በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምግብ አለርጂ እና የምግብ አለመስማማት—ልዩነታቸው ምንድን ነው?

የምግብ አለርጂ እና የምግብ አለመስማማት—ልዩነታቸው ምንድን ነው?

ኤመሊ፦ “ጭንቅ ስላለኝ ሹካዬን አስቀመጥኩ። አፌ ውስጥ የማሳከክ ስሜት ተሰማኝ፤ ምላሴም ማበጥ ጀመረ። ከዚያም አዞረኝ፤ እንዲሁም መተንፈስ አቃተኝ። የእጆቼና የአንገቴ ቆዳ ተጉረበረበ። ጭንቀቴን አፍኜ ለመያዝ ብሞክርም ወዲያው ወደ ሆስፒታል መሄድ እንዳለብኝ ተረዳሁ!”

ለአብዛኞቹ ሰዎች ምግብ መመገብ አስደሳች ነገር ነው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ምግቦችን እንደ “ጠላት” አድርገው ለመመልከት የተገደዱ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ቀደም ሲል እንደተጠቀሰችው እንደ ኤመሊ በምግብ አለርጂ ይሠቃያሉ። ኤመሊ ያጋጠማት አለርጂ አናፊላክሲስ ተብሎ የሚጠራ በጣም አደገኛ ሁኔታ ነው። ደግነቱ አብዛኞቹ የምግብ አለርጂዎች የዚህን ያህል አስጊ አይደሉም።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የምግብ አለርጂና የምግብ አለመስማማት እየተስፋፋ መጥቷል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የምግብ አለርጂ እንዳለባቸው ከሚናገሩት ሰዎች መካከል ችግሩ እንዳለባቸው በሕክምና የተረጋገጠላቸው ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።

የምግብ አለርጂ ምንድን ነው?

በዶክተር ጄኒፈር ሽናይደር ቻፈን የሚመራ አንድ የሳይንስ ሊቃውንት ቡድን ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን ላይ ባሳተመው ዘገባ መሠረት “የምግብ አለርጂ በዓለም ዙሪያ ተቀባይነት ያገኘ ፍቺ የለውም።” ሆኖም አለርጂ በዋነኝነት እንዲቀሰቀስ የሚያደርጉት የሰውነታችን በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት እንደሆኑ አብዛኞቹ ባለሙያዎች ያምናሉ።

አንድ ምግብ አለርጂ እንዲሆንብን የሚያደርገው ሰውነታችን በዚያ ምግብ ውስጥ ያሉትን ፕሮቲኖች የሚያስተናግድበት መንገድ ነው። የሰውነታችን በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት በስህተት አንድ ፕሮቲን ጎጂ እንደሆነ አድርገው ይፈርጃሉ። በመሆኑም ይህ ፕሮቲን ወደ ሰውነታችን ሲገባ የሰውነታችን በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ኢሚዩኖግሎቡሊን ኢ (IgE) ተብሎ የሚታወቅ ፀረ እንግዳ አካል በመፍጠር እንደ ወራሪ የቆጠሩት ይህ እንግዳ አካል በሰውነታችን ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ይከላከላሉ። ግለሰቡ ይህ ፕሮቲን ያለበትን ምግብ እንደገና ሲመገብ ቀደም ሲል የተመረቱት ፀረ እንግዳ አካላት ሂስታሚንን ጨምሮ ሌሎች ኬሚካሎች በሰውነት ውስጥ እንዲለቀቁ ሊያደርጉ ይችላሉ።

ሂስታሚን ሰውነታችን በሽታን መከላከል እንዲችል ጠቃሚ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ይሁን እንጂ ምክንያቱ በግልጽ በማይታወቅ ሁኔታ የኢሚዩኖግሎቡሊን ኢ ፀረ እንግዳ አካላት መኖርና የሂስታሚን መለቀቅ በምግብ ውስጥ የሚገኝ አንድ የፕሮቲን ዓይነት ሰውነታቸውን የሚያስቆጣው ሰዎች የምግብ አለርጂ ምልክቶች እንዲታዩባቸው ያደርጋል።

ከዚህ በፊት በልተህ የማታውቀውን አንድ ምግብ ስትበላ ምንም የአለርጂ ምልክት ሳያጋጥምህ በሚቀጥለው ጊዜ ግን ያንኑ ምግብ ስትመገብ የአለርጂ ችግር የሚያጋጥምህ ለዚህ ነው።

የምግብ አለመስማማት ምንድን ነው?

እንደ ምግብ አለርጂ ሁሉ የምግብ አለመስማማትም አንድ ምግብ ሰውነታችንን በመረበሹ ምክንያት የሚከሰት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በሰውነት የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ከሚቀሰቀሰው የምግብ አለርጂ በተለየ የምግብ አለመስማማት የሚከሰተው ምግብ የሚፈጭባቸው የሰውነት ክፍሎች አንድን ምግብ በሚያስተናግዱበት መንገድ የተነሳ ነው፤  በመሆኑም ከፀረ እንግዳ አካላት ጋር ግንኙነት የለውም። አንድ ሰው ምግብ አልፈጭ የሚለው በሰውነቱ ውስጥ ምግቡን ለመፍጨት የሚያስፈልጉ ኢንዛይሞች በማነሳቸው ወይም በምግቡ ውስጥ ያሉት ኬሚካሎች ለመፍጨት አስቸጋሪ በመሆናቸው የተነሳ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የላክቶስ አለመስማማት የሚከሰተው የሆድ ዕቃችን፣ በወተት ውስጥ የሚገኙትን የስኳር ዓይነቶች ለመፍጨት የሚያስፈልጉትን ኢንዛይሞች ማመንጨት ሲያቅተው ነው።

