በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከታሪክ ማኅደራችን

“ሥራው በኃላፊነት ለተሰጣቸው ሁሉ”

“ሥራው በኃላፊነት ለተሰጣቸው ሁሉ”

በውሽንፍርና በዝናብ የተሞሉት ቀናት አልፈው ሰኞ፣ መስከረም 1, 1919 ደስ የሚል ፀሐያማ ቀን ሆኗል። በዚያን ዕለት ከሰዓት በኋላ በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ትልቅ ስብሰባ ተደርጎ ነበር፤ ስብሰባው የተደረገው 2,500 የሚያህል ሰው በሚይዝ አዳራሽ ውስጥ ሲሆን በመክፈቻ ንግግሩ ላይ የተገኙት ልዑካን 1,000 እንኳ አይሞሉም ነበር። አመሻሹ ላይ ግን ተጨማሪ 2,000 ሰዎች በጀልባ፣ በመኪናና በባቡር ተሳፍረው መጡ። ማክሰኞ ዕለት ተሰብሳቢዎቹ በጣም ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ የስብሰባው ቀሪ ፕሮግራም የተካሄደው ከአዳራሹ ውጭ በነበሩ ግርማ በተላበሱ ዛፎች ጥላ ሥር ነበር።

በዛፎቹ ቅጠል ውስጥ አልፎ የሚመጣው የፀሐይ ብርሃን በወንዶቹ ኮት ላይ ሲያርፍ ጥላው ዳንቴል ይመስል ነበር። በአቅራቢያው ካለው የኤሪ ሐይቅ የሚነፍሰው ለስለስ ያለ ነፋስ በሴቶቹ ባርኔጣዎች ላይ ያሉትን ላባዎች ያውለበልባቸው ነበር። አንድ ወንድም ያን ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ከአሮጌው ዓለም ሁካታ ርቆ የሚገኘው ያ ደስ የሚል መናፈሻ በእርግጥም ገነት ይመስል ነበር።”

በተሰብሳቢዎቹ ፊት ላይ የሚነበበው ከፍተኛ ደስታ ግን ከአካባቢውም ውበት ይበልጣል። በአካባቢው የሚታተም አንድ ጋዜጣ እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉም ሲታዩ ሃይማኖተኛ ይመስላሉ፤ ያም ቢሆን በጣም ደስተኞች ናቸው።” የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ከዚያ በፊት የነበሩትን ጥቂት ዓመታት ያሳለፉት በከባድ ፈተና ውስጥ ነው፤ ለምሳሌ፣ በጦርነቱ ወቅት ተቃውሞ አጋጥሟቸዋል፤ በጉባኤዎች ውስጥ ኃይለኛ ክፍፍል ነበር፤ የብሩክሊን ቤቴል ተዘግቷል፤ እንዲሁም 20 ዓመት የተፈረደባቸውን በኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩ ስምንት ወንድሞችን ጨምሮ ብዙዎች ለአምላክ መንግሥት ሲሉ ታስረዋል፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ይህ ሁሉ አልፎ ከክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው ጋር እንደገና መገናኘት በመቻላቸው በጣም ተደስተዋል። *

በእነዚያ አስቸጋሪ ዓመታት ተስፋ ቆርጠውና ግራ ተጋብተው የነበሩ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የስብከቱን ሥራ ትተው ነበር። አብዛኞቹ ግን ከባለሥልጣናት ከፍተኛ ስደት እየደረሰባቸውም በስብከቱ ሥራ በጽናት ለመቀጠል የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል። ለምሳሌ አንድ መርማሪ፣ ምርመራ ያደረገባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም “የአምላክን ቃል እስከ መጨረሻው መስበካቸውን እንደሚቀጥሉ” መናገራቸውን ገልጿል።

በዚያ የፈተና ወቅት ታማኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች “ሁልጊዜ የአብን አመራር ለማግኘት በመጸለይ . . . ጌታ መንገዱን እንዲያሳያቸው ይጠባበቁ ነበር።” አሁን በሴዳር ፖይንት በተደረገው በዚህ አስደሳች ስብሰባ ላይ እንደገና ተገናኙ። አንዲት እህት ‘የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ከፍ የሚያደርጉትና የስብከቱን ሥራ በተደራጀ መልኩ ማከናወን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ’ ያሳስባት እንደነበር ተናግራለች፤ ይህ የብዙዎቹን ስሜት ይገልጻል። ከምንም ነገር በላይ የሚፈልጉት ሥራቸውን እንደ ቀድሞው ማከናወን ነበር!

“GA”—አዲስ መሣሪያ!

በስብሰባው ፕሮግራም፣ በእንኳን ደህና መጣችሁ ካርዶቹና በስብሰባው ቦታ በነበሩት ማስታወቂያዎች ሁሉ ላይ ታትሞ የነበረው “GA” የሚል ምህጻረ ቃል ትርጉም ሳምንቱን በሙሉ ለልዑካኑ እንቆቅልሽ ሆኖባቸው ነበር። በመጨረሻም ዓርብ ዕለት ማለትም “በረዳት ሠራተኞች ቀን” ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ 6,000 ለሚያህሉት ተሰብሳቢዎች የዚህን ምህጻረ ቃል ሚስጥር ገለጠ። “GA” የሚያመለክተው ዘ ጎልደን ኤጅ (ወርቃማው ዘመን) የተባለውን ለአገልግሎት እንዲጠቀሙበት የተዘጋጀ አዲስ መጽሔት ነው። *

