በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

JW.ORG የሰዎች ሕይወት እንዲሻሻል እየረዳ ነው

JW.ORG የሰዎች ሕይወት እንዲሻሻል እየረዳ ነው

በምድር ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች ከjw.org ጥቅም እያገኙ ነው። ከግንቦት 2014 ወዲህ ይህን ድረ ገጽ በተመለከተ ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ከተላኩት በርካታ የአድናቆት መግለጫዎች መካከል እስቲ ጥቂቶቹን እንመልከት።

ድረ ገጹ ሕፃናትን እየጠቀመ ነው

“ልጄ ከሕፃናት መዋያ ሲመለስ አብረውት የሚውሉትን ልጆች እርሳስና ትናንሽ አሻንጉሊቶች አልፎ ተርፎም መነጽሮች ይዞ የመምጣት ልማድ ነበረው። ይህን ማድረጉ እንደ ሌብነት እንደሚቆጠር ሌብነት ደግሞ ትክክል እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ልናስረዳው ሞክረን ነበር። ይሁንና ጥረታችን የተሳካው መስረቅ መጥፎ ነው በሚል ርዕስ jw.org ላይ የወጣውን ቪዲዮ ካየን በኋላ ነበር። ልጃችን ከዚህ ቪዲዮ ጥሩ ትምህርት ያገኘ ከመሆኑም ሌላ ለእሱ ታስቦ የተዘጋጀ ያህል ነበር። ቪዲዮውን ከተመለከተ በኋላ ወስዷቸው የነበሩትን ዕቃዎች በሙሉ መመለስ እንደሚፈልግ ነገረን፤ ምክንያቱም አምላክ መስረቅን እንደሚጠላ በሚገባ ተረድቶ ነበር። በእርግጥም ይህ ድረ ገጽ በእጅጉ ጠቅሞናል!”—ዲ. ኤን. ከአፍሪካ

ልጃችን መስረቅ መጥፎ ነው በሚል ርዕስ በjw.org ላይ ከወጣው . . . ቪዲዮ ጥሩ ትምህርት ያገኘ ከመሆኑም ሌላ ለእሱ ታስቦ የተዘጋጀ ያህል ነበር”

“ልጆቼ ይህን ድረ ገጽ ይወዱታል። አጫጭር የአኒሜሽን ቪዲዮዎችን ከድረ ገጹ ላይ የሚያወርዱ ሲሆን ቪዲዮዎቹ መዋሸትንና መስረቅን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን መመሪያ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አስችለዋቸዋል። በተጨማሪም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ሊጠቅሟቸው የሚችሉ ሌሎች አስፈላጊ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ ረድተዋቸዋል፤ ይህም ጠቃሚ ዜጎች እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።”—ኦ. ደብሊው. ከዌስት ኢንዲስ

ድረ ገጹ ተማሪዎችን እየጠቀመ ነው

“ትምህርትን የማየው እንደ ሸክም ስለ ነበር ትምህርት ስለ ማቆም አስብ ነበር። ሆኖም አንድ ቀን፣ jw.org ላይ የወጣውን ‘ትምህርቴን ባቋርጥ ይሻል ይሆን?’ የሚለውን ርዕስ አነበብኩ። ይህም ለትምህርት ጥሩ አመለካከት እንዲኖረኝ ረድቶኛል። ርዕሱ፣ ትምህርት መቅሰሜ ለወደፊት ሕይወቴ የሚጠቅም ሥልጠና እንደሚሰጠኝና ኃላፊነት የሚሰማው ሰው እንድሆን እንደሚረዳኝ አስገንዝቦኛል።”—ኤን. ኤፍ. ከአፍሪካ

“በዚህ ድረ ገጽ ላይ ለወጣቶች የሚወጣው ምክር በትምህርት ቤት ጥሩ ሥነ ምግባር ማንጸባረቅ የምችለው እንዴት እንደሆነ እንዳስተውል ረድቶኛል”

“በዚህ ድረ ገጽ ላይ ለወጣቶች የሚወጣው ምክር በትምህርት ቤት ጥሩ ሥነ ምግባር ማንጸባረቅ የምችለው እንዴት እንደሆነ እንዳስተውል ረድቶኛል። ሐሳቤን ከሚከፋፍሉ ነገሮች በመራቅ ትምህርቴ ላይ ብቻ እንዴት ማተኮር እንደምችል አስተምሮኛል።”—ጂ. ከአፍሪካ

