ ራስህን ስተህ እንዳትወድቅ ማድረግ ትችላለህ።—ተጽፎ የተላከልን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 “ቬዞቬጋል” የሚለው ቃል ቬገስ በተባለው ረጅም ነርቭ ላይ በሚገኙት የደም ሥሮች ላይ የሚፈጠረውን ሁኔታ ያመለክታል። ቬገስ የሚለው ቃል ከላቲን የተወሰደ ሲሆን “መቃወስ” የሚል ትርጉም አለው።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በሕክምና ወቅት መተኛት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል