በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጉልበተኛ ልጆች የሚሰነዝሩትን ጥቃት ለመቋቋም የሚረዳ ጠቃሚ መረጃ

ጉልበተኛ ልጆች የሚሰነዝሩትን ጥቃት ለመቋቋም የሚረዳ ጠቃሚ መረጃ

በ2014 የአሥር ዓመቱ ህዩጎ በብሪታንያ ካለ አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት የዳያና ሽልማት አገኘ፤ ሽልማቱን ለማግኘት የበቃው በትምህርት ቤቱ ያሉ ተማሪዎች፣ ጉልበተኛ ልጆች የሚሰነዝሩባቸውን ጥቃት መቋቋም የሚቻልበትን ዘዴ በማስረዳት ላከናወነው ተግባር ነው።

ህዩጎ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ሽልማት እንዳገኝ የረዳኝ ቡጢ ሳትሰነዝር ጉልበተኞችን ማሸነፍ የተባለው የነጭ ሰሌዳ አኒሜሽን ነው። ጉልበተኛ ልጆች የሚሰነዝሩትን ጥቃት መከላከል ስለሚቻልበት ዘዴ ለሌሎች በማስተማር ረገድ ሊሳካልኝ የቻለው jw.org ላይ ከወጣው ቪዲዮ ጥሩ ትምህርት ስላገኘሁ ነው።”

“በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ልጆችም የጉልበተኞች ጥቃት ይደርስባቸዋል። . . . ሆኖም . . . አይዞህ መፍትሔ አለው።” (ቡጢ ሳትሰነዝር ጉልበተኞችን ማሸነፍ ከተባለው ቪዲዮ የተቀነጨበ)

ህዩጎ ቡጢ ሳትሰነዝር የተባለውን አኒሜሽን መጀመሪያ ለአስተማሪዎቹ አሳያቸው። እነሱም ቪዲዮውን በጣም ስለወደዱት jw.org የተባለውን ድረ ገጽ ሁሉም ተማሪዎች ሊያገኙት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻች አደረጉ። ህዩጎ በሚማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ ያሉ ከስምንት እስከ አሥር ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ተማሪዎች አሁን jw.org​ን አዘውትረው ይጠቀማሉ። ድረ ገጹ ከጉልበተኛ ልጆች ራሳቸውን እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ መጠቆም ብቻ ሳይሆን ‘እውነተኛ ጓደኛ ማፍራት የምችለው እንዴት ነው?’ እንደሚሉ ላሉ ጥያቄዎቻቸውም መልስ እንደሰጣቸው ተናግረዋል።

ወጣቶችን የሚጠቅሙ ውጤታማ ዘዴዎች

ብሪታንያ ውስጥ በሚገኝ ሌላ ትምህርት ቤት የሚማረው የስምንት ዓመቱ ኤላይጃ ጉልበተኛ ልጆች ያስቸግሩት ነበር። እሱና ቤተሰቡ ቡጢ ሳትሰነዝር የተባለውን ቪዲዮ አብረው ሆነው ተመለከቱት። ጉልበተኛ ልጆች ሲያስቸግሩት ምን ማድረግና ምን ማለት እንደሚኖርበትም አብረው ተለማመዱ። ይህ ደግሞ ኤላይጃ በራሱ በመተማመን ችግሩን በተሳካ ሁኔታ እንዲወጣ አስችሎታል። በኋላም “የፀረ ጉልበተኛ ልጆች ሳምንት” በሚከበርበት ወቅት አስተማሪው ቪዲዮውን በትምህርት ቤቱ ውስጥ ለሚማሩ ተማሪዎች በሙሉ አሳያቸው።

እርግጥ ነው፣ ጉልበተኛ ልጆች ችግር የሚፈጥሩት በብሪታንያ ብቻ አይደለም። ይህ በመላው ዓለም ያለ ችግር ነው፤ ቡጢ ሳትሰነዝር የተባለው የነጭ ሰሌዳ አኒሜሽን በየትኛውም አገር የሚኖሩ ወጣቶችን እየረዳቸው ነው።

በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው የአሥር ዓመቷ አቪ በክፍሏ ውስጥ ያለችን አንዲት ጉልበተኛ ልጅ በጣም ትፈራት ነበር። ቡጢ ሳትሰነዝር የተባለውን ቪዲዮ ከተመለከተች በኋላ ልጅቷን ለመጋፈጥ ድፍረት አገኘች። ስለ ችግሩ ለአስተማሪዋም ነገረችው፤ እሱም ረዳት። ታስቸግራት የነበረችው የክፍሏ ተማሪ ይቅርታ የጠየቀቻት ሲሆን አሁን ተስማምተው ይማራሉ።

የይሖዋ ምሥክሮች የወጣቶች ደኅንነት በጣም ያሳስባቸዋል። በመሆኑም ጉልበተኛ ልጆች እንደሚሰነዝሩት ጥቃት ያሉ ችግሮችን ጨምሮ ወጣቶች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት የሚረዷቸውን ጠቃሚ ሐሳቦች ማዘጋጀታችንን እንቀጥላለን።