በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

በሃንጋሪ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የጎርፍ አደጋ በደረሰበት ወቅት ባበረከቱት እርዳታ አድናቆት አተረፉ

በሃንጋሪ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የጎርፍ አደጋ በደረሰበት ወቅት ባበረከቱት እርዳታ አድናቆት አተረፉ

ሰኔ 2013 በማዕከላዊ አውሮፓ በተከሰተው ከባድ ዝናብ የተነሳ ወንዞች ሞልተው አካባቢውን አጥለቅልቀው ነበር። ሃንጋሪ ውስጥ ያለው የዳንዩብ ወንዝ ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ ነበር።

ይህን ሁኔታ ያስተዋለው የሃንጋሪ የሰው ኃይል አቅርቦት ሚኒስቴር፣ የይሖዋ ምሥክሮች የጎርፍ አደጋን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በሃንጋሪ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ቅርንጫፍ ቢሮው ለጥያቄው ምላሽ በመስጠት በዳንዩብ ወንዝ አካባቢ የሚገኙ ጉባኤዎች ባለሥልጣናቱ የጎርፍ አደጋን ለመከላከል በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሐሳብ አቀረበ።

ጉባኤዎቹ የሰጡት ምላሽ በጣም አስደናቂ ነበር። በቀጣዮቹ ቀናት ከ72 ጉባኤዎች የተውጣጡ ከ900 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች በወንዙ ዳርቻ ያለውን የጎርፍ መከላከያ በማጠናከሩ ሥራ ተካፍለዋል። የይሖዋ ምሥክሮቹ ባጅ እንዲያደርጉ ተጠይቀው ነበር፤ በባጁ ላይ ስማቸውና የመጡበት ከተማ ስም እንዲሁም “የይሖዋ ምሥክሮች” የሚል ጽሑፍ ሰፍሮ ነበር።

በአንድ ከተማ ውስጥ ያለ የሃንጋሪ ቀይ መስቀል ተወካይ ለአንድ ጉባኤ የሚከተለውን መልእክት ጽፎ ነበር፦ “እንዲህ ያለ አንድነት ያላቸውና ለመርዳት ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ማየት የተለመደ አይደለም፤ በዚህ ላይ ደግሞ ብዙ ርቀት ተጉዛችሁ መጥታችኋል፤ በመሆኑም ለእናንተ ያለንን አድናቆትና አክብሮት መግለጽ እንፈልጋለን! የእናንተን ግሩም ምሳሌ ለከተማችን ሳሳውቅ ኩራት ይሰማኛል!”

የሃንጋሪ ፓርላማ አባልና በአደጋ ጊዜ እርዳታ የሚሰጥ ድርጅት ሊቀ መንበር የሆኑ ሰው የይሖዋ ምሥክሮች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ ለቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ ጽፈዋል።