በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

የዎርዊክ ፎቶ ጋለሪ 1 (ከግንቦት እስከ ነሐሴ 2014)

የዎርዊክ ፎቶ ጋለሪ 1 (ከግንቦት እስከ ነሐሴ 2014)

የይሖዋ ምሥክሮች በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ ዋና መሥሪያ ቤታቸውን እየገነቡ ነው። ከግንቦት እስከ ነሐሴ 2014 ባለው ጊዜ ውስጥ ከተሽከርካሪዎች ጥገና ሕንፃ፣ ከአስተዳደር ቢሮዎችና ከአገልግሎት መስጫ ሕንፃ እንዲሁም ከመኖሪያ ሕንፃዎች ሐ እና መ ግንባታ ጋር በተያያዘ ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል። ይህ የፎቶ ጋለሪ በእነዚህ ወራት የተከናወኑትን አንዳንድ ሥራዎች ያሳያል።

የዎርዊክ ግንባታ ሲጠናቀቅ ምን መልክ እንደሚኖረው የሚያሳይ ምስል። ከላይ ጀምሮ ከግራ ወደ ቀኝ፦

  1. የተሽከርካሪዎች ጥገና ሕንፃ

  2. የጎብኚዎች የመኪና ማቆሚያ ሕንፃ

  3. የጥገና ሕንፃ እና የነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ

  4. መኖሪያ ሕንፃ ለ

  5. መኖሪያ ሕንፃ መ

  6. መኖሪያ ሕንፃ ሐ

  7. መኖሪያ ሕንፃ ሀ

  8. የአስተዳደር ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

ግንቦት 1, 2014—የዎርዊክ የግንባታ ቦታ

ከደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በኩል ሲታይ፤ በስተ ሰሜን በኩል ያለው ሐይቅ፣ ስተርሊንግ ፎረስት ሌክ (ብሉ ሌክ) ተብሎ ይጠራል። ፊት ለፊት የሚታየው የመኖሪያ ሕንፃ መ ምድር ቤት እየተገነባ ነው። በሐይቁ በኩል የሚገኘው መኖሪያ ሕንፃ ሐ አርማታ እየተሞላለት ነው።

ግንቦት 14, 2014—ከግንባታ ቦታው ውጭ የሚካሄድ ሥራ

በመኖሪያ ክፍሎች ውስጥ የሚገባ መታጠቢያ ቤት ሲገጣጠም። የመታጠቢያ ቤቱ ፍሬም ተሠርቶ ግድግዳ የሚገጠምለት ሲሆን መታጠቢያ ቤቱ የቧንቧና የኤሌክትሪክ መስመሮችን ያካተተ ነው፤ አየር ማስገቢያ ይደረግለታል፤ እንዲሁም በውስጡ ለባኞ የሚሆን ክፍል ይከለላል። መታጠቢያ ቤቱ ተወስዶ በሕንፃው ላይ ሲገጠም አጠቃላይ ሥራው ይጠናቀቃል።

ግንቦት 22, 2014—የተሽከርካሪዎች ጥገና ሕንፃ

የቧንቧ ሠራተኞች ምድር ቤት ውስጥ እየሠሩ ነው። የግንባታው ፕሮጀክት እስኪጠናቀቅ ድረስ ይህ ቦታ እንደ መመገቢያ ክፍል ሆኖ ያገለግላል፤ በፎቶግራፉ ላይ የሚታየው ክፍል 500 ሠራተኞችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን በሕንፃው ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ቦታዎች ደግሞ ተጨማሪ 300 ሰዎችን ማስተናገድ ይችላሉ። የግንባታው ፕሮጀክት ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ጊዜያዊ የመመገቢያ ክፍሎቹ ይነሱና ሕንፃው ለተሽከርካሪዎች ጥገና አመቺ እንዲሆን ተደርጎ ይዘጋጃል።

ሰኔ 2, 2014—የተሽከርካሪዎች ጥገና ሕንፃ

ባለሙያዎች በልዩ መንገድ በተዘጋጀ አፈር ጣሪያውን ሲሸፍኑ። ተክል እንዲበቅልባቸው ታስበው በዚህ መንገድ የሚዘጋጁት ጣሪያዎች የኃይል ወጪን ይቀንሳሉ፤ በዝናብ ውኃ ምክንያት የሚከሰተውን ጎርፍ ይቀንሳሉ፤ ከዝናብ ጋር አብረው የሚወርዱ በካይ ነገሮችን ያጠራሉ።

