የተቀላጠፈና ጥራት ያለው አነጋገር፤ በውይይት መልክ ማቅረብ
ጥናት 29
የተቀላጠፈና ጥራት ያለው አነጋገር፤ በውይይት መልክ ማቅረብ
1–4. በንግግር የመደነቃቀፍን መንስኤዎችና ምልክቶች ዘርዝር።
1 ንግግር ለመስጠት በአድማጮች ፊት ስትቆም ትክክለኛውን ቃል ለመናገር ድንግርግር ይልብሃልን? ወይም በምታነብበት ጊዜ አንዳንድ ቃላት ላይ ስትደርስ ትደነቃቀፋለህን? ሁኔታህ እንደዚህ ከሆነ በቅልጥፍና በኩል ችግር አለብህ ማለት ነው። አቀላጥፎ የሚናገር ሰው ቃላትን በቀላሉ ያንቆረቁራል። ይህም ሲባል ግን ለሰው ስሜት ምንም ግድ ባለማድረግ እንዲሁ “ማነብነብ” ማለት ግን አይደለም። ቅልጥፍና አፈ ትብ መሆን፣ ለመስማት ደስ የሚል፣ ግርማ ሞገስ ያለውና እንደ ውኃ የፈሰሰ ንግግር ማቅረብ ማለት ነው። ቅልጥፍና ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸው በንግግር ምክር መስጫው ቅጽ ላይ ከተዘረዘሩት ነጥቦች አንዱ ነው።
2 ብዙውን ጊዜ በንግግር ላይ የቅልጥፍና ችግር የሚከሰተው በአእምሮ ውስጥ ነገሮች ሲዘበራረቁ ወይም ትምህርቱን ባለመዘጋጀት ነው። በተጨማሪም የመነጋገሪያ ቃላት እውቀት ውስን ሲሆን ወይም ጥሩ የቃላት
ምርጫ ሳይደረግ ሲቀር የቅልጥፍና ችግር ሊመጣ ይችላል። በንባብ ላይ የቅልጥፍና ችግር የሚታየው ብዙ ጊዜ ጮክ ብሎ ማንበብን ካለመለማመድ የተነሣ ነው። እርግጥ እዚህም ላይ ቢሆን ቃላትን አለማወቁ መደነቃቀፍን ሊያመጣ ወይም ያዝ ሊያደርግ ይችላል። በመስክ አገልግሎት ላይ እነዚህ ነገሮች ተደማምረው ፍርሃትና የእርግጠኝነት እጦት ሲጨመርባቸው የመደነቃቀፍ ችግር ሊያመጡ ይችላሉ። እዚህ ላይ ችግሩ በጣም አሳሳቢ ነው፤ ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ አድማጮችህ ጥለውህ ሊሄዱ ይችላሉ። በመንግሥት አዳራሽ ላይ አድማጮችህ ቃል በቃል ተነሥተው ላይሄዱ ይችላሉ፤ ሆኖም በሐሳብ ሊባዝኑና የተናገርከው ሁሉ በከንቱ ሊቀር ይችላል። ስለዚህ ጉዳዩ በጥሞና የሚታሰብበት ነው። ቅልጥፍና ኮትኩተን ልናዳብረው የሚገባን የንግግር ባሕርይ ነው።3 ብዙ ተናጋሪዎች “እ–እ–” የማለት ወይም በሌሎች መንገዶች ጉትት እያሉ የመናገር መጥፎ ልማድ አላቸው። ምን ያህል ጊዜ ደጋግመህ እንደዚህ እንደምታደርግ የማታውቅ ከሆነ የልምምድ ጊዜ አዘጋጅተህ ሌላ ሰው እንዲከታተልህና እንደዚያ ባደረግህ ቁጥር እርሱም አንተን ተከትሎ እንደዚያ እንዲል ማድረግ ትችላለህ። በውጤቱ ትደነቅ ይሆናል።
4 ሌሎች ሰዎች ሁልጊዜ ወደኋላ እየተንሸራተቱ የመናገር ልማድ አላቸው። አንድ ዓረፍተ ነገር ይጀምሩና አቋርጠው እንደገና ከመጀመሪያው ይነሣሉ። ይህ ዓይነቱ ሰንካላ ልማድ የሚያጠቃህ ከሆነ ከሰዎች ጋር በየዕለቱ በምታደርገው ንግግር ይህን ለማጥፋት ሞክር። ከመናገርህ በፊት ለማሰብና ነገሩን በአእምሮህ ውስጥ አጥርተህ ለማየት ዘወትር ጥረት አድርግ። ከዚያ በኋላ ሳትቆም ወይም መሐል ላይ ሐሳብህን ሳትለውጥ ጠቅላላውን ሐሳብ ተናገረው።
5–10. ቅልጥፍናን ስለ ማሻሻል ምን ምክሮች ተሰጥተዋል?
