በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መነበብ የሚገባው መጽሐፍ

መነበብ የሚገባው መጽሐፍ

መነበብ የሚገባው መጽሐፍ

አንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር በግልጽ ላነጋገረቻቸው ለአንዲት ሴት “መጽሐፍ ቅዱስ እኮ በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው መጽሐፍ አይደለም” ይላሉ።

ሴቲቱም መልሳ “መጽሐፍ ቅዱስን አንብበውት ያውቃሉ?” ትላቸዋለች።

ፕሮፌሰሩ በጥያቄው ደንገጥ ቢሉም አንብበውት የማያውቁ መሆናቸውን ለማመን ተገድደዋል።

“ታዲያ አንብበው ስለማያውቁት መጽሐፍ እንዴት እንዲህ እርግጠኛ ሆነው ሊናገሩ ይችላሉ?” አለቻቸው።

አነጋገሯ በጣም ትክክል ነበር። ሰውዬውም አስቀድመው መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ከዚያ በኋላ አስተያየት ለመስጠት ወሰኑ።

ስልሳ ስድስት መጻሕፍትን አንድ ላይ አጣምሮ የያዘው መጽሐፍ ቅዱስ “በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ተጽእኖ ያሳደረ የመጻሕፍት ስብስብ” እንደሆነ ተነግሯል።1 በእርግጥም ታላላቅ ናቸው በሚባሉት በአንዳንዶቹ የዓለም የሥነ ጥበብ፣ የሥነ ጽሑፍና የሙዚቃ ሥራዎች ላይ ትልቅ ተጽእኖ አሳድሯል። በሕግ አቀራረጽ ላይም በቀላሉ የማይገመት ተጽእኖ አሳድሯል። በሥነ ጽሑፍነቱም ከፍተኛ ቦታ የተሰጠው ሲሆን በርካታ ምሁራን ታላቅ ከበሬታ የሰጡት መጽሐፍ ነው። በተለይ በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ አስከትሏል። ከአንባቢዎቹ መካከል ብዙዎቹ በጣም አስደናቂ የሆነ የታማኝነት ባሕርይ እንዲኖራቸው ያደረገ መጽሐፍ ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ መጽሐፉን ለማንበብ ሲሉ ብቻ ሕይወታቸውን ለሞት እስከመዳረግ ደርሰዋል።

ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ ያላቸው ሰዎችም አሉ። መጽሐፉን ጨርሶ አንብበው የማያውቁ ቢሆኑም የራሳቸውን አስተያየት ከመስጠት ወደኋላ አይሉም። በሥነ ጽሑፍነቱ ወይም በታሪክ መጽሐፍነቱ ዋጋ ያለው መጽሐፍ እንደሆነ ቢናገሩም በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተጻፈ መጽሐፍ እንዴት በዚህ ዘመናዊ ዓለም ጠቃሚነት ሊኖረው ይችላል? ብለው ያስባሉ። የምንኖረው ዓለም በመረጃ ቴክኖሎጂ በመጠቀበት ዘመን ነው። ስለ ዓለም ሁኔታም ሆነ ስለ ቴክኖሎጂ ውጤቶች የምንፈልገውን መረጃ በቅጽበት ማግኘት እንችላለን። ዘመናዊው ኑሮ ለሚያመጣብን ችግሮች በሙሉ የሚያስፈልገንን “የጠበብቶች” ምክር በቀላሉ ማግኘት እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ለዘመናችን ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መረጃ ሊኖረው ይችላልን?

ይህ ብሮሹር እንደነዚህ ስላሉት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ይሞክራል። አንድ የተወሰነ ሃይማኖታዊ አመለካከት ወይም እምነት በአንተ ላይ ለመጫን ታስቦ የተዘጋጀ ብሮሹር ሳይሆን ይህ በታሪክ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳደረ መጽሐፍ ልትመረምረው የሚገባ መጽሐፍ መሆኑን ለማስገንዘብ ተብሎ የተዘጋጀ ነው። በ1994 የተጠናቀረ አንድ ሪፖርት አንዳንድ አስተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ በምዕራባውያን ባሕል ላይ የተመሠረተ በመሆኑ “ማ​ንኛውም ሰው፣ አማኝ ሆነም አልሆነ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶችና ታሪኮች የማያውቅ ከሆነ በባሕል ረገድ መሐይም ይሆናል” የሚል እምነት አላቸው ሲል ገልጿል።2

ምናልባት በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሰፈረውን ካነበብክ በኋላ፣ አንድ ሰው ሃይማኖተኛ ሆነም አልሆነ፣ ሌላው ቢቀር መጽሐፍ ቅዱስን ሊያነበው ይገባል በሚለው ሐሳብ ትስማማ ይሆናል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“መንፈሳዊ ማስተዋል ላገኝ የቻልኩት አንድ መጽሐፍ በማንበቤ ነው።​—⁠መጽሐፍ? አዎን፣ ጥንታዊና ቀላል፣ ከሰብዓዊ ኃይሎች ቁጥጥር ውጭ እንደሆነው ተፈጥሮ ትልቅ ግምት ያልተሰጠው መጽሐፍ ነው። . . . ይህ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ይባላል።”​—⁠ሃይንሪክ ሃይነ፣ የ19ኛው መቶ ዘመን ጀርመናዊ ደራሲ።3