ማጥበቅና ድምፅን መለዋወጥ

ማጥበቅና ድምፅን መለዋወጥ

ጥናት 32

ማጥበቅና ድምፅን መለዋወጥ

1, 2. ማጥበቅ ለአንድ ንግግር ምን ጥቅም አለው?

1 ማጥበቅና ድምፅን መለዋወጥ ለንግግሩ ትርጉምና ልዩ ጣዕም ይሰጡታል። እነርሱ ከሌሉ ሐሳቦች የተዛባ ስሜት ይሰጣሉ፤ ንግግሩም የማይስብ ይሆናል። ከሁለቱ ቀላል የሆነው ማጥበቅ ስለሆነ በመጀመሪያ በእርሱ ላይ እናተኩራለን።

2 የማጥበቅ ዓላማ ምን እንደሆነ ሁልጊዜ አስታውስ። ቃልን ወይም ሐሳብን ጎላ በማድረግ ትክክለኛ ስሜቱን ወይም ትርጉሙን ማስተላለፍና ከሌሎች ቃላት ጋር ሲወዳደር የቱን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለአድማጮችህ ለማመልከት ነው። አንዳንድ ጊዜ በኃይል ማጥበቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ላላ ማድረግ ይቻላል፤ ሆኖም በሁለቱም መካከል ትንሽ እየለዋወጡ መናገርም ይቻላል።

3–7. አንድ ተናጋሪ እያጠበቁ የመናገርን ችሎታ እንዴት ለማዳበር እንደሚችል አስረዳ።

3 ሐሳቡን የሚያስተላልፉትን የዓረፍተ ነገሩን ቃላት ማጥበቅ። የት ላይ ማጥበቅ እንዳለብህ ለመወሰን በመሠረቱ መጥበቅ ያለባቸውን ቃላት መለየት ያስፈልጋል። ሐሳቡን የሚያስተላልፉትን ቃላት ማወቅና በተገቢ ቦታ በማጥበቅ በዙሪያቸው ካሉት ቃላት ጎላ ብለው እንዲታዩ ማድረግ ያስፈልጋል። ሐሳቡን የማያስተላልፉት ቃላት ጠበቅ ከተደረጉ ትርጉማቸው ይሰወራል አለዚያም የተዛባ ይሆናል።

4 አብዛኞቹ ሰዎች በየዕለቱ ከሰዎች ጋር በሚያደርጉት ንግግር ለማለት የፈለጉትን ነገር ግልፅ ያደርጋሉ። መስተዋድዶችን እንደ ማጥበቅ የመሰለ የማያስፈልግ ልማድ ከሌለብህ በስተቀር በዚህ በኩል ችግር ሊኖርብህ አይገባም። አለቦታው በማጥበቅ በኩል የጎላ ድክመት የሚታየው ብዙውን ጊዜ ከእነዚህ መጥፎ ልማዶች የተነሣ ነው። ይህ ችግር ካለብህ ይህን ለማሻሻል ተግተህ ጣር። ብዙውን ጊዜ እንደነዚህ ያሉ ልማዶች በአንድ ወይም በሁለት ንግግሮች ሊጠፉ አይችሉም። ስለዚህ በተሳሳቱ ቦታዎች ላይ ጫን ማለትህ ትርጉሙን እስኪያዛባ ድረስ በጣም የጎላ እስካልሆነ ድረስ ምክር ሰጪህ እዚህኛው ነጥብ ላይ ብዙ ጊዜ እንድታጠፋ አያደርግም። ይሁን እንጂ በጣም ኃይለኛና ውጤታማ ንግግር ለመስጠት በትክክለኛው ቦታ ላይ ጫን የማለቱን ልማድ በደንብ እስክታዳብረው ድረስ ለማሻሻል መጣርህን አታቁም።