“አንዲት የሥራ ባልደረባዬ፣ ትምህርት ቤት ውስጥ ጉልበተኞች ሴት ልጇን እንደሚያስቸግሯት በተለይ ደግሞ አንዲት ልጅ በጣም እንደምታስቸግራት ስትናገር ሰማሁ። ልጅቷ በዚህ ነገር በጣም ከመረበሿና ከመፍራቷ የተነሳ ለጥቂት ቀናት ከትምህርት ቤት ቀርታ ነበር። እኔም jw.org ላይ ከወጣው ቡጢ ሳትሰነዝር ጉልበተኞችን ማሸነፍ ከሚለው የነጭ ሰሌዳ አኒሜሽን ያገኘኋቸውን ነጥቦች ለሥራ ባልደረባዬ ነገርኳት። እሷም በተለይ ቀልድ በመፍጠር ሁኔታውን ለማርገብ መሞከር ጥሩ እንደሆነ የሚገልጸውን ሐሳብ ወደደችው። ከዚያም ጉልበተኞች ሲያስቸግሯት ምን ማድረግ እንደምትችል ከልጇ ጋር ተነጋገሩ። በመሆኑም ልጅቷ በራስ የመተማመን መንፈስ ኖሯት ወደ ትምህርት ገበታዋ ተመለሰች። ከጊዜ በኋላ ሁኔታዎች የተሻሻሉ ሲሆን ታስቸግራት ከነበረችው ልጅ ጋርም መግባባት ችለዋል።”—ቪ. ኬ. ከምሥራቅ አውሮፓ

ድረ ገጹ ወጣቶችን እየጠቀመ ነው

“‘ሰውነቴን የምቆርጠው ለምንድን ነው?’ በሚል ርዕስ በድረ ገጻችሁ ላይ ስላወጣችሁት ትምህርት አመሰግናችኋለሁ። ለብዙ ጊዜያት ከዚህ ችግር ጋር ስታገል ቆይቻለሁ። ይህ ዓይነት ችግር ያለብኝ እኔ ብቻ እንደሆንኩና ለሌሎች ብናገር ያለሁበትን ሁኔታ ሊረዱልኝ እንደማይችሉ ይሰማኝ ነበር። በርዕሱ ላይ የተጠቀሱት ታሪኮች በጣም ረድተውኛል። በመጨረሻ ስሜቴን የሚረዳልኝ አገኘሁ!”—በአውስትራሊያ የምትኖር አንዲት ሴት

“በርዕሱ ላይ የተጠቀሱት ታሪኮች በጣም ረድተውኛል። በመጨረሻ ስሜቴን የሚረዳልኝ አገኘሁ!”

“jw.org ወጣቶችን የሚመለከቱ ሐሳቦችን በቀላሉ ለማግኘት አስችሎኛል። ለምሳሌ አንዱ ርዕስ የፆታ ትንኮሳ ዓይነቶችን እንዳውቅ እንዲሁም እኔም የዚህ ችግር ተጠቂ እንደሆንኩ እንዳስተውልና ችግሩን በትክክለኛው መንገድ መፍታት የምችለው እንዴት እንደሆነ እንዳውቅ ረድቶኛል።”—ቲ. ደብሊው. ከዌስት ኢንዲስ

ድረ ገጹ ወላጆችን እየጠቀመ ነው

“በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጄ ቅብጥብጥ ነው። ቅብጥብጥ መሆኑና ፈጽሞ ያልተጠበቁ ነገሮችን ማድረጉ ብዙ ጊዜ ያበሳጨኛል። ስለሆነም መግባባት ይቸግረናል። አንድ ቀን jw.orgን ከፍቼ ስለ ባለትዳሮችና ወላጆች የሚናገረውን ክፍል መመልከት ጀመርኩ። በዚህ ጊዜ የገጠመኝን ችግር ለመፍታት የሚረዱ ሐሳቦችን የያዙ በርካታ ርዕሶችን ተመለከትኩ፤ ከእነዚህ ርዕሶች፣ ልጄን እንዴት ማነጋገር እንዳለብኝ ተምሬያለሁ። እሱም ቢሆን ከዚህ ድረ ገጽ ጠቃሚ ትምህርት አግኝቷል። አሁን፣ የሚያስደስተውንም ሆነ የሚያስጨንቀውን ጨምሮ በልቡ ያለውን ሁሉ በግልጽ ያጫውተኛል።”—ሲ. ቢ. ከአፍሪካ

