በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

በ60 ቀን የጊዜ ገደብ ውስጥ ሥራውን ማጠናቀቅ

በ60 ቀን የጊዜ ገደብ ውስጥ ሥራውን ማጠናቀቅ

የበላይ አካል አባል የሆነው አንቶኒ ሞሪስ ሐምሌ 5, 2013፣ ዓርብ ዕለት በዩናይትድ ስቴትስ ለሚኖሩ የቤቴል ቤተሰብ አባላት የተናገረው የሚከተለው ማስታወቂያ የቤተሰቡን አባላት በሙሉ አስደስቶ ነበር፦ “በብሩክሊን በ117 አዳምስ ስትሪት እና በ90 ሳንድስ ስትሪት ላይ የሚገኙትን ስድስት ሕንፃዎች ለመሸጥ ስምምነት ላይ ተደርሷል። * አምስቱን ሕንፃዎች በዚህ ዓመት እስከ ነሐሴ አጋማሽ ድረስ መልቀቅ ይኖርብናል።”

ይህን ማድረግ ብዙ ሥራ እንደሚጠይቅ ግልጽ ነው። የአምስቱ ሕንፃዎች አጠቃላይ ስፋት ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚችሉ 11 የእግር ኳስ ሜዳዎችን ያክላል! ያም ሆኖ ሕንፃዎቹ በ60 ቀናት ውስጥ መለቀቅ ነበረባቸው!

ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የማተሚያ ማሽኖችና የመጻሕፍት መጠረዣ መሣሪያዎች የነበሩት በእነዚህ አምስት ሕንፃዎች ውስጥ ነበር፤ ይሁን እንጂ በ2004 እነዚህ ማሽኖች በዎልኪል፣ ኒው ዮርክ ወደሚገኝ ቦታ እንዲዛወሩ ተደርጓል።

ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሕንፃዎቹ ለመጋዘንነትና የጥገና ሥራዎች የሚከናወኑባቸው ቦታዎች በመሆን አገልግለዋል፤ በመሆኑም ሕንፃዎቹ በግንባታ ቁሳቁሶች፣ በቢሮ ዕቃዎች እንዲሁም በዩናይትድ ስቴትስና በሌሎች አገሮች የሚከናወኑ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማገዝ ታስበው በተዘጋጁ ዕቃዎች የተሞሉ ነበሩ።

በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሕንፃዎቹን ለቅቆ ለመውጣት ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድ መንደፍ ያስፈልግ ነበር። በመጀመሪያ የትኞቹ ዕቃዎች መሸጥ፣ መወገድ ወይም መቀመጥ እንዳለባቸው ለመወሰን በሕንፃዎቹ ውስጥ ያሉት ዕቃዎች ተቆጥረው እንዲመዘገቡ ተደረገ። ከዚያም ሥራውን ለአደጋ በማያጋልጥና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት ተደረገ።

የቤቴል ቤተሰብ አባላት ይህን ፕሮጀክት ለመደገፍ በትጋት ሠርተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ሥራ እገዛ ለማድረግ 41 ጊዜያዊ ፈቃደኛ ሠራተኞች ወደ ቤቴል እንዲመጡ ተጋብዘው ነበር። ፈቃደኛ ሠራተኞቹ የመጡት በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ነው። አብዛኞቹ ያላገቡና ጠንካራ ወጣት ወንዶች ናቸው። ወደ ቤቴል እንዲመጡ የቀረበላቸውን ግብዣ የተቀበሉት እነዚህ ወጣቶች ከስድስት እስከ አሥር ሳምንታት ለማገልገል ሲሉ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው መለየት እንዲሁም ሥራቸውን ትተው መምጣት ነበረባቸው። ታዲያ በዚህ ሥራ ላይ በመሳተፋቸው ምን ተሰማቸው?

ከዋሽንግተን የመጣው የ21 ዓመቱ ጆርዳን “ቀደም ብዬ አመልክቼ ቢሆን ኖሮ በጣም ደስ ይለኝ ነበር” ብሏል።

የ20 ዓመቱ ስቲቨን የመጣው ከቴክሳስ ነው። ስቲቨን እንዲህ ብሏል፦ “ትጉህ እና ደስተኛ የሆኑ አባላት ያሉት ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ አባል እንደሆንኩ ተሰምቶኛል።”

የ23 ዓመቱ ጀስቲን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ቤቴል ልክ እንደ ቤቴ ነው የሚሰማኝ። በቤቴል የሚገኙት ወንድሞች ያላቸው ጥበብ፣ ፍቅር እንዲሁም ኅብረት እጅግ አስደናቂ ነው።”

ከፖርቶ ሪኮ የመጣው የ20 ዓመቱ አድለር “በማለዳ ከእንቅልፍ መነሳት ተፈታታኝ ሆኖብኝ ነበር፤ ያም ቢሆን ለዘላለም የሚዘልቅ ወዳጅነት የመመሥረት አጋጣሚ አግኝቻለሁ” ብሏል።

የ21 ዓመቱ ዊልያም ደግሞ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ከልጅነቴ ጀምሮ ቤቴል የመግባት ምኞት ነበረኝ። ቤቴል ስገባ ብቸኝነት እንደሚሰማኝ አስብ ነበር፤ ነገር ግን ይህ አመለካከቴ ትክክል አልነበረም። እስካሁን ካጋጠሙኝ ጥሩ ነገሮች ሁሉ የበለጠው በቤቴል ያሳለፍኩት ጊዜ ነው! እዚህ ከመኖር የተሻለ ነገር ሊኖር እንደማይችል እስከ ማሰብ ደርሼያለሁ።”

እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሥራውን በተሰጣቸው ቀነ ገደብ ማጠናቀቅ ችለው ይሆን? እንዴታ! በ55 ቀናት ብቻ ሥራውን ማጠናቀቅ ችለዋል።

^ አን.2 በ90 ሳንድስ ስትሪት ላይ የሚገኘው የመኖሪያ ሕንፃ የሚለቀቀው በ2017 ነው።