በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ለመርከበኞች ምሥራቹን ማድረስ

ለመርከበኞች ምሥራቹን ማድረስ

በመላው ዓለም 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ መርከበኞች እንዳሉ ይገመታል። መርከበኞች በየጊዜው ከአንድ ወደብ ወደ ሌላ ወደብ ይንቀሳቀሳሉ፤ ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች በተቻለ መጠን በርካታ መርከበኞችን አግኝተው የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ሊያካፍሏቸው የሚችሉት እንዴት ነው? አንድ መርከብ ወደብ ላይ ደርሶ ሲቆም፣ ሥልጠና ያገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ መርከቡ ገብተው በመርከቡ ላይ ለሚሠሩ መኮንኖችና ሌሎች ሠራተኞች በሚፈልጉት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ለማስተማርና ጽሑፍ ለመስጠት ጥረት ያደርጋሉ።

ይህ ጥረት ምን ውጤት አስገኝቷል? በካናዳ በሚገኘው ቫንኩቨር ወደብ ላይ የሚያገለግለው ስቴፋኖ እንዲህ ብላል፦ “አንዳንድ ሰዎች ሁሉም መርከበኞች አስቸጋሪ ባሕርይ እንዳላቸው ያስባሉ። እርግጥ እንዲህ ያለ ባሕርይ ያላቸው ጥቂት መርከበኞች መኖራቸው ባይካድም እኛ ያገኘናቸው አብዛኞቹ መርከበኞች ግን ትሑቶችና የማወቅ ጉጉት ያላቸው ናቸው። ብዙዎቹ በአምላክ የሚያምኑና የእሱን በረከት ማግኘት የሚፈልጉ ስለሆኑ ሞቅ ያለ አቀባበል ያደርጉልናል።” ከመስከረም 2015 እስከ ነሐሴ 2016 ባሉት ወራት፣ የይሖዋ ምሥክሮች በቫንኩቨር በሚገኘው ወደብ ላይ ብቻ ከ1,600 ለሚበልጥ ጊዜ መርከቦች ውስጥ ገብተው ለሰዎች መስበክ ችለዋል። መርከበኞቹ በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ በሺዎች የሚቆጠሩ ጽሑፎችን የወሰዱ ሲሆን ከ1,100 በላይ የሚሆኑት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረዋል።

ከመርከበኞቹ ጋር የተጀመረውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት መቀጠል የሚቻለው እንዴት ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ባሉ ወደቦች አካባቢ ስለሚገኙ የጀመሩትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት መቀጠል የሚፈልጉ መርከበኞች ቀጥሎ በሚቆሙበት ወደብ ላይ አንድ ሰው መጥቶ እንዲያነጋግራቸው ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ። ለምሳሌ በቫንኩቨር የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ግንቦት 2016፣ በአንድ ዕቃ ጫኝ መርከብ ውስጥ ዋና ምግብ አዘጋጅ ሆኖ የሚሠራ ዋርሊቶ የተባለ ሰው ተዋወቁ። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? የተባለውን ቪዲዮ አሳዩትና ከአምላክ የተላከ ምሥራች! በተባለው ብሮሹር ተጠቅመው መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠኑት ጀመር። ዋርሊቶ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያደረገው ውይይት ስላስተደሰተው መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቱን መቀጠል ፈለገ፤ ሆኖም እሱ የሚሠራበት መርከብ ቀጥሎ የሚቆመው ፓራናግዋ የተባለ ርቆ የሚገኝ የብራዚል ወደብ ላይ ነው።

ከአንድ ወር ገደማ በኋላ መርከቡ ፓራናጉዋ ወደብ ላይ ሲቆም ሁለት ብራዚላውያን የይሖዋ ምሥክሮች ወደ መርከቧ መግቢያ በመምጣት ዋርሊቶን መፈለግ ጀመሩ፤ ዋርሊቶም ሰዎቹ እሱን በስም ጠቅሰው እየፈለጉት እንደሆነ ሲያውቅ ማመን አቃተው! እነሱም በቫንኩቨር የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች መወያየት የሚፈልግ መሆኑን እንዳሳወቋቸው ገለጹለት። ዋርሊቶ በብራዚል ካሉት ከእነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘቱ ያስደሰተው ሲሆን ውይይቱ እንዳይቋረጥበት ለተደረገለት ዝግጅት የተሰማውን ልባዊ ምስጋና ገልጿል። ከዚህ ቀጥሎ በሚሄድበት ወደብ ላይ ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ለመቀጠል ተስማምቷል።