5 በራስህ አገላለጽ ንግግር ከምትሰጥበት ጊዜ ይልቅ በሕዝብ ፊት ወጥተህ በምታነብበት ጊዜ የማጥበቁን ጉዳይ የበለጠ በንቃት ልታስብበት ያስፈልጋል። ይህ አባባል በጉባኤ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ለሚደረገው የአንቀጾች ንባብ እንደሚሠራው ሁሉ በንግግርህ ወቅት ለምታነባቸው ጥቅሶችም ይሠራል። በንባብ ጊዜ የማጥበቁን ጉዳይ በይበልጥ እንድናስብበት የሚያስፈልግበት ምክንያት ብዙውን ጊዜ ጽሑፉን ያዘጋጀው ሌላ ሰው ስለሚሆን ነው። ስለዚህ ትምህርቱን በጥንቃቄ ማጥናት፣ ሐሳቦቹን አበጥረህ መመርመርና ቃላቱ እስኪዋሃዱህ ድረስ መላልሰህ ማንበብ ያስፈልግሃል።

6 ማጉላት ወይም ማጥበቅ የሚቻለው እንዴት ነው? በርካታ ዘዴዎች ያሉ ሲሆን ብዙ ጊዜ አንድ ላይ በማጣመር ይሠራባቸዋል። እነርሱም የሚከተሉት ናቸው:- ድምፅን ከፍ በማድረግ፣ ስሜትን ጋል በማድረግ፣ ድምፅን በማወፈርና በማቅጠን፣ ቃላትን ሳብ ወይም ጎተት አድርጎ በማንበብ፣ ያነጋገርን ፍጥነት በመጨመር፣ ከቃሉ በፊት ወይም በኋላ (ወይም በሁለቱም ቦታዎች ላይ) ቆም በማለት፣ በሰውነት እንቅስቃሴዎችና ፊታችን ላይ በሚነበበው ስሜት አማካኝነት ነው።

7 በመጀመሪያ ላይ በይበልጥ ማሰብ ያለብህ ቁልፍ የሆኑ ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ ትክክለኛ ቦታ ላይ በትክክለኛው መጠን ስለማጥበቅህ ነው። ስለዚህ ትምህርቱ በንባብ የሚቀርብ ከሆነ በምትዘጋጅበት ጊዜ ቁልፍ የሆኑትን ቃላት አስምርባቸው። አስተዋጽኦ ይዘህ በራስህ አገላለጽ ንግግር የምትሰጥ ከሆነ ደግሞ ሐሳቦቹ በአእምሮህ ውስጥ ወለል ብለው እንዲታዩ አድርግ። በማስታወሻህ ላይ ቁልፍ ቃላት ጨምር፤ በኋላም አጥብቃቸው።

8, 9. ዋና ዋናዎቹ ሐሳቦች ጠበቅ ተደርገው መገለጻቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

8 የንግግሩን ዋና ዋና ሐሳቦች ማጥበቅ። ጫን በማለት ስሜቱን በመጠቆም ረገድ አብዛኛውን ጊዜ ጉድለት የሚታየው እዚህ ላይ ነው። ይህ ችግር ካለ በንግግሩ ውስጥ ዋና ነጥቦችን ለመቋጨት ድምፅ ከፍ የሚደረግባቸው ማሳረጊያዎች አይኖሩም። ከሌላው ነገር ሁሉ ጎላ ብሎ የሚታይ ነገር የለም ማለት ነው። ንግግሩ ከተደመደመ በኋላ ይህ ነጥብ ጎላ ብሎ ነበር በማለት ለማስታወስ በፍጹም አይቻልም። ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ በሚያስችል መንገድ በትክክል ብታዘጋጃቸውም ንግግሩን በምትሰጥበት ጊዜ በተገቢ ቦታ ላይ ካላጠበቅሃቸው መታወስ እስከማይችሉ ድረስ ሊዳከሙ ይችላሉ።

