በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

የዎርዊክ ፎቶ ጋለሪ 6 (ከመጋቢት እስከ ነሐሴ 2016)

የዎርዊክ ፎቶ ጋለሪ 6 (ከመጋቢት እስከ ነሐሴ 2016)

ይህ የፎቶ ጋለሪ ከመጋቢት እስከ ነሐሴ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ በአዲሱ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የተከናወነውን ግንባታ እንዲሁም ፈቃደኛ ሠራተኞች ለግንባታው ያደረጉትን ድጋፍ ያሳያል።

የዎርዊክ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ የተነሳ ፎቶግራፍ። ከላይ ጀምሮ ከግራ ወደ ቀኝ፦

  1. የተሽከርካሪዎች ጥገና ሕንፃ

  2. የጎብኚዎች የመኪና ማቆሚያ

  3. የጥገና ሕንፃ እና የነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ

  4. መኖሪያ ሕንፃ ለ

  5. መኖሪያ ሕንፃ መ

  6. መኖሪያ ሕንፃ ሐ

  7. መኖሪያ ሕንፃ ሀ

  8. ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

መጋቢት 16, 2016—የዎርዊክ የግንባታ ቦታ

አትክልተኞች የባሉጥና የሜፕል ዛፎችን በዛፍ መትከያ ስፍራው ላይ ሲያወርዱ። በዎርዊክ ከ1,400 በላይ አዳዲስ ዛፎች እየተተከሉ ነው።

መጋቢት 23, 2016—የተሽከርካሪዎች ጥገና ሕንፃ

በዎርዊክ የሚሠሩ ሰዎች የጌታ ራትን ሲያከብሩ። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በየዓመቱ በሚያከብሩት በዚህ በዓል ላይ በዎርዊክ 384 ሰዎች ተገኝተዋል።

ሚያዝያ 15, 2016—የዎርዊክ የግንባታ ቦታ

አናጺዎች በዋናው በር ጠባቂዎች የሚቀመጡበት ቤት ላይ መስኮቶች ሲገጥሙ። በዋናው በር ላይ የሚሆኑ ጠባቂዎች ጎብኚዎችን ይቀበላሉ፤ ሕንፃዎቹን ይጠብቃሉ፤ እንዲሁም ወደ ግቢው የሚገቡና የሚወጡ መኪኖችን ያስተናብራሉ።

ሚያዝያ 19, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

በምንጣፍ ሙያ የተሰማሩ አንድ አባትና ልጅ፣ ሁለተኛ ፎቅ በሚገኘው ኮሪደር ላይ ታይል ሲያነጥፉ። ብዙ ሰው በሚመላለስባቸው ቦታዎች ላይ በአራት ማዕዘን ቅርጽ የተቆራረጡ ታይሎች በብዛት ጥቅም ላይ ውለዋል፤ ምክንያቱም አንድ ወጥ ከሆኑት ምንጣፎች ይልቅ ታይሎች ጉዳት ቢደርስባቸው እንኳ አንስቶ በሌላ መተካት ይበልጥ ይቀላሉ።

ሚያዝያ 27, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

አናጺዎች፣ ተነቃቃይ የቢሮ መከፋፈያዎችን ሲገጥሙ። እነዚህ መከፋፈያዎች ተነቃቃይ በመሆናቸው ዲፓርትመንቶች አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የቢሮዎቹን አከፋፈል መቀየር ይችላሉ።

ግንቦት 10, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

አንድ የግንባታ ሠራተኛ የጎብኚዎች መጸዳጃ ቤቶችን የመጸዳጃ ቤት መቀመጫና መከፋፈያ ለመግጠም ሲያዘጋጅ።

ግንቦት 26, 2016—የዎርዊክ የግንባታ ቦታ

የድንገተኛ አደጋ ቡድኑ እሳት ማጥፋት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ልምምድ ሲያደርግ። እነዚህ የእሳት አደጋ ሠራተኞች አደጋ ሲከሰት በፍጥነት እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀታቸው፣ በዎርዊክ የሚገኙ ሠራተኞችንና ሕንፃዎችን ከአደጋ ለመጠበቅ ያስችላቸዋል፤ እንዲሁም በአካባቢው ባለው የድንገተኛ አደጋ ቢሮ ላይ የሚኖረውን ሸክም ይቀንሳሉ።

ግንቦት 30, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

ከዋናው የመመገቢያ አዳራሽ ጋር በኢንተርኔት የተገናኘው የመጀመሪያ የማለዳ አምልኮ ፕሮግራም ከመጀመሩ በፊት አንድ አስተናጋጅ በዎርዊክ ያሉ የግንባታ ሠራተኞችን በየቦታቸው ሲያስቀምጥ።

ግንቦት 31, 2016—የጥገና ሕንፃ እና የነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ

አንዲት አናጺ፣ ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች መረጃ ከሚሰጡት ከ2,500 የሚበልጡ ምልክቶች መካከል አንዱን የሌዘር ጨረር በመጠቀም ስትለጥፍ።

ሰኔ 1, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

አንዲት በያጅ ከመተላለፊያው ወደ አዳራሹ የሚወስደው ዋና ደረጃ ላይ የእጅ መያዣውን ስትገጥም። ፎቶው ላይ በታች በኩል የሚታየው እሳት የሚከላከል ልብስ፣ በአቅራቢያው ያሉት ተሠርተው የተጠናቀቁ ነገሮች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ይከላከላል።

