ሰኔ 3, 2025
ግሪክ

ባለፉት 100 ዓመታት፣ ግሪክ ውስጥ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች የተለያዩ ትላልቅ ስብሰባዎችን አድርገዋል፤ ከእነዚህ አንዱ በ2019 አቴንስ ውስጥ የተካሄደው “ፍቅር ለዘላለም ይኖራል!” የተሰኘው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ነው

ግሪክ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በ2025 ታሪካቸውን ዘከሩ

ግሪክ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በ2025 ታሪካቸውን ዘከሩ

የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመበት ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አንስቶ ግሪክ በይሖዋ ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ቦታ ያላት አገር ናት። በ2025 የይሖዋ ምሥክሮች፣ በዘመናችን ግሪክ ውስጥ ያሳለፉትን ታሪክ መለስ ብለው በማሰብ አንዳንድ ወሳኝ ክንውኖችን ይዘክራሉ።

የዛሬ መቶ ዓመት፦ በግሪክ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች (በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ ነበር) በዘመናችን ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቅ ስብሰባ ያደረጉት በአቴንስ ከሚያዝያ 23 እስከ 26, 1925 ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች የተገኙ ሲሆን 68 ተጠማቂዎች ነበሩ። ከአራት ወራት በኋላ በግሪክ የሚኖሩ ወንድሞቻችን ለመጀመሪያ ጊዜ የፍርድ ቤት ድል ተቀዳጁ። ሃይማኖት ማስቀየርን የሚከለክለውን የአገሪቱን ሕገ መንግሥት መሠረት በማድረግ ፖሊሶች ጽሑፎቻችንን የወረሱ ከመሆኑም ሌላ መንግሥት በስብከት ሥራችን ላይ እገዳ ጥሎ ነበር። ሆኖም ነሐሴ 27 የአቴንስ ፍርድ ቤት ለወንድሞቻችን የፈረደላቸው ሲሆን የመስበክ መብታቸውን አስከበረላቸው። ፍርድ ቤቱ ጽሑፎቻችን ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጩ እንዳልሆኑ እንዲያውም “ለሰው ልጆች የሥነ ምግባር መርሆችን እንደሚያስተምሩ” ገልጿል።

ሚያዝያ 1925 አቴንስ ውስጥ በተደረገው የመጀመሪያው ትልቅ ስብሰባ ላይ ተሰብሳቢዎች የተነሱት ፎቶ

የዛሬ ሃምሳ ዓመት፦ ሰኔ 3, 1975 የግሪክ ብሔራዊ ምክር ቤት የይሖዋ ምሥክሮች እምነት “እውቅና የተሰጠው ሃይማኖት” መሆኑን በይፋ አጸደቀ። ይህ ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት በነበሩት አሥርተ ዓመታት ወንድሞቻችን ብዙ መከራ አሳልፈዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከባድ ስደትና ተቃውሞ አጋጥሟቸዋል፤ የእርስ በርስ ጦርነትና ሁለት አምባገነናዊ አስተዳደሮችም ተፈራርቀውባቸዋል። የ84 ዓመት አረጋዊ የሆኑት እህት ቩላ ካላይትዚ በሁለተኛው አምባገነናዊ አስተዳደር ወቅት በርካታ ፈተናዎች ደርሰውባቸው ነበር። እህት እንዲህ ብለዋል፦ “በዚያን ወቅት ስብሰባ የምናደርገው ጫካ ውስጥ በድብቅ ነበር።” ከጊዜ በኋላ የመንግሥት ለውጥ ተደረገ። ሰኔ 1975 ከተደረገው ውሳኔ ብዙም ሳይቆይ ወንድሞቻችን ግሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አገር አቀፍ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ አዘጋጁ። ከሐምሌ 10 እስከ 13 አቴንስ ውስጥ በሚገኘው አፖሎን ስታዲየም በተደረገው በዚህ ስብሰባ ላይ 19,200 ገደማ ተሰብሳቢዎች የነበሩ ሲሆን 301 ሰዎች ተጠምቀዋል። እህት ቩላ አክለው “በስተ መጨረሻ ነፃነት አግኝተን በይፋ ስንሰበሰብ የተሰማን ደስታ ወደር አልነበረውም። ከደስታዬ የተነሳ እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም!” ብለዋል።

ሐምሌ 1975 ግሪክ ውስጥ የተደረገው የመጀመሪያው አገር አቀፍ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ፣ አቴንስ በሚገኘው አፖሎን ስታዲየም

በዛሬው ጊዜ ግሪክ ውስጥ የሚኖሩት 27,000 ወንድሞችና እህቶች በነፃነት መሰብሰብና የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች ማካፈል በመቻላቸው ደስተኞች ናቸው። ይሖዋ ቅንዓታቸውንና ‘በእምነት ጸንተው ለመቆም’ ያሳዩትን ቁርጠኝነት ስለባረከላቸው እናመሰግነዋለን።—1 ቆሮንቶስ 16:13