9 ይህንን ችግር ለማስወገድ በመጀመሪያ ትምህርቱን በጥንቃቄ አበጥረህ መመርመር አለብህ። በንግግሩ ውስጥ ከሁሉ የበለጠው ነጥብ ምንድን ነው? ከዚያስ ቀጥሎ በጣም አስፈላጊ የሆነው ነጥብ ምንድን ነው? የንግግሩን ፍሬ ነገር በአንድ ወይም በሁለት ዓረፍተ ነገሮች እንድታስቀምጥ ብትጠየቅ ምን ትል ነበር? ከፍተኛ ነጥቦችን ለመለየት ከሚያስችሉት የተሻሉ ዘዴዎች አንዱ ይህ ነው። እነዚህን ነጥቦች ካወቅሃቸው በኋላ በማስታወሻህ ወይም በሚነበበው ጽሑፍ ላይ ምልክት አድርግባቸው። እነርሱን እየገነባህ ከመጣህ በኋላ በመቋጫው ላይ ስትደርስ ጐላ አድርገህ ለማሳረግ ትችላለህ። የንግግርህ ከፍተኛ ነጥቦች እነዚሁ ናቸው። አስተዋጽኦው በደንብ ተቀነባብሮ ከተዘጋጀና ንግግር በምትሰጥበት ጊዜ ባስፈላጊው ቦታ ላይ በደንብ እያጠበቅህ ብትናገር አድማጮች ዋና ዋናዎቹን ሐሳቦች ማስታወስ ይችላሉ። ንግግር የመስጠቱ ዓላማም ይኸው ነው።

**********

10–12. ድምፅን መለዋወጥ ምን ማለት እንደሆነ ግለጽ።

10 እያጠበቅህ መናገርህ ለአድማጮች ሐሳቡ እንዲገባቸው ይረዳል። ድምፅን በመለዋወጥ የማጥበቁን ዘዴ መቀያየሩ ግን ንግግሩ ለአድማጮች ጣዕም ያለው እንዲሆን ያደርግላቸዋል። በመስክ አገልግሎትና በጉባኤው ውስጥ ንግግር የማቅረብ መብት ስታገኝ ድምፅህን በደንብ እየለዋወጥህ ትናገራለህን?

11 ድምፅን መለዋወጥ ሲባል ቃናን፣ የአነጋገር ፍጥነትንና የድምፅን መጠን ከፍና ዝቅ ማድረግ ማለት ሲሆን ዓላማው የአድማጮች ስሜት እንዳይጠፋ ማድረግና በንግግሩ ሂደት ላይ የደረስክባቸውን ነጥቦችና የምትነካካቸውን ስሜቶች በጉልህ ማሳየት ነው። ድምፅን መለዋወጡ ጥሩ አገልግሎት እንዲሰጥህ ከተፈለገ የንግግሩ ይዘት የሚፈቅደውን የተለያየ አቀራረብ አሟልቶ ማንጸባረቅ አለበት። ድምፅ ወይም ቃና ከፍ የሚደረገው ከፍተኛ አድናቆትን፣ የጋለ ስሜትንና ኃይለኛ ፍላጎትን ለመጠቆም ሲፈለግ ነው። መጠኑ መካከለኛ የሚደረገው መለስተኛ ስሜትን ለመግለፅ ሲሆን ከበድ ያሉ ጉዳዮችንና ትካዜዎችን ስታቀርብ ረገብ ባለ ድምፅና ዝግ ባለ አነጋገር ትጠቀማለህ።

12 ቅጥ የሌለው ስሜት በማሳየት ቲያትር የምትሠራ ለመምሰል አትፈልግም። ንግግራችን የተለያየ ድምቀት ሊኖረው ይገባል እንጂ እንደ ቄሶች እየተመጻደቅን ወይም ሁልጊዜ ኮስተር ብለን መናገር የለብንም። በሌላው በኩል ደግሞ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉትን ስሜታዊ ወንጌላውያን ለመምሰልም አንፈልግም። ለመንግሥቱ መልዕክት ተገቢ ክብርና ክብደት ለመስጠት ያለህ ፍላጎት እንደዚህ ካሉት ክርስቲያናዊ ካልሆኑ የስሜት መግለጫዎች እንድትቆጠብ ሊያደርግህ ይገባል።

13, 14. የድምፅን ኃይል መለዋወጥ ሲባል ምን ማለት ነው?

