በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ዓለምን ያዳረሰ የኢንተርኔት የቪዲዮ ስርጭት

ዓለምን ያዳረሰ የኢንተርኔት የቪዲዮ ስርጭት

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 5, 2013 በተካሄደው የዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንስልቬንያ 129ኛ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ በ21 አገራት የሚገኙ 257,294 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር፤ ይህ ቁጥር በአካል በቦታው በመገኘትም ሆነ በኢንተርኔት በሚተላለፍ የቀጥታ የቪዲዮ ስርጭት አማካኝነት ፕሮግራሙን የተከታተሉት ተሰብሳቢዎች አጠቃላይ ብዛት ነው። በዚያው ሳምንት መጨረሻ ላይ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች የተቀዳውን ፕሮግራም ተመልክተዋል። በመሆኑም አጠቃላይ በ31 አገራት የሚገኙ 1,413,676 የሚሆኑ ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለውታል። ይህ ዓመታዊ ስብሰባ በተሰብሳቢዎች ብዛት ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች እስካሁን ካደረጓቸው ስብሰባዎች ሁሉ የቀዳሚነቱን ቦታ ይዟል፤ ከዚህ ቀደም በዚህ ረገድ የተመዘገበው ከፍተኛ ቁጥር 1,327,704 ሲሆን ይህ የሆነው ሚያዝያ 28, 2013 በሜክሲኮና በመካከለኛው አሜሪካ አንድ ልዩ ስብሰባ በተደረገበት ወቅት ነው።

ከ1920ዎቹ ወዲህ የይሖዋ ምሥክሮች በስልክ መስመሮችና በሬዲዮ ሞገዶች አማካኝነት ትላልቅ ስብሰባዎችን በተለያዩ አገራት ለሚኖሩ አድማጮች ሲያስተላልፉ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ተሰብሳቢዎች ሳይቀር በስብሰባው ላይ የሚከናወኑትን ነገሮች በድምፅም ሆነ በምስል በቀጥታ ስርጭት አሊያም ስብሰባው ከተደረገ ብዙም ሳይቆይ መከታተል ችለዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር ዊልያም የተባለ የይሖዋ ምሥክር በ1941 በሪችመንድ፣ ቨርጅኒያ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ በተገኘበት ወቅት ፕሮግራሙ የተላለፈው በስልክ ነበር። ዊልያም ዓመታዊ ስብሰባ አሁን የሚተላለፍበትን መንገድ ከዚያ ጊዜ ጋር በማነጻጸር ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ፕሮግራሙ ሲተላለፍ በዓይን መመልከት እጅግ ብዙ ጥቅሞች አሉት። ያኔ ይደረግ ከነበረው ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር አይችልም።”

በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ፕሮግራሙ በኢንተርኔት አማካኝነት እንዲተላለፍ ለማድረግ ከዓመት በላይ ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩ ከመሆኑም ሌላ ለዚህ ሥራ ሲሉ በአጠቃላይ ብዙ ሺህ ሰዓታትን አውለዋል። ስብሰባው በኢንተርኔት አማካኝነት በተላለፈባቸው ቀናት ላይ ባለሙያዎች በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኝ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ውስጥ ሆነው ስርጭቱን በትኩረት ይቆጣጠሩ ነበር፤ ከዚህም በተጨማሪ ፕሮግራሙ የሚተላለፍባቸው መሰብሰቢያ ቦታዎች በ15 የተለያዩ የጊዜ ክልሎች (time zone) ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ቀንም ሆነ ሌሊት ከመቆጣጠሪያ ጣቢያው ሰው መጥፋት አልነበረበትም። ይህን ዝግጅት በማደራጀቱም ሆነ በመቆጣጠሪያ ጣቢያው ሆኖ ሁኔታውን በመከታተሉ ተግባር ላይ የተሳተፈው ራየን “እንቅልፍ አልነበረንም፤ ሆኖም ብዙዎች ከፕሮግራሙ እንደሚጠቀሙ ማወቃችን ሁሉንም ነገር አስረስቶን ነበር” ብሏል።

ተሰብሳቢዎች ፕሮግራሙን ሲከታተሉ (ካትሪን፣ ኖርዘርን ቴሪተሪ፣ አውስትራሊያ)