ሰኔ 9, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

ከግድግዳና ከጣሪያው ጋር የተያያዙ ነገሮችን የሚሠራው ክፍል አባል የሆነ አንድ ሰው፣ ያለ አስጎብኚ ከሚጎበኙት ሦስት ዐውደ ርዕዮች አንዱ ወደሆነው “በተግባር የተደገፈ እምነት” ወደተባለው ዐውደ ርዕይ በሚወስደው መንገድ ላይ ያለውን ጂፕሰም ሲሠራ። የእያንዳንዱ ጋለሪ አሠራር ከዐውደ ርዕዩ ጭብጥ ጋር የሚሄድ ነው።

ሰኔ 16, 2016—የተሽከርካሪዎች ጥገና ሕንፃ

የግንባታ ሠራተኞች አርማታ የለበሰውን ወለል ዴንሲፊኬሽን ለተባለው ሂደት ሲያዘጋጁ። ዴንሲፊኬሽን አርማታው ውስጥ ያሉ ቀዳዶች እንዲደፈኑ በማድረግ ይበልጥ ጠንካራ፣ አቧራና የጎማ ምልክት የማይዝ ብሎም ለጥገና ቀላል እንዲሆን ያደርገዋል።

ሰኔ 29, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

የአናጺዎች ቡድን ከእንግዳ መቀበያው በላይ የሚንጠለጠል ፋይበርግላስ ሲገጥሙ። የሚገጠሙት የፋይበርግላስ ፕላስቲኮች በተወሰነ መጠን ብርሃን የሚያሳልፉ በመሆናቸው ዋናው መግቢያ ብርሃን እንዲኖረው ያደርጋሉ።

ሰኔ 29, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

አንድ ባልና ሚስት “መጽሐፍ ቅዱስ እና መለኮታዊው ስም” የተባለው ዐውደ ርዕይ መግቢያ ላይ የድንጋይ ንጣፍ ሲሠሩ።

ሐምሌ 6, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

አንዲት አናጺ በዋናው የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ካሉት 1,018 መቀመጫዎች አንዱን ስትገጥም። በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ፣ የቤቴል ቤተሰብ የመጠበቂያ ግንብ ጥናትና ሌሎች ለቤተሰቡ የተዘጋጁ መንፈሳዊ ፕሮግራሞች ይካሄዳሉ።

ሐምሌ 9, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

አናጺዎች፣ የኤሌክትሪክ ሠራተኞችና ሌሎች የግንባታ ሠራተኞች ለጎብኚዎች የተዘጋጀውን የሚያበራ የእንኳን ደህና መጣችሁ ምልክት በዋናው እንግዳ መቀበያ ውስጥ ሲገጥሙ።

ሐምሌ 13, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

የግንባታ ድጋፍ ሰጪው ቡድን ሁለት አባላት፣ በዋናው እንግዳ መቀበያ ለሚሠሩ የግንባታ ሠራተኞች ውኃ ሲያቀርቡ። በተለይ አየሩ ሞቃታማ በሚሆንበት ወቅት የግንባታ ቡድኖች አዘውትረው ውኃ እንዲጠጡ ይበረታቱ ነበር።

ሐምሌ 19, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

አንድ አናጺ፣ “መጽሐፍ ቅዱስ እና መለኮታዊው ስም” በተባለው ዐውደ ርዕይ ላይ የሚታዩ ለየት ያሉ መጽሐፍ ቅዱሶች የሚቀመጡበትን ማሳያ ሲገጥም። ዐውደ ርዕዩ ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሶችንና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ጥንታዊ ቁሳቁሶችን የሚያሳይ የሚዞር ጋለሪ ይኖረዋል።

ሐምሌ 22, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

አንድ አናጺ ግድግዳ ላይ ያለውን ንድፍ በመጠቀም፣ የአውስትራሊያንና በደቡብ ምሥራቅ እስያ የሚገኙ ደሴቶችን ቅርጽ በዋናው የእንግዳ መቀበያ ውስጥ በሚገኝ ካርታ ላይ ሲለጥፍ። የይሖዋ ምሥክሮች የሚለው ስም ወደ 700 በሚጠጉ ቋንቋዎች ግድግዳው ላይ ይገኛል።

ሐምሌ 23, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

የቤቴል ቤተሰብ አባላት በአንድ የሥልጠና ስብሰባ ላይ ተገኝተው። ስብሰባዎቹ የተዘጋጁት ወደፊት በዎርዊክ የሚሠሩትን ቤቴላውያን ለመቀበልና ሥልጠና ለመስጠት እንዲሁም በዎርዊክ የግንባታ ቦታ አሁንም ስላሉት አደጋ ሊፈጥሩ የሚችሉ ነገሮች ለማስጠንቀቅ ነው።

ነሐሴ 17, 2016—የJW ብሮድካስቲንግ ስቱዲዮ

ሠራተኞች የJW ብሮድካስቲንግ አቅራቢ ከሚቀመጥበት ዴስክ በላይ የሚሆነውን የቀለበት ቅርጽ ያለው መብራትና መብራቱ የሚንጠለጠልበትን ብረት ሲሰቅሉ። በስቱዲዮው ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉት አብዛኞቹ ነገሮች ቀደም ሲል ስቱዲዮው ከነበረበት ከብሩክሊን የተወሰዱ ናቸው።

ነሐሴ 24, 2016—የዎርዊክ የግንባታ ቦታ

አንድ የኤሌክትሪክ ሠራተኛ በዋናው መግቢያ ላይ የሚሆነውን የLED መብራት ያለው አዲስ ምልክት ሲገጥም። ብዙዎቹ የዋናው መሥሪያ ቤት ዲፓርትመንቶች ከመስከረም 1 ጀምሮ በዎርዊክ ሥራቸውን ጀምረዋል።