በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ባለ እሳታማ ላባዎቹ ዳንሰኞች

ባለ እሳታማ ላባዎቹ ዳንሰኞች

ባለ እሳታማ ላባዎቹ ዳንሰኞች

ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ድምፃቸው እንደ ብዙ ሠራዊት ድምፅ ይተማል። አለማቋረጥ የሚሰማው ውካታቸው ሐይቁን ተሻግሮ ያስተጋባል። በሚያብረቀርቀው አረንጓዴ ባሕር ላይ በሺህ የሚቆጠሩ የወይን ጠጅ ቀለም ያላቸው አእዋፍ ይንሳፈፋሉ። ከላይ ደግሞ ሰማዩን በሚያምር በረራቸው ሸፍነውታል። ከባሕሩ በላይ ቀይ ሆኖ በሚታየው ረዥምና ቀጭን ክንፋቸው አየሩን ይቀዝፋሉ። ይህ በደማቅ ቀለም የሚያብረቀርቁት የአእዋፍ ትዕይንት ልብ ይሰርቃል። በምድር ላይ እንደዚህ የሚያምር የአእዋፍ ትርዒት የለም ብለው የሚከራከሩ አሉ። የአፍሪካ ታላቁ ስምጥ ሸለቆ ባለ ወይን ጠጅ ቀለም ፍላሚንጎዎች ናቸው።

የባለ ረዥም ቅልጥሞቹ ውበት

ፍላሚንጎዎች በሚያምረው ቁመናቸውና ውበታቸው መደነቅና መወደድ የጀመሩት ከብዙ ዘመናት በፊት ነው። የረዥም አንገታቸው ምስል ድንጋይ ላይ ተቀርጾ በግብፅ ሂሮግላይፍስ ጽሑፎች ላይ ይታያል። የፍላሚንጎ መልክ በጣም እንግዳና የሚያስደንቅ በመሆኑ ግብፃውያን ራ የተባለው አምላካቸው ምስል እንደሆነ ያምኑ ነበር። ጎባጣና ቀጭን የሆነው አንገቱ፣ ቀጭንና ግርማ ሞገስ ያለው እግሩ በጥንታዊ የዋሻ ሥዕሎች ላይ ተስሎ ተገኝቷል።

ባሁኑ ጊዜ አራት የፍላሚንጎ ዝርያዎች በአፍሪካ፣ በካሪቢያን ደሴቶች፣ በዩሮኤዥያ እና በደቡብ አሜሪካ አካባቢዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ ዝርያዎች በመጠን የሚያንሰው ትንሹ ፍላሚንጎ ይባላል። ቀላ ያለ ላባና ደማቅ ቀይ እግሮች ሲኖሩት በጣም የሚያምር ቀለም አለው። ትልቁ ፍላሚንጎ ከትንሹ ፍላሚንጎ በእጥፍ የሚበልጥ ሲሆን ቁመቱ እስከ 140 ሴንቲ ሜትር ይደርሳል። የሁሉም ፍላሚንጎዎች የጋራ ባሕርይ መሐሉ ላይ ጎበጥ ብሎ ወደታች የሚጎነበሰውና በጣም የሚያምር ቅርጽ ያለው አፋቸው ነው።

ይህ ወፍ ለመብረር በሚነሳበት ጊዜ ክንፎቹን እያራገበ በቀልጣፋ እግሮቹ ሲሮጥ በአየር ላይ እንዲወነጨፍ የሚያስችለውን ኃይል ያገኛል። ረዥም አንገቱንና ራሱን ከፊት ለፊት ቀጥ አድርጎና እግሮቹን ከኋላ አስከትሎ በአየሩ ላይ ይበራል። በታላቁ የአፍሪካ ስምጥ ሸለቆ አራት ሚልዮን የሚያክሉ ፍላሚንጎዎች እንደሚኖሩ ይገመታል።

አቅመ ደካማ የሚመስል ወፍና አስቸጋሪ የሆነ አካባቢ

በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ከሚኖሩት ፍላሚንጎዎች መካከል አብዛኞቹ የሚኖሩት በዓይነታቸው ልዩ በሆኑ ብዙ ሶዳ ባላቸው ሐይቆች ነው። ሐይቁ ብዙ ሶዲየም ካርቦኔት ያለው በመሆኑ በእጅ ሲነካ እንደዘይት የሚያሙለጨልጭ ከመሆኑም በላይ ቆዳ ላይ ሲያርፍ ይቆጠቁጣል። በስምጥ ሸለቆ የሶዳ ሐይቆቹ ሙቀት እስከ 65 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሊደርስ ይችላል። ከሐይቁ የሚወጣው የድኝና የጨው ሽታ ሞቃቱን አየር አልፎ ይሰነፍጣል። በውኃው ውስጥ ያሉት ጨዋማ ኬሚካሎች በጣም ብዙ በመሆናቸው ምክንያት በባሕሩ ዳርቻዎች ላይ ደረቅና ቅርፊት የመሰለ ነጭ ነገር ይታያል።

