በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

የብሪታንያ ፎቶ ጋለሪ 2 (ከመስከረም 2015 እስከ ነሐሴ 2016)

የብሪታንያ ፎቶ ጋለሪ 2 (ከመስከረም 2015 እስከ ነሐሴ 2016)

በብሪታንያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በሚል ሂል፣ ለንደን ያለውን ቅርንጫፍ ቢሯቸውን ለቀው በስተምሥራቅ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኝ ቦታ (ቼልምስፎርድ፣ ኤሴክስ ከተማ አቅራቢያ) ሊዛወሩ ነው። ይህ የፎቶ ጋለሪ ከመስከረም 2015 እስከ ነሐሴ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ ከአዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ጋር በተያያዘ የተካሄደውን ሥራ የሚያሳይ ነው።

ጥቅምት 29, 2015—ዋናው ድጋፍ ሰጪ ጣቢያ

ሠራተኞች የግንባታ ማሽኖች ከሚጠገኑበት ጋራዥ ፊት ለፊት አርማታ ሲሞሉ።

ታኅሣሥ 9, 2015—ዋናው ድጋፍ ሰጪ ጣቢያ

የግንባታ ሠራተኞች በግንባታ ወቅት ለቢሮዎችና ለመመገቢያ አዳራሽ የሚያገለግለውን ሕንፃ ጣሪያ ሲያለብሱ።

ጥር 18, 2016—ዋናው ድጋፍ ሰጪ ጣቢያ

በዋናው መግቢያ በኩል አንድ ሠራተኛ የመቁረጫ መሣሪያ በተገጠመለት ኤክስካቫተር ተጠቅሞ የተመረጡ ዛፎችን ሲቆርጥ። መቁረጫው የዛፉን ግንድ ቆንጥጦ ከያዘው በኋላ ይቆርጠዋል፤ ከዚያም ኤክስካቫተሩ ዛፉን ተሸክሞ ከቦታው ያነሳዋል። ፕሮጀክቱ ከመጠናቀቁ በፊት፣ አካባቢውን የሚያስውቡ ሠራተኞች በተቆረጡት ዛፎች ምትክ በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ዛፎችን ይተክላሉ።

መጋቢት 31, 2016—የቅርንጫፍ ቢሮው ሕንፃ የሚሠራበት ቦታ

ሠራተኞች የቀድሞው ባለቤት መሬቱ ላይ የጣላቸውን ማናቸውንም የማይፈለጉ ነገሮች ሲያስወግዱ። ከዚያም አፈሩ ከጸዳ በኋላ መልሶ አገልግሎት ላይ ይውላል።

ሚያዝያ 14, 2016—የቅርንጫፍ ቢሮው ሕንፃ የሚሠራበት ቦታ

ሠራተኞች ተንቀሳቃሽ ቤቶችን በክሬን አንስተው ቦታቸው ላይ ለማስቀመጥ ሲዘጋጁ። የግንባታው ቋሚ ሠራተኞችና ሌሎች ጊዜያዊ ሠራተኞች እነዚህን ተንቀሳቃሽ ቤቶች የአገልግሎት መስጫ ክፍልና ቢሮ አድርገው ይጠቀሙባቸዋል።

ግንቦት 5, 2016—የቅርንጫፍ ቢሮው ሕንፃ የሚሠራበት ቦታ

ሠራተኞች ዳግመኛ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ነገሮችን በዓይነት በዓይነታቸው እየለዩ በተዘጋጀላቸው ማጠራቀሚያ ቦታዎች ውስጥ ሲጨምሩ። የግንባታ ፕሮጀክት ኮሚቴው ጉዳት የማያስከትሉ ቆሻሻዎችን ከመቅበር ይልቅ 95 በመቶ የሚያክለውን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ግብ አውጥቶ ነበር፤ በአሁኑ ጊዜ፣ ከተያዘው ዕቅድ በላይ ማከናወን ተችሏል። በተጨማሪም እንደ ሸክላ፣ አርማታና እንጨት ካሉ የሕንፃ ፍርስራሾች መካከል 89 በመቶ የሚሆነው ተሰብስቦ በዚሁ የግንባታ ፕሮጀክት ላይ በድጋሚ አገልግሎት ላይ እንዲውል ተዘጋጅቷል።

ግንቦት 23, 2016—የቅርንጫፍ ቢሮው ሕንፃ የሚሠራበት ቦታ

አንዲት የግንባታ ቡድኑ አባል እንደ ውኃና ኤሌክትሪክ ያሉ አገልግሎቶች የሚያልፉበት መስመር የሚቀበርበትን ጉድጓድ ስትሞላ። እነዚህ መስመሮች የግንባታ ሠራተኞቹ ለሚኖሩባቸው ጊዜያዊ መኖሪያዎች አገልግሎት ይሰጣሉ።

