በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም ውስጥ የሐኪሞች ሕይወት

ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም ውስጥ የሐኪሞች ሕይወት

ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም ውስጥ የሐኪሞች ሕይወት

ማይሞኒደስ በ1174 የግብጽ ልዑላን ሐኪም እንዲሆን የተሾመ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ነበር። በየቀኑ ወደ ቤቱ ሲመለስ ስለሚያደርገው ነገር እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ትንሽ ምግብ እቀምሳለሁ። በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ምግብ የምቀምሰው በዚህ ጊዜ ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ ወደ ታካሚዎቼ ተመልሼ ሁኔታቸውን እከታተላለሁ፣ የሚያስፈልጋቸውን መድኃኒት አዛለሁ እንዲሁም መመሪያ እሰጣቸዋለሁ። እስከ ማታ ድረስ ታካሚዎች ሲወጡና ሲገቡ ያመሻሉ። አንዳንድ ጊዜ . . . መናገር እንኳ እስኪያቅተኝ ይደክመኛል።”

ሐኪም መሆን መሥዋዕትነት ያልጠየቀበት ጊዜ የለም። ቢሆንም የዛሬዎቹ ሐኪሞች የሚሠሩበት ዓለም ሁኔታ በፍጥነት በመለዋወጥ ላይ ነው። እንደ ማይሞኒደስ ሁሉ ዛሬ ያሉ ሐኪሞችም አድካሚ የሆነ የሥራ ጫና አለባቸው። ይሁን እንጂ እንደ ድሮዎቹ ሐኪሞች ይከበራሉ? አዳዲሶቹ ሁኔታዎች በዶክተሮቹ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ምን ዓይነት ጫና አሳድረዋል? የቅርብ ጊዜ ግኝቶች ሐኪሞች ከታካሚዎቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት የነኩባቸው እንዴት ነው?

ግንኙነቱ ተለውጧል

ሐኪሞች የሚጠቀሙባቸውን መድኃኒቶች በሙሉ በአንድ ቦርሣ ተሸክመው ይንቀሳቀሱ የነበሩባቸውን ጊዜ ዛሬም የሚያስታውሱ ሰዎች አሉ። እንደ ዛሬው ሁሉ ያኔም ሰዎች ለዶክተሮች የነበራቸው አመለካከት የተለያየ ነበር። አብዛኞቹ ሐኪሞች ስለ ችሎታቸው በጥልቅ ይከበሩ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ደረጃ ሞገስ ይሰጣቸው እንዲሁም ስለ ጥሩ ምግባራቸው ይደነቁ ነበር። ቢሆንም በሚያስከፍሉት ዋጋ መብዛት መተቸታቸው፣ ማዳን ሲያቅታቸው መናቃቸውና ርኅራኄ የጎደላቸው መስለው ሲታዩ መወገዛቸው አልቀረም።

እንዲህም ሆኖ ብዙ ሐኪሞች አንድን ቤተሰብ እስከ ልጅ ልጅ ድረስ ለመርዳት በመቻላቸው የጠለቀ እርካታ ያገኙ ነበር። በየቤቱ እየሄዱ ከማከማቸውም በላይ በገጠር አካባቢዎች ቆይተው ከሚያክሟቸው ቤተሰቦች ጋር ይመገባሉ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ልጅ ሲያዋልዱ እዚያው እስከማደር ይደርሱ ነበር። ብዙዎቹ ሐኪሞች ለታካሚዎቻቸው የሚሰጡትን መድኃኒት ራሳቸው ያዘጋጁ ነበር። ራስ ወዳድ ያልሆኑ ሐኪሞች የገንዘብ አቅም የሌላቸውን በነፃ ከማከም አልፈው ከሰኞ እስከ ሰኞ የ24 ሰዓት አገልግሎት ይሰጡ ነበር።

እርግጥ፣ ዛሬም ቢሆን ያን ያህል የሚሠሩ ሐኪሞች አሉ። ይሁን እንጂ በሐኪሞችና በታካሚዎቻቸው መካከል ያለው ግንኙነት ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ በእጅጉ ተለውጧል። ይህ ለውጥ ባለፉት በርካታ መቶ ዓመታት ውስጥ ከነበረው ለውጥ ይበልጣል። እነዚህ ለውጦች የመጡት በምን ምክንያት ነው? በመጀመሪያ በየቤቱ እየሄዱ ስለማከም እንመልከት።

ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ማከም የት ደረሰ?

በሽተኞችን በየቤታቸው እየሄዱ ማከም ተቀባይነት ያገኘ የሕክምና አሰጣጥ ሆኖ ቆይቶ ነበር። ዛሬም ቢሆን በአንዳንድ አገሮች ይሠራበታል። ይሁን እንጂ በብዙ የዓለም ክፍሎች ልማዱ እየተረሳ መጥቷል። ዘ ታይምስ ኦፍ ኢንድያ “በዚህ ስፔሽያሊስቶች በሞሉበት ዓለም በሽተኛ አልጋ አጠገብ ተቀምጦ የሚያጽናና፣ የቤተሰቡን ሁኔታ አሳምሮ የሚያውቅና በተፈለገበት ጊዜ ሁሉ ቤት ድረስ መጥቶ ለማከም ፈቃደኛ የሆነ ሐኪም ፈጽሞ የተረሳ ሆኗል” ሲል ጽፏል።

