የይሖዋ ምሥክሮች ስድስት ዓመት የፈጀውን በዎልኪል፣ ኒው ዮርክ የሚገኘውን ዋችታወር ፋርምስ የማስፋፊያ ፕሮጀክት በቅርቡ አጠናቀዋል። በመጨረሻዎቹ ሁለት ዓመታት ግንባታው የሚካሄድበት ፍጥነት በመጨመሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች የሚኖሩባቸው ተጨማሪ ቤቶች አስፈልገው ነበር። በዚህም ምክንያት በአቅራቢያው የሚገኙ 25 ቤቶችን ተከራዩ።

የተከራዮቹ ባህርይ

የቤቶቹ ባለቤቶች ቤታቸውን ለይሖዋ ምሥክሮች በማከራየታቸው ምን ተሰምቷቸው ነበር?

  • አንዲት አከራይ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ተከራዮቹን ወደናቸዋል። እኔና ባለቤቴ የምንኖረው ልክ [ካከራየነው ቤት] አጠገብ ነው፤ ሁልጊዜም ተከራዮቹ ተባባሪዎችና ሰው ወዳዶች እንደሆኑ ይሰማን ነበር።”

  • ባከራየችው ቤት አካባቢ የምትኖር ሌላ የቤት ባለቤትም ተከራዮቿን በተመለከተ እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ባገኘናቸው ቁጥር ደስ ይለን ነበር። ግቢያችን ውስጥ ለዋና የሚያገለግል ጥሩ ኩሬ አለ፤ ልጆቹን እየጋበዝናቸው ብዙ ጊዜ ሊዋኙ ይመጡ ነበር። በመጡ ቁጥር የሚያደርጉት ነገር በጣም አሳቢና ሰው አክባሪ እንደሆኑ የሚያሳይ ነው። ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስተን ነበር፤ እንዲሁም እነሱ ሜዳው ላይ ሲሮጡ ማየት ይናፍቀናል።” በተጨማሪም “በጣም አስደሳች ጊዜ አሳልፈናል” ስትል ገልጻለች።

  • ሌላ የቤት አከራይ “ነዋሪዎቹ ጥሩ ተከራይ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ጎረቤቶችም ነበሩ” በማለት ተናግሯል።

የቤት አያያዝ

የቤቶቹ ባለቤቶች ተከራዮቹ ከለቀቁ በኋላ ያከራዩት ቤት ስላለበት ሁኔታ ምን ተሰምቷቸዋል?

  • “ሁልጊዜም ኪራያቸውን በሰዓቱ ይከፍሉ ነበር፤ ቤቱንም በደንብ የያዙት ሲሆን ለእኛ ያስረከቡን በጥሩ ሁኔታ ነው።”

  • ቀደም ሲል ከተጠቀሱት አከራዮች አንዱ እንዲህ ብሏል፦ “ቤታችንን በጥሩ ሁኔታ ስለያዛችሁልን እናንተንም ሆነ መላውን የመጠበቂያ ግንብ ድርጅት ማመስገን እፈልጋለሁ፤” አክሎም የይሖዋ ምሥክሮች “እንዲህ በደንብ” ያጸዳሉ ብሎ አስቦ እንደማያውቅ ተናግሯል።

  • አንዲት ሴት እንዲህ ስትል ገልጻለች፦ “ድርጅታችሁ ያለውን ጥሩ ስም ስለምናውቅ መያዣ [አልጠየቅንም]። ያከራየናቸው ሁለቱም ቤቶች ሲመለሱልን ምንም እንከን አላገኘንም።”

  • አንድ አከራይ የይሖዋ ምሥክሮቹ ቤቱ ላይ አንዳንድ ጥገና ካደረጉለት በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “የእናንተ ሰዎች እንዲሠሩልኝ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው? በሆነ ቀን ላይ እንደምትሠሩ ቃል ከገባችሁ ሁልጊዜም ባላችሁት ሰዓት ትሠራላችሁ። በአብዛኛው ጥገና የሚሠሩልኝ ሰዎች ቃላቸውን አያከብሩም።”

የማጠቃለያ አስተያየት

  • የአንዱ ቤት የኪራዩ ውል ከማብቃቱ በፊት አከራዩ የይሖዋ ምሥክሮቹ ውላቸውን ካደሱ በኪራዩ ላይ ከፍተኛ ቅናሽ እንደሚያደርግላቸው ገልጿል።

  • ሌላ አከራይ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “አጋጣሚው ከተገኘ በድጋሚ ለመጠበቂያ ግንብ ድርጅት ቤታችንን ማከራየት እንፈልጋለን።”