5 ሌላም ነገር አለ። በቃላት ተጠቅመን ሐሳባችንን መግለጹ ለእኛ እንግዳ ነገር አይደለም። ስለዚህ ለመናገር የፈለግነውን ጉዳይ በትክክል የምናውቅ ከሆነ ቃሎቹ ራሳቸው ይመጣሉ። ስለምትናገራቸው ቃላት ማሰብ አያስፈልግህም። እንዲያውም ለልምምዱ ይረዳህ ዘንድ ሐሳቡ በአእምሮህ ውስጥ ጥርት ብሎ መቀመጡን እያረጋገጥህ ስለምትናገራቸው ቃላት እግረ መንገድህን ብታስብ ጥሩ ይሆናል። ይህን ብታደርግና አእምሮህ በምትናገራቸው ቃላት ላይ ሳይሆን በሐሳቡ ላይ እንዲያተኩር ብታደርግ እነዚያ ቃላት ራሳቸው ይመጣሉ። ሐሳብህንም ልክ በውስጥህ እንደሚሰማህ አድርገህ መግለጽ ትችላለህ። ነገር ግን በሐሳቦች ላይ በማተኮር ፋንታ ስለ ቃላቱ ማሰብ ስትጀምር ወዲያው ንግግርህ ቁርጥ ቁርጥ ማለት ይጀምራል።
6 ቅልጥፍና እንዳይኖርህ የገታህ የቃላት ምርጫህ ውስን መሆኑ ነውን? እንግዲያው የምትጠቀምባቸውን መነጋገሪያ ቃላት ብዛት ለመገንባት ቋሚ ጥናት ማድረግ ይኖርብሃል። በመጠበቂያ ግንብ እና በሌሎቹ የማኅበሩ ጽሑፎች ላይ ለአንተ እንግዳ የሆኑ ቃላት ስታገኝ ዝም ብለህ አትለፋቸው፤ በዕለታዊ የመነጋገሪያ ቃላት ክምችትህ ውስጥ ጨምራቸው።
7 በንባብ ጊዜ መደነቃቀፍ የሚመጣው ከቃላት ጋር ባለመተዋወቅ ስለሆነ ይህ ችግር ካለብህ የተወሰነ ዘዴ ተከትለህ ዘወትር ጮክ እያልክ በማንበብ ብትለማመድ ጥሩ ነው።
8 ይህን ማድረግ የምትችልበት አንዱ መንገድ ከምንባቡ ውስጥ አንድ ወይም ሁለት አንቀጽ መርጠህ ሐሳቡ በደንብ እስኪገባህ ድረስ በልብህ በጥንቃቄ ማንበብ ነው። አንድ ላይ ሲነበቡ ስሜት የሚሰጡ ሐረጎችን ለይ፤ አስፈላጊ ከሆነም ምልክት አድርግባቸው። ከዚያ በኋላ ይኸኛውን ምንባብ ጮክ ብለህ በማንበብ መለማመድ ጀምር። እያንዳንዱን የቃላት ስብስብ ሳትሰነካከል ወይም አፍህን ሳይዝህ ማንበብ እስክትችል ድረስ እየመላለስክ በማንበብ ተለማመድ።
9 እንግዳ ወይም አስቸጋሪ የሆኑብህን ቃላት በቀላሉ ማንበብ እስክትችል ድረስ መላልሰህ ማንበብ ይኖርብሃል። ይህን ቃል ለብቻው በደንብ ማንበብ ከቻልክ በኋላ እንደምታውቃቸው ሌሎች ቃላት ቀላል እስኪሆንልህ ድረስ ቃሉ ያለበትን ዓረፍተ ነገር በጠቅላላ እየደጋገምህ አንብብ።
10 በተጨማሪም ከዚህ በፊት ያላየኸውን ጽሑፍ ጮክ ብሎ ማንበብን ዘወትር ተለማመድ። ለምሳሌ የዕለት ጥቅሱንና በእርሱ ላይ የተሰጠውን ሐሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ስታያቸው ሁልጊዜ ጮክ ብለህ አንብብ። ዓይኖችህ ቃላትን አንድ በአንድ እየነጠሉ በማየት ፋንታ አንድ ሐሳብ የሚያስተላልፉ በርከት ያሉ ቃላትን አንድ ላይ ሰብሰብ አድርገው እንዲያዩ አለማምዳቸው። ከተለማመድህ ይህን ውጤታማ በሆነ መንገድ የመናገርና የማንበብ ችሎታ የራስህ ልታደርገው ትችላለህ።
**********
11–15. የውይይት መልክ ያለው ንግግር ተማሪው በሚጠቀምባቸው ቃላት ላይ የተመካው እንዴት ነው?
