በግፍ ለተገደሉት የይሖዋ ምሥክሮች የመታሰቢያ ድንጋይ ቆመላቸው

በግፍ ለተገደሉት የይሖዋ ምሥክሮች የመታሰቢያ ድንጋይ ቆመላቸው

በግፍ ለተገደሉት የይሖዋ ምሥክሮች የመታሰቢያ ድንጋይ ቆመላቸው

መጋቢት 7, 2002 በምዕራብ ሃንጋሪ በምትገኘው በኮርሜንድ ከተማ አንድ የመታሰቢያ ድንጋይ ለሕዝብ እይታ ይፋ ተደረገ። የመታሰቢያ ድንጋዩ የተዘጋጀው ናዚዎች በ1945 የገደሏቸውን ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች ለማስታወስ ነበር።

የመታሰቢያ ድንጋዩ ምሥክሮቹ በሕዝብ ፊት በተገደሉበት በሁንዮዲ ጎዳና በሚገኘው የእሳት አደጋ መከላከያ ዋና መሥሪያ ቤት አጥር ግንብ ላይ ተሰቀለ። የመታሰቢያ ድንጋዩ ‘አንታል ሂዩኒች (1911-1945)፣ ቤርታላን ሳቦ (1921-1945)፣ ያኖሽ ዞንዶር (1923-1945) ለተባሉት በሕሊናቸው ምክንያት በጦርነት አንካፈልም በማለታቸው መጋቢት 1945 ለተገደሉ ክርስቲያኖች’ መታሰቢያ እንዲሆን ተዘጋጅቶ ‘በ2002 ለይሖዋ ምሥክሮች’ የተሰጠ መሆኑን ይገልጻል።

ምሥክሮቹ የተገደሉት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሊያበቃ ሁለት ወር ሲቀረው ነበር። እነዚህ ክርስቲያኖች የተገደሉት ለምን ነበር? ቮሽ ናፕ የተባለው የሃንጋሪ ጋዜጣ እንዲህ ይላል:- “ሂትለር በጀርመን ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ከአይሁዳውያን በተጨማሪ ታማኝ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮችም ስደትና መከራ ይደርስባቸው፣ በማጎሪያ ካምፖች ይታሰሩ እንዲሁም ሃይማኖታዊ እምነታቸውን ካልካዱ ሞት ይፈረድባቸው ነበር። . . . መጋቢት 1945 በምዕራብ ሃንጋሪ ሽብር ነግሦ ነበር። . . . ይህ ሽብር የይሖዋ ምሥክሮችን ከቦታ ቦታ ማጋዝንና መግደልን ይጨምር ነበር።”

የመታሰቢያው ድንጋይ የምርቃት ሥነ ሥርዓት በሁለት የተከፈለ ነበር። የመጀመሪያው ክፍል የተከናወነው ባትዬን ካስተል ተብሎ በሚጠራው ቲያትር ቤት ሲሆን እዚያም ንግግር ከሰጡት ሰዎች መካከል በቡዳፔስት የሆሎኮስት መረጃ ማዕከል ዋና ኃላፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ሳቦች ሲታ፣ በፓርላማው ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች፣ የአናሳ ቡድኖችና የሃይማኖታዊ ጉዳዮች ኮሚቴ አባል የሆኑት ላስሎ ዶናች እንዲሁም አሁን የከተማው ታሪክ ጸሐፊ የሆኑትና በግድያው ወቅት የዓይን ምሥክር የነበሩት ካልማን ኮምያቺ ይገኙበታል። ከዚያም በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት ከ500 በላይ የሚሆኑ ሰዎች የከተማው ከንቲባ የሆኑት ዮዜፍ ሆንፊ የመታሰቢያ ድንጋዩን ለሕዝብ እይታ ይፋ ሲያደርጉ ለመመልከት ከተማውን አቋርጠው ተጓዙ።

ያን ዞንዶር (ያኖሽ ዞንዶር) ከመገደሉ በፊት በጻፈው የስንብት ደብዳቤው ላይ ክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ እንዳያዝኑ በማሳሰብ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ራእይ 2:10 ላይ የሚገኙት ‘እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን’ የሚሉት የዮሐንስ ቃላት አሁንም ድረስ በጭንቅላቴ ውስጥ ያቃጭላሉ። . . . የምገደለው ለእውነት ስል እንጂ ወንጀለኛ ሆኜ ባለመሆኑ የሚያውቁኝ ሁሉ እንዳያዝኑ ንገሯቸው።”

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቤርታላን ሳቦ

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንታል ሂዩኒች

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ያን ዞንዶር