በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

JW.ORG በአሁኑ ጊዜ ከ300 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል!

JW.ORG በአሁኑ ጊዜ ከ300 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል!

በ​jw.org ላይ የሚገኘውን የቋንቋዎች ዝርዝር ብትከፍት ከ300 የሚበልጡ ቋንቋዎችን ታገኛለህ። ይህን ያህል ብዛት ባላቸው ቋንቋዎች የሚገኝ ሌላ ድረ ገጽ የለም ማለት ይቻላል!

ይህ ቁጥር ከሌሎች ታዋቂ ድረ ገጾች ጋር ሲወዳደር ምን ያህል ብልጫ አለው? እስቲ ይህን መረጃ ተመልከት፦ እስከ ሐምሌ 2013 ድረስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድረ ገጽ የሚገኘው በ6 ቋንቋዎች ነው። ዩሮፓ የተባለው የአውሮፓ ሕብረት ሕጋዊ ድረ ገጽ በ24 ቋንቋዎች አገልግሎት ይሰጣል። ጉግል ደግሞ በ71 ቋንቋዎች የሚገኝ ሲሆን ዊኪፒዲያ 287 በሚያክሉ ቋንቋዎች አገልግሎት ይሰጣል።

አንድን ድረ ገጽ ከ300 በሚበልጡ ቋንቋዎች ማዘጋጀት ሰፊ ጊዜ ይጠይቃል! ይህ ሥራ የሚሠራው ለይሖዋ ክብር ማምጣት በሚፈልጉ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በመቶዎች በሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ነው። ለእያንዳንዱ ቋንቋ በቡድን የሚሠሩ ተርጓሚዎች ያሉ ሲሆን ተርጓሚዎቹ ያካበቱትን ልምድ በመጠቀም የእንግሊዝኛውን ጽሑፍ ወደሚፈለገው ቋንቋ ይተረጉማሉ።

JW.ORG ከ300 በሚበልጡ ቋንቋዎች የተተረጎሙ በጣም ብዙ ገጾች ያሏቸውን መረጃዎች ይዟል፤ በአጠቃላይ በድረ ገጹ ላይ ያለው መረጃ ከ200,000 ገጽ ይበልጣል!

JW.ORG በብዙ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ድረ ገጽ ብቻ ሳይሆን በብዙዎች ዘንድ ታዋቂ ነው። ዓለም አቀፉን የኢንተርኔት መረጃ ፍሰት የሚያጠናው አሊክሳ የተባለው ተቋም ለተለያዩ ድረ ገጾች የሰጠው ደረጃ ይህን ያሳያል። ይህ ተቋም “ሃይማኖትና መንፈሳዊነት” በሚለው ምድብ ውስጥ 87,000 የሚያክሉ ድረ ገጾችን አካትቷል። በዚህ ምድብ ውስጥ በዓለማችን ያሉ ዋና ዋና ሃይማኖቶችን ጨምሮ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን ጽሑፎች የሚያዘጋጁና በተመሳሳይ ሥራ ላይ የተሠማሩ ድርጅቶች ይገኙበታል። እስከ ሐምሌ 2013 በዚህ ዝርዝር ውስጥ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው jw.org ነው! የአንደኛነት ደረጃን የያዘው ብዙ ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን በኢንተርኔት የሚያቀርብ አንድ የንግድ ድርጅት ድረ ገጽ ነው።

እስከ ጥቅምት 2013 jw.org በቀን በአማካይ ከ890,000 በሚበልጡ የተለያዩ ተጠቃሚዎች ተጎብኝቷል። በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ጠቃሚ ትምህርት በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥላለን።