በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሆሎኮስት እልቂት ዳግም ይከሰት ይሆን?

የሆሎኮስት እልቂት ዳግም ይከሰት ይሆን?

የሆሎኮስት እልቂት ዳግም ይከሰት ይሆን?

ስዊድን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ የ48 መንግሥታት መሪዎችና ተወካዮች የሆሎኮስት እልቂትን በተመለከተ ከጥር 26-28, 2000 በተካሄደው የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ ፎረም ላይ ለመገኘት በስዊድን ዋና ከተማ ተሰባስበው ነበር። ከመድረክ የቀረቡት አንዳንዶቹ ንግግሮች የዓለም መሪዎች የናዚ አገዛዝ እንደገና ሊያንሰራራ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለባቸው ያመላከቱ ነበሩ። የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ኤሁድ ባራክ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “ይህ ኮንፈረንስ ማንኛውም ሰው በየትኛውም የምድር ክፍል ክፋትንና ነፍስ ግድያን የሚያስፋፋንና በሰው ልጆች መካከል በሃይማኖት፣ በዘር ወይም በቀለም ልዩነት የሚያደርግን መንግሥት መታገስ እንደሌለበት ዓለም አቀፋዊ መልእክት ያስተላልፋል።”

አይሁዶችን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ አይደለም

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብዙ ሰዎች “ሆሎኮስት” የሚለውን ቃል የሚያዛምዱት ከአይሁዶች ጋር ብቻ ነው። ይሁን እንጂ የሆሎኮስት ሰለባ የሆኑ ሌሎች ሰዎችም አሉ። ፎረሙ በተካሄደበት ወቅት በሆሎኮስት ያለቁ አይሁዶችን ለማሰብ በስቶክሆልም በሚገኘው በታላቁ ምኩራብ በተዘጋጀው ይፋዊ ክብረ በዓል ላይ የስዊድኑ ጠቅላይ ሚንስትር ሕዝቡ ስለ ሆሎኮስት ያለውን ግንዛቤ ያሰፋ ዘንድ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ቤተ መዛግብት በሙሉ እንዲከፈቱ የሚያደርግ አንድ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ሐሳብ አቅርበዋል። “በሮማ [ጂፕሲዎች] ላይ ስለደረሰው እልቂት፣ በአካል ጉዳተኞች ላይ ስለተካሄደው የጅምላ ጭፍጨፋና በግብረ ሰዶማውያን፣ በተቃዋሚዎችና በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስለደረሰው ስደትና ስለተፈጸመው ነፍስ ግድያ ማወቅ ይኖርብናል” ብለዋል።

የስዊድን መንግሥት ስለ ሆሎኮስት የሚናገር ለልጆቻችሁ ንገሯቸው የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ ያወጣ ሲሆን መጽሐፉ በመላ አገሪቱ ልጆች ላሏቸው ቤተሰቦች ሁሉ በነፃ ታድሏል። ይህ ጽሑፍ የይሖዋ ምሥክሮች “ለሂትለርና ለናዚ ጀርመን ታማኝ መሆናቸውን መሐላ በመፈጸም እንዲያረጋግጡ የቀረበላቸውን ጥያቄ አልተቀበሉም። ታማኝነታቸውን በሚገልጽ ሰነድ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸው ብቻ ስደቱን ያስቆምላቸው የነበረ ቢሆንም ይህን ለማድረግ የመረጡት በጣም ጥቂቶች መሆናቸው የሚያስገርም ነበር” ሲል ይገልጻል።

ሆሎኮስትና የይሖዋ ምሥክሮች

በ1933 በጀርመን ወደ 25, 000 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። በሺህ የሚቆጠሩት መጀመሪያ ላይ ወደ ናዚ ካምፖችና ወኅኒ ቤቶች ከተወረወሩት ሰዎች መካከል ይገኙበታል። ክርስቲያኖች እንደመሆናቸው መጠን ከየትኛውም ዓይነት ፖለቲካዊና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ገለልተኞች መሆናቸውን በግልጽ አሳውቀዋል። ሃይል ሂትለር አላሉም። የናዚን የዘረኝነት ርዕዮተ ዓለም ለመቀበልም ሆነ በሂትለር ፖለቲካዊና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ ለማድረግ ፈቃደኞች አልነበሩም። ወደ 2, 000 የሚጠጉ ምሥክሮች የሞቱ ሲሆን ከ350 በላይ የሚሆኑት ሕይወታቸውን ያጡት የሞት ቅጣት ተበይኖባቸው ነው።

ከዚህም በላይ የይሖዋ ምሥክሮች እስረኞች አይሁዶችንና ሌሎችን ጨምሮ አብረዋቸው የታሠሩት እስረኞች መጽናት እንዲችሉ ይረዷቸው ነበር። ይህን ያደርጉ የነበረው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተስፋ በልባቸው ውስጥ በመትከልና ለታመሙትና ለደከሙት በእጃቸው ላይ የቀረችውን ቁራሽ ዳቦ ሳይቀር በማካፈል ነበር። ናዚ ስደት ያደርስባቸው በነበሩት የመጀመሪያ ዓመታት ማጎሪያ ካምፖች መቋቋማቸውን የሚጠቁምና በካምፖቹ ውስጥ የሚፈጸመውን ሁኔታ የሚገልጽ መረጃ በድብቅ ይልኩ ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በዓለም ዙሪያ በሚሠራጩት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! የተሰኙ መጽሔቶቻቸው ላይ ናዚ ስለፈጸማቸው አሰቃቂ ድርጊቶች የሚያወሱና በሕይወት የተረፉትን ሰዎች ታሪክ የያዙ በርካታ ጽሑፎች አውጥተዋል።

በሆሎኮስት ጉዳይ ላይ ለመወያየት ስብሰባ በተቀመጠው የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ ፎረም ላይ የተገኙት ልዑካን የናዚ ርዕዮተ ዓለም እንደገና ሊያንሰራራ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው በግልጽ ተንጸባርቋል። በእስራኤል በዘመናዊ አይሁዶች ተቋም የሆሎኮስት ጥናቶች ዓለም አቀፍ ማዕከል ዲሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ይሁዳ ባወር ሁኔታውን እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል:- “ከዚህ ቀደም እንደደረሰ ሁሉ አሁንም ዳግመኛ ሊደርስ ይችላል። በቀድሞው መልክ ላይሆን ይችላል፤ ድርጊቱን የሚፈጽሙትም ሆነ የሚፈጸምባቸው ሰዎችም የግድ እነዚያው ሰዎች ላይሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ማንኛውም ሰው በማንኛውም ሰው ላይ ሊፈጽመው ይችላል። በዚያን ጊዜ እንግዳ ነገር ነበር፤ አሁን ግን እንግዳ ነገር አይደለም።”

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፐርፕል ትሪያንግል በካምፖቹ ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች መለያ ሆኖ አገልግሏል

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

1. ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ የሆነው ጁሊየስ ኤንግልሃርት ነሐሴ 14, 1944 ላይ በብራንደንበርግ በናዚዎች ተገድሏል

2. በ1945 ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች ከሳክሰንሃውዘን ተለቅቀው ወደ ቤታቸው ሲያቀኑ

3. ከሕፃን ሴት ልጅዋ ተነጥላ ለሦስት ዓመት ገደማ የታሠረች ኤልሳ አብት የተባለች ምሥክር

[ምንጭ]

Nordrhein-Westfälisches Hauptstaatsarchiv, Düsseldorf

[በገጽ 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በሕይወት የተረፉ ምሥክሮች የተናገሩትን ታሪክ የያዙ ቪዲዮዎች