13 የድምፅን ኃይል መለዋወጥ። ድምፅን ለመለዋወጥ የሚቻልበት ቀላሉ መንገድ ምናልባት የድምፅህን ኃይል ከፍና ዝቅ በማድረግ ሳይሆን አይቀርም። ነጥቦችን ለማሳረግና የንግግርህን ዋና ዋና ነጥቦች ጎላ ለማድረግ የምትጠቀምበት አንዱ መንገድ ይህ ነው። ይሁን እንጂ ድምፅህን ከፍ ማድረግህ ብቻ ነጥቦቹን ሁልጊዜ አያጎላቸውም። እርግጥ አንዳንድ ጊዜ ከሌሎቹ ነጥቦች ደመቅ ብለው እንዲታዩ ሊያደርጋቸው ይችላል፤ በአንፃሩም እነዚያን ነጥቦች ከፍ ባለ ድምፅ ማቅረብህ ያሰብከውን ነገር ሊያከሽፈው ይችላል። ምናልባት እነዚያ ነጥቦች ከግለት ይልቅ በፍቅራዊና በልባዊ ስሜት ቢቀርቡ የተሻለ ይሆናል። ሁኔታው እንዲህ ሲሆን ድምፅህን ዝቅ አድርገው፤ ተመስጦህን ግን ጨምር። ስጋትን ወይም ፍርሃትን የሚገልጽ ሐሳብ ስታቀርብም በዚሁ መንገድ ይሆናል።

14 ድምፅን ለመለዋወጥ የድምፁን ኃይል ከፍና ዝቅ ማድረግ ቢኖርብህም አድማጮችህ ሊሰሙህ እስከማይችሉ ድረስ በሹክሹክታ እንዳትናገር መጠንቀቅ አለብህ። በሌላም በኩል ድምፅህ ጆሮን እስኪያደነቁር ድረስ ቅጥ የለሽ መሆን የለበትም።

15–17. የአነጋገርን ፍጥነት መለዋወጥ የንግግርን ጣዕም ሊጨምር የሚችለው እንዴት ነው?

15 ፍጥነት መለዋወጥ። ጀማሪ ተናጋሪዎች መድረክ ላይ ሲወጡ አብዛኛውን ጊዜ የአነጋገር ፍጥነታቸውን አይለዋውጡም። በዕለታዊ ንግግራችን ወቅት ግን ድምፃችንን እየለዋወጥን እንናገራለን። ምክንያቱም የምንፈልጋቸው ቃላት በአእምሮአችን ውስጥ ልክ ስናስባቸው ወይም ባስፈለጉን ጊዜ ያለምንም ችግር ከተፍ ብለው ስለሚቀርቡልን ነው። መድረክ ላይ የወጣው አዲስ ተናጋሪ ግን ብዙውን ጊዜ ይህን ማድረግ ያስቸግረዋል። የሚናገራቸውን ቃላትና ሐረጎች በከፍተኛ ጥንቃቄ ስለሚያዘጋጅ በንግግሩ ጊዜ ሁሉም ቃላት በአንድ ዓይነት ፍጥነት ይወጣሉ። ከአስተዋጽኦ መናገሩ ይህንን ድክመት ለማረም ይረዳል።