11 በምክር መስጫው ቅጽ ላይ የሚገኝ ተፈላጊ የሆነ ሌላው የንግግር ባሕርይ “የውይይት መልክ” የሚለው ነው። በየዕለቱ የምታደርገው ነገር ነው፤ ግን ንግግር ለመስጠት ስትወጣ ትጠቀምበታለህን? ብዙ ሰው ባለበት በቀላሉ መነጋገር የሚችሉ ሰዎች እንኳ “ንግግር ለመስጠት” ተዘጋጁ ተብሎ በቅድሚያ ከተነገራቸው በድንገት ተለውጠው “ዲስኩር” የሚሰጡ ወይም ቁም ንባብ የሚያነቡ ይመስላሉ። ይሁን እንጂ በውጤታማነቱ ተወዳዳሪ የሌለው የሕዝብ ንግግር አሰጣጥ ሰውን እያነጋገሩ እንዳሉ በሚመስል ወይም በውይይት መልክ የሚቀርበው ነው።
12 በመወያያ ቃላት መጠቀም። በውይይት መልክ የመናገራችን ውጤታማነት በአብዛኛው የተመካው በምንጠቀምባቸው ቃላት ላይ ነው። አስተዋጽኦ ይዘን በራሳችን አገላለጽ ንግግር በምንሰጥበት ጊዜ ልክ በጽሑፍ ላይ እንዳለው አድርጎ ሐሳቦቹን ማቅረቡ ብዙውን ጊዜ ጥሩ አይደለም። የጽሑፍና የንግግር አባባል ይለያያል። ስለዚህ እነዚህን ሐሳቦች በራስህ አነጋገር አቀነባብራቸው። ውስብስብና የተንዛዛ ዓረፍተ ነገር ከመናገር ተቆጠብ።
13 መድረክ ላይ ወጥተህ የምትሰጠው ንግግር ዕለታዊ አነጋገርህን ማንጸባረቅ ይኖርበታል። “ለመራቀቅ” አትሞክር። ያም ሆኖ ግን ተዘጋጅተህ
የምታቀርበው ንግግር ከዕለታዊ አነጋገርህ የተሻለ እንደሚሆን የታወቀ ነው፤ ምክንያቱም ነጥቦቹን በደንብ አስበህባቸው ስለምትመጣ በበለጠ ቅልጥፍና ትናገራቸዋለህ። ይህም በመሆኑ ቃላትን በተሻለ ሁኔታ አሳክተህ መናገር መቻል አለብህ።14 ይህም በየዕለቱ የመለማመድን አስፈላጊነት አጥብቆ ያሳያል። ንግግር ስታቀርብ ሌላ ሰው ለመሆን አትሞክር። ጸያፍ አነጋገርንም አስወግድ። ሁሉንም ሐሳብ በአንድ ዓይነት ቃላትና ሐረጎች አትግለጽ። ትርጉም በሚሰጥ መንገድ መናገርን ተማር። በዕለታዊ የንግግር ችሎታህ ኩራ። መድረክ ላይ ስትወጣ ቃላት በቀላሉ ይመጡልሃል። በዚህ ምክንያት ለማንኛውም አድማጭ በሚጥም፣ ቀላል በሆነና ተቀባይነት ባለው መንገድ በውይይት መልክ ትናገራለህ።
15 ይህ ምክር በተለይ ለመስክ አገልግሎት ይሠራል። የተማሪ ንግግር በምታቀርብበት ጊዜ ለአንድ ባለቤት የምትናገር ከሆነ ልክ በመስክ አገልግሎት ላይ እንዳለህ ሆነህ በማሰብ ወትሮ በቀላሉ የምትጠቀምባቸውን ቃላት ተጠቀም። ይህም የተዝናና ተፈጥሮአዊ አነጋገር እንድትጠቀም ያስችልሃል። ከዚህም በላይ በመስክ አገልግሎት ላይ ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ትምህርት እንድታቀርብ ያስችልሃል።