“ብዙውን ጊዜ ልጆቻችን የሚገጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት የሚያስችሏቸው ትምህርቶች ልክ በአስፈላጊው ጊዜ በjw.org ላይ ይወጡልናል”

“jw.org ልጆቻችንን በጨዋታ መልክ ማስተማር የምንችልባቸውን ግሩም መንገዶች እንድናውቅ ረድቶናል። ለምሳሌ ያህል እውነተኛ ጓደኛ ማግኘት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጸው የነጭ ሰሌዳ አኒሜሽን ልጆቻችን ስለ ጓደኝነት ተገቢው አመለካከት እንዲኖራቸው እንዲሁም በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩባቸው የሚችሉ ወዳጆችን እንዲመርጡ ረድቷቸዋል። ብዙውን ጊዜ ልጆቻችን የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት የሚያስችሏቸው ትምህርቶች ልክ በአስፈላጊው ጊዜ በjw.org ላይ ይወጡልናል። ጥሩ ምክር ለመስጠት የሚያችሉ በርካታ ጠቃሚ ሐሳቦችን ከድረ ገጹ ላይ ማግኘት ችለናል።”—ኢ. ኤል. ከአውሮፓ

ድረ ገጹ ባለትዳሮችን እየጠቀመ ነው

“እኔና ባለቤቴ ከተጋባን ስድስት ዓመታችን ነው። እንደ ሌሎች ባለትዳሮች ሁሉ ሐሳባችንን በምንገልጽበት መንገድ፣ ከአስተዳደግ በወረስናቸው ነገሮችና በአንዳንድ ነገሮች ላይ ባለን አመለካከት ረገድ ያሉንን ልዩነቶች ማስታረቅ ተፈታታኝ ሆኖብን ነበር። በአንድ ወቅት በjw.org ላይ የወጣው ‘ጥሩ አድማጭ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?’ የሚለው ርዕስ ትኩረቴን ሳበው። ይህ ርዕስ የማዳመጥ ችሎታን ማሻሻል የሚቻለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጹ ጠቃሚ ምክሮችን ይዟል። እኔም ሐሳቡን ካነበብኩ በኋላ ያነበብኩትን ለባለቤቴ ነገርኳት። አሁን እነዚህን ጠቃሚ ምክሮች ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው።”—ቢ. ቢ. ከዌስት ኢንዲስ

“ይህ ድረ ገጽ ትዳሬን ከመፍረስ ታድጎልኛል”

“ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘሁት ባለፈው ዓመት ሲሆን ስለ jw.org ያለኝን ልባዊ አድናቆት መግለጽ እፈልጋለሁ። ቁጣዬን መቆጣጠር እንዲሁም ጥሩ ባልና አባት መሆን እንድችል የረዱኝን ምክሮች ጨምሮ ከዚህ ድረ ገጽ ላይ ብዙ ትምህርት አግኝቻለሁ። ይህ ድረ ገጽ ትዳሬን ከመፍረስ ታድጎልኛል ብዬ መናገር እችላለሁ።”—ኤል. ጂ. ከዌስት ኢንዲስ

ድረ ገጹ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች እየጠቀመ ነው

“jw.org ዳግም እንደተፈጠርኩ ሆኖ እንዲሰማኝ አድርጎኛል። በአሜሪካ የምልክት ቋንቋ የተዘጋጁት ቪዲዮዎች የምልክት ቋንቋ ችሎታዬን እንዳሻሽል ረድተውኛል። በሕይወቴ ውስጥ የረባ ግብ ማውጣት እንደማልችል ሆኖ ይሰማኝ ነበር፤ የአምላክን ቃል በቋንቋዬ መመልከት የሚል ርዕስ ያለውን ቪዲዮ ካየሁ በኋላ ግን ልቤ በደስታ የተሞላ ከመሆኑም ሌላ በሕይወት መልካም ጎን ላይ ለማተኮር የወሰድኩት አቋም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተጠናክሯል።”—ጄ. ኤን. ከአፍሪካ

“jw.org ዳግም እንደተፈጠርኩ ሆኖ እንዲሰማኝ አድርጎኛል”

“ይህ ድረ ገጽ ውድ ዕንቁ ነው ሊባል ይችላል። የበጎ ፈቃድ ሠራተኛ ስሆን መስማት የተሳናቸውን ሰዎች በተለይም መስማት የተሳናቸውን ወጣቶች እረዳለሁ። በምልክት ቋንቋ የተዘጋጁት ብዙ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ቪዲዮዎች የምልክት ቋንቋ ችሎታዬን እንዳሻሽል ረድተውኛል። እንዲሁም ድረ ገጹ፣ የቤተሰብ ሕይወታቸውን እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሻሻል የሚፈልጉ ሰዎችን ለመርዳት አስችሎኛል።”—ኬ. ጄ. ከዌስት ኢንዲስ