16 የንግግርህ አካሄድ በአመዛኙ መካከለኛ መሆን አለበት። ንዑስ ነጥቦች፣ ትረካዎች፣ አብዛኛዎቹ ምሳሌዎችና የመሳሰሉት ፈጠን ብሎ ለመናገር ይፈቅዱልሃል። ክብደት ያላቸው ነገሮች፣ ማሳመኛ ገለጻዎች፣ ማሳረጊያዎችና ዋና ዋና ነጥቦች ብዙውን ጊዜ ፍጥነትን ዝግ ማድረግን ይጠይቃሉ። አንዳንድ ጊዜ በኃይል ለማጉላት ሲፈለግ ሆን ብለህ ቃላቱን እየሳብህ ወይም እየቆጠርህ ለመናገር ትችላለህ። እንዲያውም ለትንሽ ጊዜ ጨርሶ ቆም ለማለት ትችላለህ። ይህም ፍጥነቱን ፈጽሞ ይለውጠዋል።

17 ጥንቃቄ ስለሚያስፈልጋቸው ነገሮች ጥቂት ምክሮች እንስጥህ። የአነጋገርህ ጥራት እስኪነካ ድረስ ፈጽሞ በጥድፊያ አትናገር። በግልህ ለመለማመድ ግሩም የሆነው አንድ ዘዴ ድምፅ እያወጣህ ሳትደነቃቀፍ በተቻለ ፍጥነት ለማንበብ መሞከር ነው። ጥራት ባለው መንገድ ሳትደነቃቀፍ አንድን አንቀጽ መላልሰህ በማንበብ በየጊዜው ፍጥነትህን ለመጨመር ሞክር። ከዚያ በኋላ ቃላትን ከመሸራረፍ ይልቅ ሳብ እያደረግህ ለማንበብ ሞክር። ቀጥለህም ድምፅህ እንደ ልብ መታዘዝ እስኪችል ድረስ ፍጥነትህን እያቀያየርህ አንብብ። ይህን ልምምድ ካደረግህ በኋላ ንግግር ስትሰጥ ሐሳቡ የሚያስተላልፈውን ስሜት እያየህ የአነጋገር ፍጥነትህን በደመ ነፍስ ከፍና ዝቅ ታደርጋለህ።

18–20. አንድ ተናጋሪ ቃናን ከፍና ዝቅ የማድረግን ችሎታ እንዴት ማዳበር እንደሚችል ግለጽ።

18 ቃናን መለዋወጥ። ድምፅን በመለዋወጥ በኩል የሚያጋጥመው ከሁሉ የሚከብደው ነገር ቃናን መለዋወጥ ሳይሆን አይቀርም። እርግጥ ድምፅን ቀጠን፣ የድምፅንም ኃይል ከፍ በማድረግ ብዙ ጊዜ እንናገራለን። በዚህ መንገድ የፈለግነውን ቃል እናጠብቃለን። ክራር የሚጫወት ሰው አንዳንድ ጊዜ ክሮቹን በኃይል በመምታት ድምፃቸውን እንደሚያጐላው ሁሉ ቃሉም በዚህ መንገድ ጐላ ይላል።

19 ይሁን እንጂ ድምፅን በመለዋወጥ በኩል ከዚህኛው ዘርፍ ሙሉ ጥቅም ለማግኘት ቃናን ከላይ ከተገለጸው በበለጠ ሁኔታ ከፍና ዝቅ ማድረግ ያስፈልግሃል። እስቲ ዘፍጥረት 18:3–8⁠ንና 19:6–9⁠ን ድምፅ እያሰማህ ለማንበብ ሞክር። እነዚህን ጥቅሶች ለማንበብ የሚያስፈልገውን የፍጥነትና የቃና ከፍተኛ ለውጥ አስተውል። ከኃዘንና ከስጋት ይልቅ ከፍተኛ የአድናቆት ስሜትና ግለት ቀጠን ያለ ቃና ይፈልጋሉ። እነዚህ ስሜቶች ባዘጋጀኸው ትምህርት ውስጥ ካሉ በዚሁ መንገድ እንድትገልጻቸው ይፈለጋል።

