በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

በዩናይትድ ስቴትስ የሚኙትን የቤቴል ሕንጻዎች እንድትጎበኝ ጋብዘንሃል

በዩናይትድ ስቴትስ የሚኙትን የቤቴል ሕንጻዎች እንድትጎበኝ ጋብዘንሃል

ከቫኑዋቱ ደሴት የመጡ አንድ ባልና ሚስት በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ከጎበኙ በኋላ “ቤቴልን መጎብኘታችን ዕድሜ ልካችንን የማንረሳው ልዩ ትዝታ ጥሎብን አልፏል” ብለዋል። በየዓመቱ ከ70 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ቤቴልን የሚጎበኙ ሲሆን እነሱም የእነዚህን ባልና ሚስት ስሜት ይጋራሉ።

አንተስ በዩናይትድ ስቴትስ ያለውን ቤቴል ጎብኝተሃል? ካልጎበኘህ እንዲህ እንድታደርግ እንጋብዝሃለን።

በዋነኞቹ ሦስት የቤቴል ሕንጻዎች ውስጥ ምን ሥራዎች ይከናወናሉ?

ብሩክሊን ኒው ዮርክ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት። በተመደበልህ አስጎብኚ አማካኝነት ይህን ሕንጻ ስትጎበኝ በዓለም ዙሪያ እየተካሄደ ያለውን ምሥራቹን የመስበኩን ሥራ ለማስተባበርና ለሥራው ድጋፍ ለመስጠት የሚደረገውን የተቀናጀ ጥረት መመልከት ትችላለህ። በተጨማሪም ሁለት ዐውደ ርዕዮችን ያለአስጎብኚ የማየት አጋጣሚ ታገኛለህ። አንደኛው “ለይሖዋ ስም የሚሆን ሕዝብ” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን የይሖዋ ሕዝቦች ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አንስቶ እስከ ዘመናችን ድረስ ያሳለፉትን ታሪክ የሚያስቃኝ ነው። ሌላው ደግሞ “መጽሐፍ ቅዱስ እና መለኮታዊው ስም” የሚል ርዕስ አለው፤ በዚህ ዐውደ ርዕይ ላይ የአምላክን ስም የያዙ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ለእይታ ቀርበዋል።

ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ የሚገኘው የትምህርት ማዕከል። በዚህ ማዕከል ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ ትምህርት ቤቶች፣ ለምሳሌ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤትን እንዲሁም ለቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀውን ትምህርት ቤት በተመደበልህ አስጎብኚ አማካኝነት መጎብኘት ትችላለህ። በተጨማሪም የሥዕል፣ የኦዲዮ/ቪዲዮ፣ የሕግና የአገልግሎት ክፍሎችን ጨምሮ በተለያዩ ቢሮዎች ውስጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን የሚያሳዩ ትዕይንቶችንና ቪዲዮዎችን ማየት ትችላለህ።

በዎልኪል፣ ኒው ዮርክ የሚገኙት የጽሑፍ ማተሚያና መላኪያ ሕንፃዎች። መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የሚታተሙት፣ የሚጠረዙት እንዲሁም በዮናይትድ ስቴትስ፣ በካሪቢያንና በሌሎች አካባቢዎች ወደሚገኙ ጉባኤዎች የሚላኩት እንዴት እንደሆነ በተመደበልህ አስጎብኚ አማካኝነት መጎብኘት ትችላለህ።

እነዚህን ሕንጻዎች መጎብኘት ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?

በብሩክሊን የሚገኘውን ቤቴል ለመጎብኘት አንድ ሰዓት ገደማ ይወስዳል፤ በፓተርሰን የሚገኘውን ቤቴል ለመጎብኘት ሁለት ሰዓት ገደማ፣ በዎልኪል የሚገኘውን ቤቴል ለመጎብኘት ደግሞ አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ ይወስዳል።

አስጎብኚዎቹ እነማን ናቸው?

አስጎብኚዎቹ በቤቴል በሚገኙ የተለያዩ ዲፓርትመንቶች ውስጥ የሚያገለግሉት ቤቴላውያን ናቸው። በዚህ ረገድ የሚያደርጉትን ተሳትፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው የማስተማር ሥራ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይሰማቸዋል። በግንቦት 2014 በእነዚህ ሦስት ቤቴሎች ውስጥ ከ5,000 በላይ ፈቃደኛ ሠራተኞች ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል ከ3,600 በላይ የሚሆኑት የአስጎብኚነት ስልጠና ወስደዋል። ጉብኝቱን ወደ 40 ገደማ በሚሆኑ ቋንቋዎች ማካሄድ ይቻላል።

ጉብኝቱ ምን ያህል ያስከፍላል?

ጉብኝቱ የሚካሄደው ያለክፍያ ነው።

እነዚህን ቦታዎች ለመጎብኘት የግድ የይሖዋ ምሥክር መሆን ያስፈልጋል?

በፍጹም። እንዲያውም አብዛኞቹ ጎብኚዎች የይሖዋ ምሥክሮች አይደሉም። የይሖዋ ምሥክሮችም ሆኑ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች እነዚህን ቦታዎች መጎብኘታቸው የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ እያከናወኑ ስላሉት ሥራ ይበልጥ እንዲያውቁ ያስችላቸዋል።

ከሕንድ የመጣች አንዲት የእስልምና እምነት ተከታይ ፓተርሰንን ጎብኝታ ነበር። ከጉብኝቱ በኋላ “እኔም የዚህ ድርጅት አባል መሆን እፈልጋለሁ። በአክብሮት ስለያዛችሁኝ እጅግ አመሰግናለሁ” ብላለች።

ልጆች መጎብኘት ይችላሉ?

እንዴታ! ልጆች እንዲህ ያለ ጉብኝት ማድረጋቸው በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድርባቸው ይችላል። ጆን የተባለ ከዩናይትድ ስቴትስ የመጣ አንድ ጎብኚ እንዲህ ብሏል፦ “አብረውን የጎበኙት ልጆች ወደ ቤት ከተመለስን በኋላም በጉብኝታቸው ወቅት ስላዩአቸው ነገሮች ማውራታቸውን አላቆሙም። ከጉብኝቱ በፊት ቤቴል ማገልገል ሲባል ምን እንደሆነ በውል የሚያውቁት ነገር አልነበረም፤ አሁን ግን ቤቴል ገብተው ለማገልገል ግብ አውጥተዋል።”

በሌሎች አገሮች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎችን መጎብኘት ይቻላል?

አዎ፣ በብዙ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎችንም መጎብኘት ይቻላል። ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ የሚገኙበትን አድራሻ ለማወቅ ከቢሮዎቻችንና ከጉብኝት ጋር የተያያዘ መረጃ የሚገኝበትን ገጽ ተመልከት። የይሖዋ ምሥክሮች ቅርጫፍ ቢሮዎችን መጥተህ እንድትጎበኝ በአክብሮት ጋብዘንሃል።