እንዲህ ባለው ጨዋማ ባሕር ሊኖሩ የሚችሉ ፍጥረታት በጣም ጥቂት ናቸው። ቢሆንም በማይክሮስኮፕ ብቻ ሊታዩ የሚችሉ ሰማያዊ አረንጓዴ ቀለም ያላቸው አልጌዎች ይኖሩበታል። በጣም የሚሞቀው የዚህ አካባቢ ፀሐይ ጨዋማውን ውኃ ስለሚያሞቀው ለአልጌዎቹ እድገት በጣም አመቺ የሆነ ሁኔታ ይፈጠራል። አልጌዎቹ በጣም ከመብዛታቸው የተነሳ የሐይቁ ቀለም ወደ አረንጓዴነት ይለወጣል። እነዚህ የሶዳ ሐይቆች በሚያምር የአንገት ሐብል ላይ እንደተተከሉ አረንጓዴ ፈርጦች በረዥሙ ስምጥ ሸለቆ የሚገኙትን ረባዳ ቦታዎችና ተራራዎች አስጊጠዋል።

እንደ ፍላሚንጎ ያለ አቅመ ደካማ የሚመስል ፍጥረት እንዲህ ባለው የማይመችና አስቸጋሪ የሆነ አካባቢ ሊኖር መቻሉ በጣም የሚያስደንቅ ነው። ቢሆንም ፍላሚንጎዎቹ ተመችቷቸዋል። እግሮቻቸው ከሲታ ቢሆኑም ጨዋማ የሆነው ባሕር አይደፍራቸውም። የሸረሪት ድር የመሰሉት እግሮቻቸው ረግረጋማ በሆነው የባሕር ዳርቻ ውስጥ እንዳይሰምጡ ይረዳቸዋል። በተለይ ትንሹ ፍላሚንጎ በዚህ አስቸጋሪ የሆነ አካባቢ ለመኖር የሚያስችል አፈጣጠር አለው። በአፉ ላይ ከባሕሩ ወለል ከ5 እስከ 7 ሴንቲ ሜትር ድረስ ጠልቆ በሚገኘው አካባቢ በብዛት የሚገኙትን ጥቃቅን ነፍሳት ከውኃው ለይቶ የሚመጥ ማጣሪያ አለው። ፍላሚንጎ በሚመገብበት ጊዜ ታችኛውን የአፉን ክፍል ወደ ላይ ያዞርና ከባሕሩ ወለል ትንሽ ገባ አድርጎ ያቆያል። ከዚያም ውኃውን በምላሱ ይመጥና ጥቃቅኖቹን ነፍሳት አጣርቶ በሚያስቀረው ማጣሪያ በኩል እንዲወጣ ያደርጋል።

አስደናቂ የሆነ የመራባት ሥርዓት

የማለዳው ፀሐይ አረንጓዴ በሆነው ሐይቅ ላይ ሲወጣ ትልቅ መጋረጃ የተገለጠ ይመስላል። ወርቃማው የፀሐይ ብርሃን በባሕሩ ላይ እንደ እሳት ነበልባል የሚርመሰመሱ ፍላሚንጎዎችን ያሳያል። እጅብ ብለው ይታያሉ። የሚታዩት አእዋፍ አንገቶቻቸውን ወደላይ ቀጥ አድርገው አፋቸውን ከወዲያ ወዲህ እያወዛወዙ በቡድን በቡድን ተሰልፈዋል።

ሠልፈኞቹ አእዋፍ በተቃራኒ አቅጣጫ በሚተላለፉበት ጊዜ በላባቸው ላይ የሚያርፈው የፀሐይ ብርሃን የሚፈጥረው ነጸብራቅ በጣም አምሮ ይታያል። ወፎቹ ዘለል ዘለል እያሉ ክንፎቻቸውን ይዘረጉና ደማቅ ቀይ ቀለም ያለውን ላባቸውን ያሳያሉ። አንጸባራቂ ቀለማቸውን እያሳዩ ባሕሩ ላይ እየሮጡ በአየር ላይ ለመንሳፈፍ ይሞክሩና ተመልሰው ያርፋሉ። ተመልሰው እንደገና ያንኑ እንቅስቃሴ ይደግማሉ። ፍላሚንጎዎቹ በጣም እጅብ ስላሉ ሁሉም በአንድ ጊዜ ተነስተው መብረር ስለማይችሉ ከዳር ያሉት ወፎች በረው እስኪያልቁ ድረስ የመሐለኞቹ ይጠብቃሉ። እያሽካኩና እየተጯጯሁ ጆሮ የሚበጥስ ውካታና ጫጫታ ይፈጥራሉ።

ከዚያም በድንገት ጨለማን ተገን አድርገው ብድግ ይሉና አንድ ላይ መብረር ይጀምራሉ። ቀጥ ያለ ረዥም መስመር ወይም የቪ ቅርጽ ሠርተው ጎጆአቸውን ለመሥራትና ልጆቻቸውን ለማሳደግ ወደሚመቻቸው የሶዳ ሐይቅ ለመድረስ በመቶ ኪሎ ሜትሮች የሚቆጠር ጉዞ ያደርጋሉ። የሚያስደንቀው ይህ ጉዞ የሚደረግበት ጊዜ በሌላ ስምጥ ሸለቆ የሶዳ ሐይቆች የሚኖሩት ፍላሚንጎዎች ጉዞ ከሚያደርጉበት ጊዜ ጋር አንድ መሆኑ ነው።