ሰኔ 5, 2014—የአስተዳደር ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

ይህ ግንባታ ሦስት ሕንፃዎችን እርስ በርስ የሚያገናኝ ይሆናል፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ በአጠቃላይ 42,000 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ ማግኘት ይቻላል። ፎቶግራፉ ላይ የሚታዩት የሕንፃ ተቋራጭ ሠራተኞች ዓምዶቹ የሚገነቡባቸውን የብረት ፌሮዎች እያሰሩ ነው።

ሰኔ 18, 2014—የተሽከርካሪዎች ጥገና ሕንፃ

ሠራተኞች ፕሮፔን በተባለ ጋዝ የሚነድ እሳት ተጠቅመው ጣሪያው ላይ አስፋልት ሲለጥፉ። ከጣሪያው ላይ እንዳይወድቁ የሚጠብቅ የደኅንነት ቀበቶ ታስሮላቸዋል።

ሰኔ 24, 2014—መኖሪያ ሕንፃ ሐ

ከግንባታው ቦታ ውጭ አስቀድሞ የተገጣጠመ የተለያዩ መስመሮችን የያዘ ቱቦ እንዲሁም የማሞቂያና የማቀዝቀዣ መሣሪያ ሕንፃው ላይ ሲገጠም። በዎርዊክ የግንባታ ፕሮጀክት ላይ ከሚሳተፉት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል 35 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።

ሐምሌ 11, 2014—ሞንትጎሜሪ፣ ኒው ዮርክ

ለግንባታው ድጋፍ የሚሰጠው ይህ ቦታ ለመጋዘንነት እና ለግንባታው የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለመገጣጠም የሚያገለግል ሲሆን ቦታውን ያገኘነው በየካቲት 2014 ነው። ስፋቱ 20,000 ካሬ ሜትር ነው። ፎቶግራፉ ላይ በስተ ቀኝ፣ በላይ በኩል የሚታዩት ነጭ ነገሮች በሕንፃው ላይ ለመገጠም ዝግጁ የሆኑ መታጠቢያ ቤቶች ናቸው።

ሐምሌ 24, 2014—መኖሪያ ሕንፃ ሐ

ሕንፃው በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ ሲታይ ይህን ይመስላል። ይህ ሕንፃ በዋናው መሥሪያ ቤት የሚሠሩ 200 ሰዎችን ለማኖር የሚያስችል አቅም አለው። የአብዛኞቹ መኖሪያ ክፍሎች ስፋት ከ30 እስከ 55 ካሬ ሜትር ሲሆን እያንዳንዱ ክፍል አነስተኛ ኩሽና፣ መታጠቢያ ቤትና ትንሽ በረንዳ አለው።

ሐምሌ 25, 2014—የጥገና ሕንፃ እና የነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ

መሬቱ ለግንባታ ሲዘጋጅ። ፎቶግራፉ ላይ በስተ ግራ በኩል ከላይ የሚታየው መሣሪያ ድንጋይ የሚፈጭ ሲሆን ከመሬት ተቆፍሮ የወጣውን ንጥረ ነገር በኋላ ላይ ለግንባታው ዝግጁ እንዲሆን ያደርጋል። ይህ ፕሮጀክት በሚጠናቀቅበት ወቅት በአጠቃላይ 260,000 ሜትር ኩብ ገደማ የሚሆን አፈር ከዎርዊክ የግንባታ ቦታ ተቆፍሮ ይወጣል። በየቀኑ በአማካይ 23 የጭነት መኪናዎች ለዚህ ሥራ ጥቅም ላይ ይውላሉ።

ሐምሌ 30, 2014—የተሽከርካሪዎች ጥገና ሕንፃ

በጣሪያው ላይ ተክል ሲተከል።

ነሐሴ 8, 2014—የዎርዊክ የግንባታ ቦታ

ለቢሮዎች እንዲሆን ታስቦ ከሚገነባው ሕንፃ በላይ፣ በስተ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ካለ ረጅም የከባድ ዕቃ ማንሻ መሣሪያ ላይ ሆኖ የተነሳ ፎቶግራፍ። በስተ ግራ ከታች በኩል የሚታየው ሕንፃ የጎብኚዎች የመኪና ማቆሚያ ሕንፃ ሲሆን በየቀኑ የግንባታው ሠራተኞች በሚጠቀሙባቸው መኪኖች የተሞላ ነው። አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ለሦስት ወይም ለአራት ቀን ቆይተው ያለ ምንም ክፍያ በግንባታው ለመካፈል ሲሉ ለአንድ ጉዞ ብቻ እስከ 12 ሰዓት የሚፈጅ መንገድ ተጉዘው ይመጣሉ።