ድረ ገጹ ዓይነ ስውራንን እየጠቀመ ነው

“ከjw.org ጥቅም ካገኙት ዓይነ ስውራን መካከል አንዱ እኔ ነኝ። ድረ ገጹ፣ በፖስታ ቢላኩልኝ ኖሮ እኔ ጋር ለመድረስ ወራት ሊፈጁ የሚችሉ መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት አስችሎኛል። እንዲሁም ድረ ገጹ የቤተሰቤ ሕይወት እንዲሻሻልና ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ ነገር ማከናወን እንድችል ረድቶኛል። ከዚህም በተጨማሪ ማየት ከሚችሉት ወዳጆቼ እኩል መረጃዎችን ማግኘት ችያለሁ።”—ሲ. ኤ. ከደቡብ አሜሪካ

“ድረ ገጹ የቤተሰቤ ሕይወት እንዲሻሻልና ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ ነገር ማከናወን እንድችል ረድቶኛል”

“ብሬይል ማንበብ ለማይችሉ ወይም በብሬይል የተዘጋጁ መጻሕፍትን የመግዛት አቅም ለሌላቸው ሰዎች jw.org ይህ ነው የማይባል ጥቅም እያስገኘላቸው ነው። አስተማሪ የሆኑት በድምፅ የተቀረጹ ጽሑፎች አንድ ዓይነ ስውር ስለተለያዩ ነገሮች እውቀት መቅሰም እንዲችል ይረዱታል። ይህ ድረ ገጽ ያለ አድልዎ ሁሉንም ሰዎች ለመጥቀም ታስቦ የተዘጋጀ ነው። እንደ እኔ ያሉ ዓይነ ስውራን እንደምንፈለግና የኅብረተሰቡ ክፍል እንደሆንን እንዲሰማን አድርጎናል።”—አር. ዲ. ከአፍሪካ

ድረ ገጹ በመንፈሳዊ የተራቡ ሰዎችን እየጠቀመ ነው

“ድረ ገጻችሁን ከሌሎች የሃይማኖት ድረ ገጾች ልዩ የሚያደርገው ቀሳውስት ብቻ ሊረዷቸው በሚችሉ አባባሎችና ቃላት የታጨቀ አለመሆኑ ነው። በተጨማሪም አንድ ሰው ግራ እስኪገባው ድረስ የመረጃ ናዳ አታወርዱበትም። በድረ ገጻችሁ ላይ ያሉት ሐሳቦች ግልጽና ለመረዳት ቀላል ናቸው። የተንዛዙ ወይም በፍልስፍና የተሞሉ አይደሉም። እምነት የተወሳሰበ ነገር እንደሆነ አድርገው አያቀርቡም። ከዚህ ይልቅ ማንኛውም ሰው እምነት ማዳበር እንደሚችል የሚያሳዩ ናቸው።”—ኤ. ጂ. ከእስያ

“በድረ ገጻችሁ ላይ ያሉት ሐሳቦች ግልጽና ለመረዳት ቀላል ናቸው። . . . ማንኛውም ሰው እምነት ማዳበር እንደሚችል የሚያሳዩ ናቸው”

“jw.org ባይኖር ኖሮ ሕይወቴ አሳዛኝ ይሆን ነበር! በመንፈሳዊ ጨለማ በተዋጠው በዚህ ዓለም ውስጥ ይህ ድረ ገጽ በፈለግኩት ጊዜ ማብራት እንደምችለው መብራት ሆኖልኛል። ከአንድ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አምላክ ያለውን አመለካከት የሚያብራሩ ነገሮችን መመልከት ወይም ማዳመጥ እንዲሁም ከሕይወት ጋር ለተያያዙ በርካታ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ችያለሁ።”—ጄ. ሲ. ከዌስት ኢንዲስ

“የምኖረው በደቡብ አሜሪካ ርቆ በሚገኝ አንድ ጫካ ውስጥ ቢሆንም ስለተደረገልኝ መንፈሳዊ እርዳታ እጅግ አመሰግናለሁ። ይህ ድረ ገጽ ባይኖር ኖሮ ጠፍቼ ነበር።”—ኤም. ኤፍ. ከደቡብ አሜሪካ