16–19. የንግግሩ አሰጣጥ እንዴት የውይይት መልክ እንዳይኖረው ሊያደርግ እንደሚችል አስረዳ።
16 የውይይት መልክ ያለው አቀራረብ። የውይይት መልክ ያለው አቀራረብ ተናጋሪው በሚጠቀምባቸው ቃላት ላይ ብቻ የተመካ አይደለም። የአነጋገርህ ሁኔታም ትልቅ ድርሻ አለው። ይህም የድምፅ ቃናን፣ ድምፅ የሚያስተላልፈውን ስሜትና እንደ ወትሮው ሆኖ መናገርን ያጠቃልላል። ልክ እንደ ዕለታዊ ንግግራችን ሁሉ ይህም በደመ ነፍስ ይመጣል፤ ብቻ አድማጮች እንዲሰሙት ሲባል ጎላ ይላል።
17 በውይይት መልክ የሚቀርብ ንግግር ልዩ ደንብ ተከትሎ ከሚቀርብ ንግግር ተቃራኒ ነው። “የሰባኪነት” መንፈስ የማይንጸባረቅበት የተውሶ ያልሆነ ንግግር ነው።
18 ጀማሪ ተናጋሪዎች በውይይት መልክ ማቅረብን የሚረሱበት አንዱ ምክንያት ትምህርቱን በምን ቃላት እንደሚያቀርቡ በቅድሚያ ለመወሰን ብዙ ጊዜ ስለሚያጠፉ ነው። ንግግር ለማቅረብ በምትዘጋጅበት ጊዜ ጠቅላላውን ንግግር በቃል ካላጠናሁ በደንብ አልተዘጋጀሁም ማለት ነው ብለህ አታስብ። አስተዋጽኦ ይዘህ በራስህ አገላለጽ ንግግር ለመስጠት በምትዘጋጅበት ጊዜ በንግግሩ ላይ የሚቀርቡትን ሐሳቦች በጥንቃቄ ለመመልከት የበለጠ ትኩረት ስጥ። እነዚህን እንደ ሐሳቦች አድርገህ በመከለስ በአእምሮህ ውስጥ አንድ በአንድ በቀላሉ ሊታወሱህ እስኪችሉ ድረስ መላልሰህ መከለስ አለብህ። ሐሳቦቹ በጥሩ ቅንብር ከተቀመጡና በቅድሚያ በደንብ ከታሰበባቸው ይህን ማድረጉ አስቸጋሪ አይሆንም። ንግግር በምትሰጥበትም ጊዜ ሐሳቦችህ በቀላሉ እንዳይመጡልህ የሚያግዳቸው ነገር አይኖርም። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነና ሐሳቦቹ ለሌሎች ሰዎች መልዕክት ለማስተላለፍ ባለህ ምኞት ከተገለጹ በውይይት መልክ ማቅረቡ የንግግርህ ክፍል ይሆናል።
19 ይህን ማድረግህን የምታረጋግጥበት አንዱ መንገድ በአድማጮች መካከል ያሉ የተለያዩ ግለሰቦችን እያየህ ለመናገር ጥረት ማድረግ ነው። በአንድ ጊዜ ለአንዱ ሰው በቀጥታ ተናገር። ያ ሰው ጥያቄ እንዳቀረበልህና አሁን መልስ እንደምትሰጠው አድርገህ አስብ። ከአንድ ሰው ጋር በግል ተገናኝታችሁ ያን ሐሳብ እያብራራህለት እንዳለህ አድርገህ አስብ። ከዚያም በአድማጮች መካከል ወደ ሌላው በመዞር ልክ እንደዚሁ አድርግ።
20–23. አነባበባችንን ተፈጥሮአዊ ሁኔታ እንዲያንጸባርቅ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