የሕክምና እውቀት እጅግ በመራቀቁ ምክንያት ብዙ ሐኪሞች በተወሰኑ የሕክምና መስኮች ላይ ብቻ ስለሚያተኩሩና ከሌሎች ሐኪሞች ጋር አብረው ስለሚሠሩ ታካሚዎች ሐኪም ቤት በሄዱ ቁጥር በተለያዩ ሐኪሞች ለመታከም ይገደዳሉ። በዚህ የተነሣ ብዙ ሐኪሞች ከሚያክሟቸው ቤተሰቦች ጋር ዘላቂ የሆነ ዝምድና ሊኖራቸው አልቻለም።

ቤት ድረስ እየሄዱ ማከም እየቀረ የመጣው ሐኪሞች በላቦራቶሪ ምርመራዎችና የመመርመሪያ መሣሪያዎች በይበልጥ መገልገል ከጀመሩበት ካለፈው መቶ ዓመት ወዲህ ነው። በብዙ አገሮች የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት በየቤቱ እየሄዱ ማከም የሐኪሞችን ጊዜ ማባከን እንደሚሆን እየተሰማቸው መጣ። በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ታካሚዎች መጓጓዣ ማግኘት ስለማይቸግራቸው በቀላሉ ሐኪም ቤት ሄደው መታከም ይችላሉ። በተጨማሪም በአንድ ወቅት ዶክተሮችን ብቻ ይጠብቅ የነበረው የድንገተኛ አደጋ ሕክምናና ሌሎች ቀላል ሕክምናዎች በጤና ረዳቶች ሊሰጡ ይችላሉ።

የሁኔታዎች መለወጥ

በዛሬው ዓለም በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ ሐኪሞች እምብዛም አይገኙም። በአሁኑ ጊዜ የሕክምና አገልግሎቶች አብዛኛውን ጊዜ የሚሰጡት በመንግሥታዊ ተቋማት ወይም በጤና አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ነው። ሐኪሞች የእነዚህ መንግሥታዊ ተቋማት ወይም ኩባንያዎች ተቀጣሪዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ብዙ ዶክተሮች በሐኪም-ታካሚ ግንኙነት ውስጥ ሦስተኛ ወገን መግባቱን አይወዱትም። እንደነዚህ ያሉት ድርጅቶች ብዙውን ጊዜ ዶክተሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ በሽተኞችን እንዲያዩ ይፈልጋሉ። በብሪታንያ የሚኖሩት የጠቅላላ ደዌ ሐኪም፣ ዶክተር ሺላ ፐርኪንስ “ከሰባት እስከ አሥር ደቂቃ በሚደርስ ጊዜ ውስጥ አንድ በሽተኛ አይቼ እንድጨርስ እገደዳለሁ። ከዚህ ጊዜ ውስጥ አብዛኛውን የማሳልፈው ስለታካሚው የሚገልጹ መረጃዎችን ኮምፒውተር ላይ በመሙላት ነው። ከታካሚው ጋር ትርጉም ያለው ዝምድና ለመመሥረት የሚያስችል ጊዜ የለም። ይህ ደግሞ በጣም ተስፋ ያስቆርጣል” ብለዋል።

ሐኪሞች ተግባራቸውን የሚያከናውኑበት እየተለወጠ ያለው ዓለም ታካሚዎች ይበልጥ ተደማጭነት እያገኙ የመጡበት ነው። በአንድ ወቅት “የሐኪም ትእዛዝ” አላንዳች ጥያቄ ተቀባይነት ያገኝ ነበር። ዛሬ ግን በበርካታ አገሮች ታካሚው የሚሰጠውን ሕክምና ለመቀበል ወይም ላለመቀበል መምረጥ እንዲችል ሐኪሞች ስለሚሰጡት ሕክምናና ሕክምናው ሊያስከትል ስለሚችለው ውጤት በቂ ማብራሪያ እንዲሰጡ ይገደዳሉ። ስለዚህ በሐኪምና በታካሚዎች መካከል የነበረው ዝምድና ተለውጧል። በአንዳንዶች አስተያየት ሐኪሞች ከቴክኒክ አዋቂዎች የተለዩ ሆነው አይታዩም።

በዚህ ፈጣን ለውጥ በሚካሄድበት ዓለም አብዛኞቹ ሐኪሞች ሴቶች ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ ሴት ሐኪሞች የተሻሉ አዳማጮች መሆናቸው ስለታየ ይበልጥ ተፈላጊዎች ናቸው። እነርሱ ያሳደሩት ተጽዕኖ የሕክምና ሞያ ይበልጥ ስለሰው ስሜት የሚያስብ እንዲሆን አድርጓል።

ብዙ ሰዎች የታካሚዎችን ስሜትና የሚኖሩበትን ውጥረት የሚረዱ ሐኪሞችን ይወዳሉ። ይሁን እንጂ የሐኪሞቻቸውን ስሜትና ያለባቸውን ውጥረት የሚረዱ ታካሚዎችስ ምን ያህል ናቸው? ብሎ መጠየቅ ምክንያታዊ ነው። ይህ በሐኪሞችና በታካሚዎች መካከል ያለውን ዝምድና ለማሻሻል ይረዳል። በዚህ ረገድ የሚቀጥለው ርዕስ ጠቃሚ ነው።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማይሞኒደስ

[ምንጭ]

ብራውን ወንድማማቾች

[በገጽ 4 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ባለፉት ዘመናት ዶክተሮች በየቤቱ እየሄዱ ያክሙ ነበር