በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በአፍሪካ የሚኖሩ ዓይነ ስውራንን መርዳት

በአፍሪካ የሚኖሩ ዓይነ ስውራንን መርዳት

በአንዳንድ ታዳጊ አገራት ውስጥ የሚኖሩ ዓይነ ስውራን በሌሎቹ አገራት እንዳሉት ዓይነ ስውራን ሁኔታዎች የተመቻቹላቸው አይደሉም። አንዳንድ ