በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

በቱር ደ ፍራንስ የብስክሌት ውድድር ላይ የሚያጽናና መልእክት መናገር

በቱር ደ ፍራንስ የብስክሌት ውድድር ላይ የሚያጽናና መልእክት መናገር

ቱር ደ ፍንራስ የተባለው በዓለም ታዋቂ የሆነው የብስክሌት ውድድር 103ኛ ዙር የተካሄደው ከሐምሌ 2 እስከ 24, 2016 ነበር። ወቅቱ ውጥረት የነገሠበት ነበር። ከዚያ በፊት በነበረው ዓመት በፈረንሳይ የደረሱ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶች በድምሩ ከ100 የሚበልጡ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል። ከዚያም ሐምሌ 14, 2016 ብሔራዊ በዓል እየተከበረ ሳለ አንድ አሸባሪ በኒስ ከተማ የርችት ትርዒት ለማየት ተሰብስበው በነበሩ ሰዎች ላይ የጭነት መኪና እየነዳ ሕዝቡ ላይ ወጣ። በጥቃቱ 86 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ብዙዎች ቆስለዋል።

ፍርሃትና ሐዘን በነገሠበት በዚህ ሁኔታ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ለተደናገጠው የፈረንሳይ ሕዝብ ተስፋና መጽናኛ የያዘ መልእክት ለማድረስ በትጋት ሲሰሩ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ተወዳዳሪዎቹ በውድድሩ መሃል አረፍ በሚሉባቸው ቦታዎች ላይ ተንቀሳቃሽ የጽሑፍ ጋሪዎችን በማቆም ሲሰብኩ ነበር። በዚህ ሥራ ለመሳተፍ ከ1,400 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች በፈቃደኝነት ራሳቸውን ያቀረቡ ሲሆን በአእምሯቸው ውስጥ ለሚጉላሉ አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ ለሚፈልጉ ሰዎች ከ2,000 በላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ሰጥተዋል።

‘እናንተ የማትገኙበት ቦታ የለም!’

ከከተማ ወደ ከተማ በመሄድ ተወዳዳሪዎቹን የሚያበረታቱት ደጋፊዎች በሄዱበት ቦታ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችን በማየታቸው ተገርመዋል። የቱር ደ ፍራንስ ውድድር አዘጋጆች የይሖዋ ምሥክሮቹ ምን ያህል ተቀናጅተው እንደሚሠሩ ከተመለከቱ በኋላ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፦ “ውድድሩ በሚካሄድበት በሁሉም ቦታ አላችሁ!” ብዙ ደጋፊዎች “የይሖዋ ምሥክሮች እዚህም አሉ!” በማለት በአድናቆት ተናግረዋል። አንድ የአውቶቡስ ሾፌር በአንድ የውድድሩ ቦታ ትራክት እንዲወስድ ግብዣ ሲቀርብለት በዚህ ውድድር ወቅት ቀደም ብሎ አራት ትራክቶች እንደተቀበለ በመግለጽ ተጨማሪ እንደማይፈልግ በትሕትና ተናግሯል!

አንዳንድ ግለሰቦች በሄዱበት ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችን ማግኘታቸው ስላስገረማቸው ከጋሪዎቹ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ጽሑፍ ወስደዋል። ባለፈው ዓመት በተካሄደው ቱር ደ ፍራንስ ውድድር ላይ የይሖዋ ምሥክሮችን አይቷቸው እንደነበረ ያስታወሰ በስፖርት ቴሌቪዥን ጣቢያ የሚሠራ አንድ ሰው በዚህ ዓመት ወደ ጽሑፍ ጋሪው ቀረብ ብሎ ለማየትና ጽሑፍ ለመውሰድ ተነሳስቷል። ከዚያም ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ መርጦ ወስዷል። መኪናው ውስጥ ሆኖ ከመጽሐፉ ላይ የተወሰነ ክፍል ካነበበ በኋላ ለሥራ ባልደረቦቹ ስለ ጽሑፍ ጋሪዎቹ የነገራቸው ሲሆን እነሱም የተለያዩ ርዕሶች ያሏቸውን ጽሑፎች ወስደዋል።

ተስፋና እምነት የሚያሳድሩ

ውድድሩን ለማየት የመጡ አንዳንድ ሰዎች ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ቀርበው የልባቸውን አጫውተዋቸዋል። አንዲት ወጣት በጣም ተስፋ ቆርጣ እንደነበር፣ እንዲያውም በዚያው ቀን ባቡር ሃዲድ ውስጥ በመግባት ሕይወቷን ለማጥፋት እያሰበች እንደነበር ነግራቸዋለች። ይሁን እንጂ ወደፊት የአምላክ መንግሥት ስለሚያመጣው ሰላም የሰፈነበት ጊዜ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ አጽናኝ መልእክት ስትሰማ ሕይወቷን ላለማጥፋት ወስናለች። አንዲት ሌላ ሴትም የይሖዋ ምሥክሮቹን “መልካም ሥራችሁን ግፉበት!” ብላቸዋለች።

ብዙውን ጊዜ የማያውቃቸውን ሰዎች እንደሚጠራጠር ሳይሸሽግ የተናገረ አንድ በምርኩዝ የሚሄድ ሰው ልከኛ አለባበስ ያላትን አንዲት ሴት የይሖዋ ምሥክር መሆኗን ስላወቀ እገዛ ልታደርግለት ስትሞክር እርዳታዋን ለመቀበል ፈቃደኛ ሆኗል። እንዲህ ብሏል፦ “ለፈገግታሽና ለአለባበስሽ አመሰግንሻለሁ። እምነት እንድጥልብሽ ያደረገኝ ይህ ነው።”