20 በዚህ ድምፅን የመለዋወጥ ዘርፍ ለሚታየው ድክመት ዋነኛ ከሆኑት ምክንያቶች አንዱ ድምፅን እንደ ልብ ለመለዋወጥ አለመቻል ነው። ችግርህ ይህ ከሆነ ይህን ችግር ለማስወገድ ጣር። በዚህ ጥናት ውስጥ በመጀመሪያው አካባቢ የተጠቆመልህን ሐሳብ በመተግበር ለመለማመድ ሞክር። ሆኖም ለዚህኛው ችግር ፍጥነትን ከፍና ዝቅ ማድረግ ሳይሆን ቃናህን ወፈርና ቀጠን ለማድረግ ሞክር።

21–24. ድምፁ ለሐሳቡ ወይም ለሚገለጸው ስሜት ተስማሚ መሆን ያለበት ለምንድን ነው?

21 ለሐሳቡ ወይም ለስሜቱ የሚስማማ ድምፅ። ስለዚህኛው የንግግር ባሕርይ እስካሁን ድረስ በተመለከትነው ማብራሪያ መሠረት ድምፅን መለዋወጥ የሚያስፈልገው እንዲሁ ደስ ስለሚል ብቻ እንዳልሆነ ተረድተናል። ድምፅህ የምትናገረው ሐሳብ ለሚያንጸባርቀው መንፈስ የሚስማማ መሆን አለበት። እንግዲያው የድምፅ ለውጥ የሚጀምረው ከየት ነው? ንግግር ልትሰጥበት ካዘጋጀኸው አስተዋጽኦ እንደሆነ ግልጽ ነው። ንግግርህ ክርክር ወይም ማሳሰቢያዎችን ብቻ ያካተተ ከሆነ ድምፅን እምብዛም እያለዋወጥህ ንግግሩን ማቅረብ አትችልም። ስለዚህ የንግግሩን አስተዋጽኦ አዘጋጅተህ ከጨረስህ በኋላ አንድ በአንድ መርምረው። አስተዋጽኦው አስፈላጊ የሆኑትን ቅመሞች ሁሉና ትርጉም ያላቸውን ነጥቦች ያካተተ መሆኑን እርግጠኛ ሁን።

22 አንዳንድ ጊዜ ግን በንግግርህ መሀል የፍጥነት ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። ንግግርህ ችክ ያለ መስሎ ሊሰማህ ይችላል። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላለህ? በራስ አገላለጽ ንግግር ማቅረብ የሚሻልበትን ሌላውን መንገድ እዚህም ላይ ማየት ይቻላል። ንግግርህን እያቀረብክ ሳለ በመሀሉ መልኩን ልትለውጥ ትችላለህ። እንዴት? አንደኛው ዘዴ መናገርህን አቁመህ መጽሐፍ ቅዱስን በመግለጥ ጥቅስ ማንበብ መጀመር ነው። ወይም ሐተታውን ወደ ጥያቄ ልትለውጠውና ለማጥበቅ ያህል ትንሽ ቆም ልትል ትችላለህ። ምናልባትም አንድ ምሳሌ ጣልቃ በማስገባት በአስተዋጽኦህ ውስጥ ያለውን የማሳመኛ ነጥብ ለየት ባለ መንገድ ለማቅረብ ትችል ይሆናል።

23 እርግጥ በንግግሩ መሀል እነዚህን ዘዴዎች ማስገባት የሚችሉት ብዙ ልምድ ያላቸው ተናጋሪዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ክፍልህን በቅድሚያ በምትዘጋጅበት ጊዜ እነዚህን ሐሳቦች ልትጠቀምባቸው ትችላለህ።

24 ድምፅን መለዋወጥ የንግግር ቅመም ነው እየተባለ ይነገራል። ትክክለኛውን ዓይነት ድምፅ ከተጠቀምክና መጠኑም ልክ ከሆነ ትምህርቱ ከነሙሉ ጣዕሙ ይቀርባል፤ አድማጮችህም በደንብ እያጣጣሙ ይሰሙታል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]