20 በውይይት መልክ ማንበብ እጅግ በጣም አስቸጋሪ፤ ነገር ግን በጣም አስፈላጊ ከሆኑት የንግግር ባሕርያት አንዱ ነው። አብዛኛውን ጊዜ በሕዝብ ፊት የምናነበው መጽሐፍ ቅዱስን ነው፤ ይኸውም በራሳችን አገላለጽ ንግግር በምናቀርብበት ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ልዩ ልዩ ጥቅሶችን እያወጣን እናነባለን። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ትርጉሙን በንቃት እየተከታተልን በስሜት ማንበብ ይኖርብናል። አነባበቡ ሕያው መሆን አለበት። ነገር ግን የአምላክ አገልጋዮች የቄሶችን የመመጻደቂያ ዘይቤ እየተጠቀሙ አስመሳይ ስሜት ለማሳየት በፍጹም አይፈልጉም። የይሖዋ አገልጋዮች የእርሱን ቃል የሚያነቡት በተፈጥሮአዊ ስሜት ቃላትን እያጠበቁና የዚህ መጽሐፍ ሕያው አነጋገር በሚጠይቀው ውሸት አልባ በሆነ እውነታ ነው።
21 በመጠበቂያ ግንብ ወይም በመጽሐፍ ጥናት ጊዜ የሚጠኑትን አንቀጾች የምናነበውም ከዚህ ባልተለየ መንገድ ነው። እዚህም ላይ ቢሆን የቃላቱ አሰካክና የዓረፍተ ነገሮቹ አወቃቀር በውይይት መልክ የተዘጋጀ ስላልሆነ ንባብህ ሁልጊዜ ውይይት ሊመስል አይችልም። ቢሆንም የምታነበውን ቃል ትርጉም እያስተዋልህ ልክ እንደ ወትሮህ ሆነህ ካነበብህ ከአስተዋጽኦ የሚቀርብ ንግግር ሊመስል ይችላል። እርግጥ ከወትሮ አነጋገርህ ትንሽ ለወጥ ብሎ የመደበኛነት መልክ መያዙ አይቀርም። እንግዲያው በቅድሚያ ለመዘጋጀት አጋጣሚ ካለህ ሊረዳህ የሚችል ማንኛውንም ምልክት በጽሑፉ ላይ እያደረግህ መዘጋጀትን ልማድ ማድረግና ንባቡን ባልተጋነነ መልኩ በወትሮው የአነጋገር መንገድ እየተጠቀምህ ለማንበብ የምትችለውን ያህል ጣር።
22 በውይይት መልክ ስናነብም ሆነ ስንናገር ቅንነትና ተፈጥሮአዊ ባሕርይ ቁልፍ ነገሮች ናቸው። ልብህ በስሜት ተሞልቶ ለአድማጮችህ ማራኪ በሆነ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ተናገር።
23 ሥነ ሥርዓታማነት ለተወሰኑ ጊዜያት ብቻ የተጠበቀ ጠባይ እንዳልሆነ ሁሉ የታረመ ንግግርም በተወሰኑ ወቅቶች ብቻ የምንጠቀምበት ነገር አይደለም። እቤት ውስጥ የምታሳያቸው መልካም ጠባዮች ከሌሎች ሰዎች ጋር ስትሆን እንደሚታዩ ሁሉ በየቀኑ ጥሩ የአነጋገር ዘይቤ የምትጠቀም ከሆነ ይኸው ልማድ በመድረክ ላይ ይንጸባረቃል።
**********
24, 25. ጥራት የጎደለው ንባብ ወይም አነጋገር የማይፈለግ ነገር የሆነው ለምንድን ነው?
24 የንባብና የአባባል ጥራት። የንባብና የአባባል ጥራትም በጣም አስፈላጊ ነገር ሲሆን በንግግር ምክር መስጫው ቅጽ ላይ ለብቻው ተቀምጧል። ጴጥሮስና ዮሐንስ ያልተማሩና ተራ ሰዎች መሆናቸው እንደተስተዋለ
ሁሉ ዛሬም በዓለማዊ ትምህርት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱት ሁሉም ክርስቲያኖች አይደሉም። ቢሆንም ጥራት በጎደለው አነጋገር ወይም ንባብ የመልእክቱን ውበት እንዳይቀንሱ መጠንቀቃቸው በጣም አስፈላጊ ነው። በቂ ትኩረት ከተሰጠው በቀላሉ ሊታረም የሚችል ጉድለት ነው።25 የአንድ ሰው ንባብ ወይም አነጋገር በጣም ጥራት ከጐደለው ለአድማጮች አእምሮ ያልሆነ ሐሳብ ሊያስተላልፍ ይችላል። ይህ ደግሞ የማይፈለግ ነገር ነው። ተናጋሪው አንድን ቃል አወላግዶ ቢናገር ወዲያው እንደ ቀይ የትራፊክ መብራት አእምሮህ ላይ ብልጭ ይልብሃል። እንዲያውም ተናጋሪው የሚደረድራቸውን ሐሳቦች መከታተል ታቆምና አሳስቶ ስለተናገረው ቃል ማሰብ ልትጀምር ትችላለህ። ሐሳብህ ከትምህርቱ ይልቅ ወደ አነጋገሩ ሊሳብ ይችላል።
26, 27. ጥራትን በተመለከተ ምን ችግሮች ተዘርዝረዋል?
26 ጥራትን በተመለከተ በአጠቃላይ ሦስት ዓይነት ችግሮች አሉ ለማለት ይቻላል። አንደኛው የተሳሳተ አባባል ወይም አነባበብ ነው። አንባቢው አለቦታው ያጠብቃል ወይም ያላላል፤ አለዚያም ፊደላትን አሳስቶ ያነባል፣ ይገድፋል። በዛሬው ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ ቋንቋዎች ቋሚ የሆነ የቃላት አባባል ወይም አነባበብ አላቸው። የእንግሊዝኛ ቋንቋ ግን ቋሚ ሥርዓት ስለሌለው ችግሩን ይበልጥ ያባብሰዋል። በሌላው በኩል ግን ትክክለኛ ሆኖ ነገር ግን በተጋነነ መንገድ ወይም ቄንጥ እያወጡ ማንበብም አለ። ይህም የተውሶ አባባል ሊመስል እንዲያውም እንደ ጉረኝነት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ይህ ደግሞ ተፈላጊ አይደለም። ሦስተኛው የንዝህላልነት አነጋገር ነው። ቃላትን ወይም ፊደላትን በመዋጥና በመሳሰሉት ልማዶች የሚደረግ ሰባራ አነጋገር ነው። ይህም መወገድ አለበት።
27 በዕለታዊ ንግግራችን ወቅት በደንብ በምናውቃቸው ቃላት እንጠቀማለን። ስለሆነም አጥርቶ መናገርን በተመለከተ ትልቅ ችግር አያጋጥመንም። ትልቅ ችግር ያለው በንባብ ጊዜ ነው። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች በግላቸውም ይሁን በሰው ፊት ብዙ ጊዜ ያነባሉ። ከቤት ወደ ቤት በምንሄድበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ለሰዎች እናነባለን። አንዳንድ ጊዜም በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ወይም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲመራ ወይም በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ላይ የጽሑፉን አንቀጾች እንድናነብ እንጠየቃለን። ልቅም ያለ አነጋገርና አነባበብ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ሌሎች ስለ ምን እየተናገርን እንዳለን እንደማናውቅ አድርገው ሊወስዱት ይችላሉ። በተጨማሪም የመልእክቱን ውበት ይቀንሳል።
28–34. አንድ ተማሪ የአነጋገሩንና የንባቡን ጥራት እንዲያሻሽል እንዴት እርዳታ ሊሰጠው ይችላል?
28 ጥራትን በተመለከተ ለተማሪው ከመጠን በላይ ጠንከር አድርጎ መምከር አያስፈልግም። ስለ አንድና ሁለት ቃላት ጥያቄ ካለ በግል መምከር በቂ ሊሆን ይችላል። ሆኖም በንግግር ወቅት በትክክል ያልተነበቡት ወይም ያልተነገሩት ቃላት በጣም ጥቂት ቢሆኑም እነዚህ ቃላት በመንግሥት አገልግሎታችን ወይም በዕለታዊ ንግግራችን ላይ አዘውትረን የምንጠቀምባቸው ከሆነ ተማሪው እንዴት አስተካክሎ ሊያነብ እንደሚችል እንዲያውቅ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ይህንን ቢጠቅስለት ለተማሪው ይጠቅመዋል።
29 በሌላው በኩል ግን ተማሪው ከመጽሐፍ ቅዱስ ሲያነብ አንድ ወይም ሁለት የዕብራይስጥ ቃላትን አሳስቶ ቢያነብ ይህ የጎላ ጉድለት ተደርጎ አይታይም። ነገር ግን በርካታ ስሞችን እያወላገደ ቢያነብ የዝግጅት ጉድለት መኖሩን ስለሚያሳይ ምክር መሰጠት ይኖርበታል። ተማሪው ትክክለኛውን አነባበብ አረጋግጦ እንዲለማመድበት ምክር ማግኘት አለበት።
30 ቄንጥ አውጥቶ ስለ ማንበብም ተመሳሳይ ምክር መስጠት ይቻላል። ተደጋጋሚ ልማድ በመሆኑ የንግግሩን ውበት የሚቀንስ ከሆነ ተማሪው እርዳታ ያስፈልገዋል። በተጨማሪም ብዙ ሰዎች በችኮላ ሲናገሩ አንዳንድ ፊደላትን እንደሚውጡ መታወስ አለበት። በዚህ ላይ ምንም ምክር መስጠት አያስፈልግም፤ ነገር ግን የዘወትር ልማድ ከሆነ ይኸውም ተማሪው ደጋግሞ ፊደላትን የሚውጥ ከሆነና ንግግሩን ለመከታተል የሚያስቸግር፤ ከዚህም አልፎ የንግግሩን ውበት የሚያጠፋበት ከሆነ ፊደላትን አስተካክሎ በመናገር ረገድ ርዳታ እንዲደረግለት ያስፈልጋል።
31 እርግጥ ምክር ሰጪው አንድ ቃል በተለያዩ አካባቢዎች ተቀባይነት ባለው የተለያየ መንገድ ጠብቆ ወይም ላልቶ ሊነበብ እንደሚችል ማስታወስ ይኖርበታል። ሌላው ቀርቶ የተለያዩ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት አንድ ቃል ሊነበብ የሚችልባቸውን ተቀባይነት ያላቸውን የተለያዩ መንገዶች ያስቀምጣሉ። ስለዚህ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች የአነባብን ወይም የአባባልን ጥራት በተመለከተ ምክር ሲሰጥ ይጠነቀቃል። ራሱ ደስ የሚለውን መሠረት አድርጎ ማረም የለበትም።
32 የቃላትን አባባል ወይም አነባበብ በተመለከተ ችግር ካለብህና ቆርጠህ ከተነሣህበት ይህን ማረም አያቅትህም። ብዙ ልምድ ያላቸው ተናጋሪዎችም እንኳን በደንብ የማያውቋቸውን የእንግሊዝኛ ቃላት ትክክለኛ አነባበብ ለማወቅ መዝገበ ቃላት ያያሉ። እንደመሰላቸው አያነቧቸውም።
33 ጥራትን ማሻሻል የምትችልበት ሌላው መንገድ ጥሩ ንባብ ለሚችል ሰው ቁጭ ብሎ ማንበብና እንዲከታተልህ መጠየቅ ነው። በተሳሳትህ ቁጥር እንዲያስቆምህና እንዲያርምህ ጠይቀው።
34 ሦስተኛው ዘዴ ጥሩ ተናጋሪዎችን በጥንቃቄ ማዳመጥ ነው። በሚናገሩበት ጊዜ በውስጥህ አሰላስል። ከአንተ አባባል በተለየ መንገድ የሚናገሯቸውን ቃላት አስተውል። ጻፋቸው። ብዙም ሳይቆይ የአነጋገርና የንባብ ጥራት ይኖርሃል። ቅልጥፍና፣ ጥራትና የውይይት መልክ ንግግርህን በጣም የሚስብ ያደርጉታል።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]