ከአስቀያሚነት ወደ ቁንጅና

ፍላሚንጎዎች ጎጆአቸውን ለመሥራት የሚመርጡት ራቅ ያሉና ሰው ሊደርስባቸው የማይችሉ አካባቢዎችን ነው። የቦታው ገለልተኛ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም እንቁላላቸውን ሲቀፈቅፉና ጎጆአቸውን ሲሠሩ የሚረብሻቸው ነገር እንዲኖር አይፈልጉም። ወላጆቹ አእዋፍ ከተረበሹ እንቁላላቸውን እዚያው ትተው ይሄዱና ዳግመኛ ሳይመለሱ ይቀራሉ።

እንቁላል ለመቀፍቀፍ የሚዘጋጁት ወፎች ለሥራ ይጣደፋሉ። ቤታቸውን ለመሥራት ይሯሯጣሉ። ረዥሙን አንገታቸውን ደፋ ቀና እያደረጉ ጭቃና የወፍ ኩስ እያመጡ በላባዎቻቸው የሠሩትን 40 ሴንቲ ሜትር ያህል ከፍታ ያለው ጎጆ ይመርጋሉ። በጎጆው አናት ላይ የሚቀፈቀፈውን ብቸኛ እንቁላል ከጨዋማው ውኃ የሚጠብቅ ትንሽ ጉድጓድ ይሠራል። ብዙም ሳይቆይ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ጫጩቶች ይፈለፈላሉ። ወላጆቹ ወፎች ብዙ ሆነው ጎጆዎቹ ወደሚገኙበት ቦታ እየተመላለሱ አፋቸውን ከፍተው የሚጠብቋቸውን ወፎች ይመግባሉ።

ጫጩቶቹ በእግራቸው ለመሄድ ሲደርሱ ወላጆቹ ወፎች በድንገት ልጆቻቸውን ይተዉና ሰማያዊ አረንጓዴ አልጌዎች በብዛት ወደሚገኙበት ወደ ሌላው የሐይቅ ክፍል ይበራሉ። እዚህም ጫጩቶቻቸው ሳያስቸግሯቸው በቂ ምግብ ተመግበው ጉልበታቸውን ለማደስ ይችላሉ። የጫጩቶቹ መንጋ በአካባቢው በቀሩ ጥቂት ወላጅ ወፎች ወደ አንድ አካባቢ ይሰበሰባሉ። እነዚህ ረባሽ የሆኑ ወጣት ወፎች በሞግዚቶቹ ወፎች እየተነዱ ሐይቁን ያቋርጡና ከወላጆቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ይደረጋል። የሚያስደንቀው በዚህ ሁሉ ትርምስ ወላጆቹ ወፎች የየራሳቸውን ጫጩቶች ለይተው ለማወቅ መቻላቸውና እንደገና እየተንከባከቡ ማሳደጋቸው ነው።

ወጣቶቹ ጫጩቶች ወልካፎች ከመሆናቸውም በላይ መልካቸው ከሚያምሩት ወላጆቻቸው ጋር ፈጽሞ አይመሳሰልም። እግሮቻቸውና አንገታቸው አጭር፣ አፋቸው ቀጥ ያለና የላባቸውም ቀለም ነጭ ነው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አጫጭር እግሮቻቸው ማደግ፣ አንገታቸው መርዘምና መጉበጥ፣ አፋቸው ጎንበስ ማለት ይጀምርና የፍላሚንጎዎች መለያ መልክ የሆነውን ጎበጥ ያለ ቅርጽ ይይዛል። ብዙም የማያምር ቅርጽ ያላቸው ጫጩቶች እሳት የሚመስል ላባ ያላቸው የሚያምሩ ፍላሚንጎዎች እስኪሆኑ ድረስ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት ሊፈጅ ይችላል። በዚህ ጊዜ ከአንድ የኑሮ ጓደኛ ጋር ይጣመሩና የስምጥ ሸለቆን የሶዳ ሐይቆች ከሚያስውቡት ቀላ ያሉ የፍላሚንጎ ሠራዊቶች ጋር መኖር ይጀምራሉ።

የፍላሚንጎዎች ግርማና ውበት አስደናቂ ለሆነው የፈጣሪ አሠራር አንድ ምሳሌ ይሆናል። እነዚህን አስደናቂ ፍጥረታት በሚኖሩበት አካባቢ ለማየት መቻል ለዓይናችንም ሆነ ለጆሯችን ትልቅ ደስታ ይሰጣል። ከዚህ ይበልጥ ግን ድንቅ ለሆነው ፈጣሪያቸው ለይሖዋ አምላክ ያለንን አድናቆትና ፍቅር ከፍ ያደርግልናል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትላልቆቹ ፍላሚንጎዎች

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትናንሾቹ ፍላሚንጎዎች

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወጣቶቹ ጫጩቶች በጣም ከሚያምሩት ወላጆቻቸው ጋር ብዙም አይመሳሰሉም