ግንቦት 26, 2016—የቅርንጫፍ ቢሮው ሕንፃ የሚሠራበት ቦታ

አንድ የግንባታ ሠራተኛ አፈሩ በሕንፃው ዙሪያ ለሚሠራው መንገድ ተስማሚ መሆን አለመሆኑን ለማጣራት የአፈር ናሙና ሲሰበስብ።

ግንቦት 31, 2016—የቅርንጫፍ ቢሮው ንድፍ

ይህ ንድፍ ግንቦት 31፣ 2016 በይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል ጸደቀ። የአካባቢው ባለሥልጣናትም ፈቃድ ሰጥተው ስለነበር የግንባታው ፕሮጀክት ተጀመረ።

ሰኔ 16, 2016—የቅርንጫፍ ቢሮው ሕንፃ የሚሠራበት ቦታ

ሠራተኞች ከግንባታ ቦታው ከተነሳው አፈር ውስጥ የማይፈለጉ ነገሮችን ለይተው ሲያስወግዱ። ከዚያም አፈሩ መልሶ ጥቅም ላይ ለመዋል ዝግጁ ይሆናል። ይህ ሥራ አፈሩን ከቦታው ለማስወገድም ሆነ በቦታው የሚሞላ ሌላ ነገር ለመግዛት የሚወጣውን ወጪ ያስቀራል።

ሰኔ 20, 2016—የቅርንጫፍ ቢሮው ሕንፃ የሚሠራበት ቦታ

ሠራተኞች ዋናው መግቢያ መንገድ የሚሠራበትን ቦታ ሲጠርጉ። ሙሉውን ወር ከባድ ዝናብ ይጥል ስለነበር በአካባቢው ከባድ ረግረግ የተፈጠረ ቢሆንም ሥራው አልተቋረጠም።

ሐምሌ 18, 2016—ዋናው ድጋፍ ሰጪ ጣቢያ

አቧራው እንዳይነሳ ለማድረግ ሲባል መንገዶች ውኃ ሲርከፈከፍባቸው። የግንባታ ፕሮጀክት ኮሚቴው የአካባቢውን የፕላን መመሪያ ማክበሩን የሚቆጣጠረው ኮንሲደሬት ኮንስትራክተርስ ስኪም የተባለው ድርጅት ካወጣቸው ደንቦች አንዱ የግንባታ ቦታዎች ንጽሕናቸው እንዲጠበቅ ያዛል። ድርጅቱ ያወጣው ደንብ ለማኅበረሰቡና ለሰዎች አክብሮትና አሳቢነት ማሳየትን ስለሚያበረታታ ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር ይስማማል።

ሐምሌ 18, 2016—ዋናው ድጋፍ ሰጪ ጣቢያ

አንዲት የግንባታ ሠራተኛ የአየር መቆጣጠሪያ ቧንቧዎችን የሚሸከመው ማስቀመጫ የሚንጠለጠልባቸውን ባለ ጥርስ ብረቶች ስትቆርጥ።

ሰኔ 22, 2016—የቅርንጫፍ ቢሮው ሕንፃ የሚሠራበት ቦታ

ሠራተኞች 20,000 ሜትር ኩብ የሚሆን የአፈርና የጠጠር ድብልቅ ሲለዩ። በፎቶግራፉ መካከለኛ ክፍል ላይ እንደሚታየው ድብልቁ አፈር ወደ ማጣሪያ መሣሪያው ይጨመራል። የተለያየ ስፋት ያላቸውን ወንፊቶች በመጠቀም ትላልቅና መካከለኛ መጠን ያላቸው ድንጋዮች ከተለዩ በኋላ ደቃቁ አፈር ወደታች ይወርዳል። በሦስት ጎኖች የተገጠሙት ማንሸራተቻዎች የተለዩትን ነገሮች ጭነት መኪኖች ላይ ይጭናሉ።

ሐምሌ 22, 2016—የቅርንጫፍ ቢሮው ሕንፃ የሚሠራበት ቦታ

የግንባታ ሠራተኞች ሕንፃውን በተፈቀደው የከፍታ መጠን ላይ ለመገንባት ከፍተኛ መጠን ያለው አፈር ወደ ሌላ ቦታ ሲወስዱ።

ነሐሴ 18, 2016—የቅርንጫፍ ቢሮው ሕንፃ የሚሠራበት ቦታ

በፎቶግራፉ መካከለኛ ክፍል በስተግራ በኩል እንደሚታየው የግንባታ ሠራተኞች የመኖሪያ ቤቶች ሕንፃ መሠረት ግንባታ መጀመር እንዲችል መሬቱን የመደልደሉን ሥራ አጠናቀዋል። ከዚያ በስተግራ ደግሞ ለ118 የግንባታ ሠራተኞች የሚበቃ የመኖሪያ ሕንፃ ተጠናቆ ይታያል።