ወንድም ራዘርፎርድ እንደ እሱ ቅቡዕ ስለሆኑት ክርስቲያኖች ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ከመከራው ጊዜ ባሻገር ወርቃማ ዘመን የሆነው የመሲሑ ክብራማ ግዛት በእምነት ዓይናቸው ይታያቸዋል። . . . የወርቃማውን ዘመን መምጣት ለዓለም ማወጅ ዋነኛ ኃላፊነታቸው እንዲሁም መብታቸው እንደሆነ ይሰማቸዋል። አምላክ የሰጣቸው ተልእኮ ይህንንም ይጨምራል።”

“የእውነት፣ የተስፋና የጽኑ እምነት መጽሔት” የሆነው ዘ ጎልደን ኤጅ፣ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ በዘመቻ መልክ ኮንትራት በማስገባት እውነትን ለማሰራጨት የሚረዳ አዲስ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። በዚህ ሥራ ለመካፈል የሚፈልግ ማን እንደሆነ ሲጠየቅ ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ ተነስተው ቆሙ። ከዚያም “ጌታ ሆይ፣ ብርሃንህንና እውነትህን ላክ” የሚለውን መዝሙር “በቅንዓትና በደስታ ስሜት” ዘመሩ፤ “ይህን ስሜት ሊረዱት የሚችሉት የኢየሱስን ፈለግ የሚከተሉ ሰዎች ብቻ ናቸው።” ጀጅ ሚልተን ኖሪስ፣ ያንን ወቅት አስመልክቶ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ ‘የዘመርነው በጣም ጮክ ብለን ስለነበር ዛፎቹ እንኳ የሚወዛወዙ ይመስሉ ነበር።’

ስብሰባው እንዳለቀ ልዑካኑ የመጽሔቱን ኮንትራት ወዲያውኑ መግባት ስለፈለጉ ለሰዓታት ተሰልፈው ቆሙ። ብዙዎች እንደ እህት ሜበል ፊልብሪክ ተሰምቷቸዋል፤ እንዲህ ብላ ነበር፦ “የምንሠራው ሥራ በድጋሚ እንዳገኘን ማወቃችን በጣም አስደስቶናል!”

“ሥራው በኃላፊነት ለተሰጣቸው ሁሉ”

ወደ 7,000 የሚጠጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለሥራ ተዘጋጅተው ነበር። ድርጅታዊ አሠራር (እንግሊዝኛ) የሚለው በራሪ ጽሑፍና ሥራው በኃላፊነት ለተሰጣቸው ሁሉ (እንግሊዝኛ) የተሰኘው ቡክሌት የሚከተለውን ዝርዝር ማብራሪያ ይዘው ነበር፦ ሥራውን የሚመራ አዲስ የአገልግሎት ዘርፍ በዋናው መሥሪያ ቤት ተቋቋመ። በጉባኤ ውስጥ የአገልግሎት ኮሚቴ እንዲቋቋምና መመሪያዎችን የሚያስተላልፍ ዳይሬክተር እንዲሾም ተደረገ። የአገልግሎት ክልሎች ከ150 እስከ 200 ቤቶች እንዲይዙ ተደርገው ተዋቀሩ። ወንድሞች ተሞክሮዎች እንዲለዋወጡና የአገልግሎት ሪፖርታቸውን እንዲሰጡ ሐሙስ ምሽት የአገልግሎት ስብሰባ እንዲደረግ ተወሰነ።

“ወደ ቤታችን ስንመለስ ሁላችንም ኮንትራት በማስገባት ዘመቻ ተጠመድን” በማለት ሄርማን ፊልብሪክ ተናግሯል። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በየቦታው ያገኙ ነበር። “ጦርነቱ ከፍተኛ ሐዘን አስከትሎ ስለነበር ሁሉም ሰው ወርቃማ ዘመን ይመጣል የሚለውን ሐሳብ መስማት እንኳ ያስደስተው ነበር” በማለት ቢዩለ ኮቪ ተናግራለች። አርተር ክላውስ “በርካታ ሰዎች ኮንትራት በመግባታቸው መላው ጉባኤ በጣም ተገርሞ ነበር” በማለት ጽፏል። ዘ ጎልደን ኤጅ የተባለው መጽሔት የመጀመሪያው እትም በወጣ በሁለት ወር ውስጥ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ቅጂ የተበረከተ ሲሆን 50,000 ሰዎች ኮንትራት ገብተዋል።

የሐምሌ 1, 1920 መጠበቂያ ግንብ “የመንግሥቱ ወንጌል” የሚል ርዕስ ይዞ ወጣ፤ ከጊዜ በኋላ አሌክሳንደር ሂዩ ማክሚላን ይህን ርዕስ አስመልክቶ “በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለውን ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥሩ አድርጎ የገለጸ ርዕስ ነው” በማለት ተናግሯል። ይህ ርዕስ ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች “መንግሥተ ሰማያት እንደቀረበ ለዓለም ሁሉ እንዲመሠክሩ” አሳስቦ ነበር። በዛሬው ጊዜ የስብከቱን ሥራ በቅንዓት የሚያከናውኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “ሥራው በኃላፊነት ለተሰጣቸው” የክርስቶስ ወንድሞች ድጋፍ እያደረጉ ነው፤ እነዚህ ሰዎች የመሲሐዊውን መንግሥት ወርቃማ ዘመን በጉጉት ይጠባበቃሉ።

^ አን.5 የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) በተሰኘው መጽሐፍ ምዕራፍ 6 ላይ “የፈተና ወቅት (1914-1918)” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.9 ዘ ጎልደን ኤጅ በ1937 ኮንሶሌሽን (መጽናኛ) የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን በ1946 ደግሞ ንቁ! ተብሏል።