በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች የተባለው መጽሐፍ ትምህርት ቤት ገባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች የተባለው መጽሐፍ ትምህርት ቤት ገባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች የተባለው መጽሐፍ በፓንጋሲናን ቋንቋ በ2012 ተተርጉሞ የወጣ ሲሆን ፊሊፒንስ ውስጥ ይህን ቋንቋ የሚናገሩ ተማሪዎች በዚህ መጽሐፍ እየተጠቀሙ ነው። ይህ መጽሐፍ፣ የፊሊፒንስ የትምህርት ሚኒስቴር በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ያወጣውን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚጠቅም ነው።

በፊሊፒንስ ከ100 በላይ ቋንቋዎች ስለሚነገሩ ልጆች በትምህርት ቤት ውስጥ በየትኛው ቋንቋ መማር እንዳለባቸው የተነሳው ሐሳብ ለረጅም ጊዜ ሲያከራክር ቆይቷል። የትምህርት ሚኒስቴሩ በ2012 ባወጣው መግለጫ ላይ፣ “ቤት ውስጥ የሚነገረውን ቋንቋ መጠቀም” ትምህርቱን ለልጆች “በተሻለ መንገድና በፍጥነት” ለማስተላለፍ እንደሚያስችል መገንዘቡን ገልጿል። በመሆኑም በፊሊፒንስ “በአፍ መፍቻ ቋንቋ ላይ ተመሥርቶ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚሰጥ የትምህርት ሥርዓት” ተዘርግቷል።

ትምህርት እንዲሰጥባቸው ከተመረጡት ቋንቋዎች አንዱ ፓንጋሲናን ነው። ሆኖም አንድ እንቅፋት የሆነ ነገር ነበር። በፓንጋሲናን ቋንቋ የተዘጋጁ መጻሕፍት በጣም ጥቂት እንደሆኑ አንድ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ገልጿል። በፓንጋሲናን ቋንቋ የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለው መጽሐፍ የወጣው ኅዳር 2012 በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ነበር፤ በእርግጥም የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፉን ያወጡት ጥሩ ጊዜ ላይ ነው።

በስብሰባው ላይ የዚህ መጽሐፍ 10,000 ቅጂዎች ተሰራጭተዋል። ትናንሽ ልጆችና ወላጆቻቸው መጽሐፉን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል። አንድ ባልና ሚስት “ልጆቻችን መጽሐፉን በደንብ ስለሚረዱት ወደውታል” ብለዋል።

ልክ ስብሰባው እንዳለቀ የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች የተባለውን መጽሐፍ በዳጉፓን ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ ትምህርት ቤት ይዘው ሄዱ። በዚያ የነበሩ አስተማሪዎች በፓንጋሲናን የተዘጋጁ መጻሕፍት ለማግኘት ተቸግረው ስለነበረ ይህን መጽሐፍ በማግኘታቸው ተደስተዋል። ከ340 የሚበልጡ መጻሕፍት ተሰራጭተዋል። አስተማሪዎቹ ልጆቹን በራሳቸው ቋንቋ ንባብ ለማስተማር ወዲያውኑ በዚህ መጽሐፍ መጠቀም ጀምረዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች ይህ መጽሐፍ ትናንሽ ልጆችን ለማስተማር ጥቅም ላይ መዋሉ ያስደስታቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ በመተርጎሙ ሥራ ላይ ከተካፈሉት ተርጓሚዎች አንዱ እንዲህ ብሏል፦ “የሰዎችን ልብ ለመንካት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ጽሑፎችን ማዘጋጀት ጠቃሚ መሆኑን እኛ አስቀድመን ተገንዝበን ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ለመተርጎም ጥረት የሚያደርጉት በዚህ ምክንያት ነው።”