ነሐሴ 13, 2014—የተሽከርካሪዎች ጥገና ሕንፃ

ጊዜያዊ የመመገቢያ አዳራሹ ግንባታ እየተጠናቀቀ ነው። የቪዲዮ ስክሪኖች (እርግጥ በዚህ ጊዜ አልተገጠሙም) እና ጣሪያው ላይ የሚሰቀሉ የድምፅ ማጉያ መሣሪያዎች በዚህ የግንባታ ፕሮጀክት የሚካፈሉት ሠራተኞች በዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ማለዳ ላይ የሚካሄደውን የአምልኮ ፕሮግራም እና ሌሎች መንፈሳዊ ፕሮግራሞችን በቀጥታ ስርጭት ለመከታተል ያስችሏቸዋል።

ነሐሴ 14, 2014—የአስተዳደር ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

የመጀመሪያው ፎቅ ላይ ያለው ወለል አርማታ እየተሞላ ነው። በስተ ቀኝ በኩል የሚታየው ሠራተኛ የአርማታ መጠቅጠቂያ መሣሪያ እየተጠቀመ ነው፤ ይህ መሣሪያ አርማታው ክፍተት እንዳይኖረው እንዲሁም ጥቅጥቅ ብሎ እንዲሞላ ለማድረግ ያስችላል።

ነሐሴ 14, 2014—የአስተዳደር ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

የኤሌክትሪክ መስመሮች የሚተላለፉባቸው ቱቦዎች፤ በኋላ ላይ የምድር ቤቱ ወለል እነዚህን ቱቦዎች ይሸፍናቸዋል።

ነሐሴ 14, 2014—የአስተዳደር ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

የመጀመሪያው ፎቅ የአርማታ ሥራ እየተጠናቀቀ ነው። በዎርዊክ የግንባታ ፕሮጀክት ላይ እስከዚህ ጊዜ ድረስ አርማታ ከተሞሉባቸው ወለሎች መካከል ሰፊው ይህ ነው፤ በአጠቃላይ 540 ሜትር ኩብ የሚሆን አርማታ አስፈልጓል። በግንባታው ቦታ የሚገኝ ትልቅ የመደባለቂያ መሣሪያ ለአርማታው የሚያስፈልጉ ነገሮችን ይደባልቃል፤ ከዚያም ውህዱ መደባለቂያ ባላቸው ስምንት መኪኖች ተጭኖ ወደሚፈለገው ቦታ ይሄዳል፤ በተጨማሪም አርማታውን የሚሞሉ ሁለት ፓምፖች አሉ፤ በዚህ መንገድ አርማታውን ለመሙላት 5 ሰዓት ተኩል ይፈጃል። በፎቶግራፉ መሃል ላይ የሚታየው የሕንፃው የመወጣጫ ደረጃ ነው።

ነሐሴ 14, 2014—መኖሪያ ሕንፃ ሐ

በሕንፃው ጣሪያ ዙሪያ መከታ የሚሆን አጭር ግንብ ሲሠራ። ከላይ በኩል እንደሚታየው የመኖሪያ ሕንፃ ሀ ምድር ቤት ግንባታ እየተከናወነ ነው።

ነሐሴ 15, 2014—መኖሪያ ሕንፃ ሐ

ተገጣጥሞ የመጣ መታጠቢያ ቤት በከባድ ዕቃ ማንሻ አማካኝነት ወደ ሦስተኛ ፎቅ ሲወሰድ። በዎርዊክ የግንባታ ፕሮጀክት ላይ የሚውሉት አንዳንዶቹ ነገሮች አስቀድመው የተገጣጠሙ ናቸው፤ ይህም በግንባታው ቦታ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ስለሚረዳ ሥራውን ያፋጥነዋል።

ነሐሴ 20, 2014—መኖሪያ ሕንፃ ሐ

የሕንፃ ሥራ ተቋራጭ ሠራተኞች የኃይል ወጪን የሚቀንስ የሲሚንቶ ግድግዳ ሲገጥሙ። ግድግዳው የተሠራበት የሲሚንቶ ግንብ የቀለመ ስለሆነ ግድግዳውን ቀለም መቀባት አያስፈልግም፤ እንዲሁም ግድግዳውን መንከባከብ ብዙ ሥራ አይጠይቅም። ግድግዳዎቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ መግጠም የሚቻል ሲሆን ይህም ፕሮጀክቱ በታሰበለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ያስችላል።

ነሐሴ 31, 2014—የዎርዊክ የግንባታ ቦታ

ከደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በኩል ሲታይ። ከፊት ለፊት የሚታየው የመኖሪያ ሕንፃ መ ወለል እየተሠራ ሲሆን ከዚያ በስተ ጀርባ የሚታየው የመኖሪያ ሕንፃ ሐ ግንባታ ሊጠናቀቅ እየተቃረበ ነው።