በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

እስረኞችን መርዳት

እስረኞችን መርዳት

በዩናይትድ ስቴትስ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ እስረኞች መንፈሳዊ እርዳታ እንዲደረግላቸው ለመጠየቅ በየቀኑ በርካታ ደብዳቤዎችን ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ ይልካሉ።

እኛም በአቅራቢያው በሚገኙ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ሰባኪዎች ሄደው በእስር ቤት፣ በወህኒ፣ በአእምሮ ሕክምና ተቋማት፣ በወጣቶች ማረሚያ ቤቶችና የዕፅ ሱሰኞችን በሚረዱ ተቋማት ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች እንዲያነጋግሩና መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስተምሯቸው ዝግጅት በማድረግ ለደብዳቤዎቹ ምላሽ እንሰጣለን።

በአንዳንድ እስር ቤቶች ውስጥ ሰባኪዎቻችን መደበኛ የጉባኤ ስብሰባዎችን ያካሂዳሉ። ለምሳሌ ያህል በአንድ እስር ቤት ውስጥ በሁለት ቦታዎች ላይ የቀረቡትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ንግግሮች 32 ሰዎች ተከታትለዋቸዋል።

እንዲህ ያሉት ዝግጅቶች እስረኞቹን እጅግ እየጠቀሟቸው መሆኑን ማየት ያስደስታል። ለምሳሌ ያህል፣ በነፍስ ግድያ ወንጀል ተከሶ የዕድሜ ልክ እስራት የተበየነበት በኢንዲያና ግዛት በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ያለ አንድ ግለሰብ ጥሩ የባሕርይ ለውጥ በማድረጉ ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆኗል።

በካሊፎርኒያ በሚገኝ አንድ ትልቅ ማረሚያ ቤት ውስጥ የታሰረ ግለሰብን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምር የነበረ አንድ የይሖዋ ምሥክር ግለሰቡን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ቀደም ሲል የነበረውን ባሕርይም ሆነ በኋላ ላይ ያደረገውን ለውጥ አይቻለሁ። ለጥምቀት ብቁ ለመሆን ሲል አስደናቂ እርምጃዎችን ወስዷል።

በርካታ እስረኞች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀብለዋል፤ ይህን ያደረጉት፣ የወሰዱት እርምጃ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል እያወቁም ጭምር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶቹ ከነበሩበት የወሮበሎች ቡድን በመውጣታቸው የተነሳ ለደኅንነታቸው ሲባል ለብቻቸው እንዲታሰሩ አሊያም ወደ ሌላ እስር ቤት እንዲዛወሩ ተደርጓል።

የእስር ቤት ባለሥልጣናት መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንዳለው ሲመለከቱ እጅግ ይደነቃሉ። አንዳንዶቹም የይሖዋ ምሥክሮች በማረሚያ ቤቶቹ ውስጥ ላከናወኑት ሥራ የአድናቆት መግለጫ የምሥክር ወረቀቶችንና ለበጎ አድራጎት ሠራተኞች የሚሰጡ ሽልማቶችን አበርክተውላቸዋል።