የምግብ አለመስማማት ከፀረ እንግዳ አካላት መመንጨት ጋር ምንም ግንኙነት ስለሌለው ይህ ሁኔታ አንድን ምግብ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንመገብ ሊከሰት ይችላል። የተመገብነው ምግብ መጠን በዚህ ረገድ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል፤ በሌላ አባባል ምግቡን በትንሹ ስንመገብ ምንም ሳይለን በብዛት ስንመገብ ግን ላይስማማን ይችላል። በመሆኑም የምግብ አለመስማማት፣ በጣም ትንሽ የሆነ መጠን ብንበላ እንኳ ለሕይወታችን አስጊ ሊሆን ከሚችለው የምግብ አለርጂ የተለየ ነው።

ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

የምግብ አለርጂ ካጋጠመህ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ምልክቶች ሊታዩብህ ይችላል፦ ማሳከክ፣ የቆዳ መጉረብረብ፣ የጉሮሮ፣ የዓይን፣ ወይም የምላስ ማበጥ፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ ተቅማጥ፣ ሲከፋ ደግሞ የደም ግፊት መውረድ፣ ራስ ማዞር፣ ራስን መሳት አልፎ ተርፎም የልብ ምት መቆም። እንዲያውም አለርጂው በፍጥነት ተባብሶ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል።

በመሠረቱ ማንኛውም ምግብ አለርጂ ሊያስከትል ይችላል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የከፋ አለርጂ እንዲከሰት የሚያደርጉት ጥቂት ምግቦች ይኸውም ወተት፣ እንቁላል፣ ዓሣ፣ የሸርጣን ዝርያዎች፣ ለውዝ፣ አኩሪ አተር፣ የገውዝ ዝርያዎች (ትሪ ነትስ) እና ስንዴ ናቸው። አንድ ሰው በማንኛውም ዕድሜ አለርጂ ሊጀምረው ይችላል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት አለርጂ በዋነኝነት የሚመጣው በዘር ስለሆነ አንድ ሕፃን ከወላጆቹ አንዱ ወይም ሁለቱም አለርጂ ካለባቸው እሱም አለርጂ ሊኖርበት ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ልጆች እያደጉ ሲሄዱ አለርጂው ሊለቃቸው ይችላል።

በጥቅሉ ሲታይ የምግብ አለመስማማት ምልክቶች ከከባድ አለርጂ ምልክቶች ጋር ሲወዳደሩ ያን ያህል የከፉ አይደሉም። ከምግብ አለመስማማት ምልክቶች መካከል የሆድ ህመም፣ የሆድ መነፋት፣ ብስና፣ ቁርጠት፣ ራስ ምታት፣ ሽፍታ፣ የድካም ስሜት ወይም አጠቃላይ የሆነ የሕመም ስሜት ይገኙበታል። የምግብ አለመስማማት በተለያዩ ምግቦች የተነሳ ሊከሰት ይችላል፤ ከእነዚህ መካከል በጣም የተለመዱት ወተትና የወተት ተዋጽኦዎች፣ ስንዴ፣ ግሉተን፣ አልኮልና እርሾ ናቸው።

ምርመራና ሕክምና

የምግብ አለርጂ ወይም የምግብ አለመስማማት ችግር እንዳለብህ ከተሰማህ በዚህ ዘርፍ ወደሠለጠነ የሕክምና ባለሙያ ሄደህ ለመመርመር ልትወስን ትችላለህ። ይህ ችግር እንዳለብህ በራስህ መደምደምና ከአንዳንድ ምግቦች መራቅ ጎጂ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ሰውነትህ አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን እንዳያገኝ ልትነፍገው ትችላለህ።

አለርጂ ሊቀሰቅሱ ከሚችሉ ምግቦች ሙሉ በሙሉ ከመራቅ ውጪ ለከባድ የምግብ አለርጂዎች የሚሰጥ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ ሕክምና የለም። * በሌላ በኩል ደግሞ ያለብህ የምግብ አለርጂ ወይም የምግብ አለመስማማት ችግር ቀለል ያለ ከሆነ አንዳንድ ምግቦችን ባለማዘውተር ወይም በመቀነስ ጠቃሚ ውጤት ማግኘት ትችላለህ። አንዳንድ ጊዜ ግን ችግሩ ያለባቸው ሰዎች እንደ ችግሩ ክብደት ከአንዳንድ ምግቦች፣ ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ ለመራቅ ይገደዳሉ።

ስለዚህ የምግብ አለርጂ ካለብህ ወይም አንዳንድ ምግቦች የማይስማሙህ ከሆነ እንዲህ ያለ ችግር ያለባቸው በርካታ ሰዎች ጥንቃቄ ቢያደርጉም ገንቢና ጣፋጭ የሆኑ የተለያዩ ምግቦችን በመመገብ መደሰት እንደቻሉ ማወቅህ ያጽናናህ ይሆናል።

^ አን.19 አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚመክሩት አብዛኛውን ጊዜ፣ ከባድ የምግብ አለርጂ ያለባቸው ሰዎች ድንገት ችግሩ ቢያጋጥማቸው ራሳቸውን መርፌ መውጋት እንዲችሉ የአድሬናሊን (ኤፒኔፍሪን) መርፌ መያዛቸው ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። አለርጂ ያለባቸው ልጆች አስተማሪዎቻቸው ወይም እንክብካቤ የሚሰጧቸው ሰዎች ስለ ችግራቸው እንዲያውቁ ለማድረግ አለርጂ ስለሚሆኑባቸው ነገሮች የሚናገር ሰነድ እንዲይዙ ወይም እንዲያስሩ አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ።