በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ፍቅር ያስገኘው አንድነት—በፍራንክፈርት፣ ጀርመን የተደረገ ትልቅ ስብሰባ

ፍቅር ያስገኘው አንድነት—በፍራንክፈርት፣ ጀርመን የተደረገ ትልቅ ስብሰባ

ፍራንክፎርተር ሩንድሻው በተባለ ጋዜጣ ሽፋን ላይ “የቤተሰብ ግብዣ ይመስላል” የሚል ርዕስ ወጥቶ ነበር። በዚያ የተገኙ ሰዎች ሁሉ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ።

ከፖርቶ ሪኮ የመጣችው ካርላ “ምንም እንግድነት አልተሰማኝም ነበር” ብላለች።

ከአውስትራሊያ የመጣችው ሣራ ደግሞ “በሌላ የምድር ክፍል የሚገኙ ቤተሰቦቼን ለመጠየቅ እንደመጣሁ ነው የተሰማኝ” ብላለች።

እንዲህ ያለ ልብ የሚነካ አስተያየት የሰጡት በምን ምክንያት ነው? በይሖዋ ምሥክሮች ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ባዩት ነገር ልባቸው ስለተነካ ነው። ከሐምሌ 18 እስከ 20, 2014 ድረስ የቆየው ይህ ስብሰባ የተደረገው ጀርመን ውስጥ በፍራንክፈርት አም ሜይን በሚገኘው ኮሜርትዝባንክ ስታዲየም ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ 37,000 የሚያህሉ ሰዎች ተገኝተው ነበር።

ተሰብሳቢዎቹ እዚያ የተገኙት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ለመቅሰም ነው። ፕሮግራሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን፣ መዝሙሮችን፣ ጸሎቶችን፣ ሁለት ድራማዎችን እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ሕያው ንግግሮችን ያካተተ ነበር።

ከሊባኖስ፣ ከሰርቢያ፣ ከብሪታንያ፣ ከአውስትራሊያ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ከደቡብ አፍሪካና ከግሪክ የመጡ ከ3,000 በላይ ልዑካንና በአገሪቱ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በስብሰባው ላይ ተገኝተው ነበር። ከ70 አገሮች የመጡና እንደ ሚስዮናዊነት ባሉ ልዩ የአገልግሎት መስኮች የሚካፈሉ ወደ 234 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮችም በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል።

የተወሰነ የስብሰባው ክፍል በኢንተርኔት ሥርጭት አማካኝነት ጀርመን ውስጥ በሚገኙ 19 የስብሰባ ቦታዎች እንዲሁም በስዊዘርላንድና በኦስትሪያ በቀጥታ ተላልፏል። አጠቃላይ የተሰብሳቢዎች ቁጥር 204,046 ነበር።

መሰናክሎችን መወጣት

በፍራንክፈርት ፕሮግራሙ የቀረበው በእንግሊዝኛ፣ በጀርመንኛና በግሪክኛ ነው። ስብሰባው በተደረገባቸው ሌሎች ቦታዎች ደግሞ ቱርክኛን፣ ታሚልን፣ ቻይንኛን፣ አረብኛንና ሁለት የምልክት ቋንቋዎችን ጨምሮ ፕርግራሙ በ17 ቋንቋዎች ተተርጉሟል።

በስብሰባው ላይ የተገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ከተለያዩ አገሮች የመጡ እንዲሁም የተለያየ ባሕልና ቋንቋ ያላቸው ቢሆኑም በመካከላቸው ክፍፍል አልነበረም፤ ፍቅር አንድ አድርጓቸዋል። (ዮሐንስ 13:34, 35) እርስ በርስ የሚተያዩት እንደ ወንድማማችና እህትማማች ነበር።

ከብሪታንያ የመጣው ቶባያስ “ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ድንበር የማይገድበው መሆኑን በገዛ ዓይናችን ማየት ችለናል” ብሏል።

“ከ20 ከሚበልጡ አገሮች የመጡ የይሖዋ ምሥክሮችን ማግኘት ችያለሁ። ለአምላክ እንዲሁም እርስ በርስ ያለን ፍቅር አንድ አድርጎናል” በማለት ከፖርቶ ሪኮ የመጣችው ዳቪያና ተናግራለች።

ከአውስትራሊያ የመጣው ማልኮም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክር የሆንኩት በአንዲት ትንሽ የገጠር ከተማ ውስጥ ነው። ልዩ ስለሆነው ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበራችን አንብቤያለሁ፤ እንዲሁም ቪዲዮዎችን ተመልክቻለሁ። እዚህ ግን በገዛ ዓይኔ የማየት አጋጣሚ አግኝቻለሁ። ይህ ደግሞ ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበሩ ይበልጥ እውን እንዲሆንልኝ አድርጓል። በእርግጥም እዚህ መገኘት በጣም እምነትን የሚያጠናክር ነው።”

የማይረሳ አቀባበል

በፍራንክፈርትና በአካባቢዋ ከሚገኙ 58 ጉባኤዎች የተውጣጡ የይሖዋ ምሥክሮች ለልዑካኑ ስጦታ የሰጡ ከመሆኑም በላይ የምሽት የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጅተውላቸዋል።

ከዩናይትድ ስቴትስ የመጣችሁ ሲንትያ እንዲህ ብላለች፦ “አስደናቂ አቀባበል ነው የተደረገልን። ወንድሞቻችን ያሳዩንን ፍቅር፣ ደግነትና ልግስና መቼም ቢሆን አልረሳውም።”

“የነበረው ፍቅር፣ ሳቅና ደስታ እንዲሁም የወንድማማች መዋደድ ከጠበቅኩት በላይ ነበር። አንዳችን ከሌላው ብዙ መማር እንችላለን” በማለት በጀርመን የሚኖረው ዛይመን ተናግሯል።

ከአውስትራሊያ የመጣችው ኤሚ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ምሽት ላይ የነበረው ዝግጅት፣ እኛ የይሖዋ ምሥክሮች የባሕታዊ ዓይነት ሕይወት እንደማንመራ ያረጋግጣል። መዝናናት እናውቅበታለን፤ ያውም ጨዋነት በሚንጸባረቅበት እውነተኛ መዝናኛ።”

የማይረሳ ትዝታ

በፍራንክፈርት የተደረገው ይህ ትልቅ ስብሰባ በዓለም ዙሪያ በዘጠኝ አገሮች ውስጥ ከተካሄዱት ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች አንዱ ብቻ ነው።

በፍራንክፈርት በተደረገው ስብሰባ ላይ የተገኘ አንድ ልዑክ ስብሰባው እንዴት እንደነበር ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “ከዚህ በፊት ከማታውቁት የቅርብ ዘመዳችሁ ለምሳሌ ከወንድማችሁ ጋር ተዋወቃችሁ እንበል። ልክ እንደ ተገናኛችሁ ልቡንም ቤቱንም ለእናንተ ወለል አድርጎ ከፈተላችሁ። በዚህ ጊዜ በቃላት ለመግለጽ የሚያስቸግር ደስታ ይሰማችኋል። እንግዲህ ይህን ስሜት በ37,000 አባዙት። በዚያ ስብሰባ ላይ በተገኘሁ ጊዜ የተሰማኝ እንደዚህ ነበር።”