መጋቢት 1 ቀን 2014 ቅዳሜ ዕለት፣ ቤኒን ሲቲ በተባለ የይሖዋ ምሥክሮች የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ውስጥ በደስታ የተሞሉ 823 ሰዎች በናይጄሪያ የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበትን ወቅት ለመመሥከር ተሰብስበው ነበር። የገንዘብ አቅማቸው ውስን በሆኑ አገሮች ውስጥ የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባት የተደረገው ዝግጅት ከጀመረበት ከ1999 ወዲህ የይሖዋ ምሥክሮች በናይጄሪያ 3,000 የመንግሥት አዳራሾችን ገንብተዋል።

የቀድሞው

ከ1920ዎቹ ወዲህ ናይጄሪያ ውስጥ የመሰብሰቢያ ቦታዎችን ለማግኘት ይደረግ የነበረው ጥረት በስብሰባው ላይ በአጭሩ ተገልጾ ነበር። መጀመሪያ አካባቢ የይሖዋ ምሥክሮች ይሰበሰቡ የነበረው በግለሰብ ቤቶች ውስጥ ወይም አዳራሾችን በመከራየት ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ለአምልኮ ዓላማ ብቻ የሚውል አዳራሽ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኙት በ1935 ሲሆን አዳራሹ የተገነባው በኢሌሳ ከተማ ነበር። ከ1938 እስከ 1990 ባሉት ዓመታት ውስጥ የጉባኤዎች ቁጥር 200 እጥፍ ያህል በማደግ ከ14 አንስቶ 2,681 ደረሰ፤ ከእነዚህ ጉባኤዎች መካከል ብዙዎቹ የመሰብሰቢያ ቦታ ለማግኘት ይቸገሩ ነበር። በአንዳንድ ቦታዎች ስድስት ጉባኤዎች በአንድ የመንግሥት አዳራሽ ይጠቀሙ ነበር። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ የተሰብሳቢዎቹ ቁጥር አዳራሹ ሊይዘው ከሚችለው በላይ ይሆንና አንዳንዶች ውጭ ቆመው በመስኮት በኩል ስብሰባውን ለመከታተል ይገደዱ ነበር። በተጨማሪም ብዙ ጉባኤዎች በግለሰብ ቤቶችና በትምህርት ቤቶች ውስጥ መሰብሰባቸውን አላቆሙም።

የአሁኑ

በ1990 የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ለመንግሥት አዳራሽ ግንባታ የሚደረገውን መዋጮ ለጉባኤዎች በማበደር ለአዳራሾች ግንባታ ድጋፍ መስጠት ጀመረ። እስከ 1997 ባለው ጊዜ ውስጥ የአካባቢ የግንባታ ኮሚቴዎች፣ 105 ጉባኤዎች አዳራሽ እንዲገነቡ ወይም አዳራሻቸውን እንዲያድሱ እርዳታ ሰጥተዋል። ከ1997 እስከ 1999 ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ ከ7 እስከ 15 ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ 13 አዳራሾች ተገንብተዋል።

የግንባታ ሥራው እንዲህ ባለ ፍጥነት ቢከናወንም እንኳ በናይጄሪያ እየጨመረ ከመጣው የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ጋር ሊጣጣም አልቻለም። በሚያዝያ 1998 የአገሪቱ ቅርንጫፍ ቢሮ 1,114 የመንግሥት አዳራሾች እንደሚያስፈልጉ ገልጾ ነበር።

የናይጄሪያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ዶን ትሮስት በቤኒን ሲቲ በተካሄደው ልዩ ስብሰባ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “በጣም ከባድ ሥራ ነበር! ‘ይህን ሥራ ማጠናቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?’ የሚለው ጉዳይ አሳስቦን ነበር።” ከ1999 ወዲህ ግን ይህ ጥያቄ ምላሽ አገኘ፤ ከስድስት እስከ ስምንት አባላትን ያቀፉ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ቡድኖች በአገሪቱ በሙሉ ለሚገኙ ጉባኤዎች እርዳታ መስጠት ጀመሩ። እነዚህ ቡድኖች ቀለል ያሉ የግንባታ ንድፎችን በመጠቀም ባለፉት 14 ዓመታት ውስጥ በየወሩ በአማካይ 17 አዳራሾችን መገንባት ችለዋል።

ወንድም ትሮስት ለተከናወነው አስደናቂ ሥራ ተሰብሳቢዎቹን ካመሰገነ በኋላ ሥራው ገና እንዳልተጠናቀቀ ጠቆመ። በ2013 የናይጄሪያ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከ8,000 የሚበልጥ ጭማሪ አሳይቷል። “ወደፊት የሚገኘውን ጭማሪ ግምት ውስጥ በማስገባት በየዓመቱ ተጨማሪ 100 የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጉናል” በማለት ተናገረ። በ2013 በናይጄሪያ የተመዘገበው የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ ቁጥር 351,000 ነበር፤ ከ5,700 የሚበልጡ ጉባኤዎች እንዳሉም ሪፖርት ተደርጓል።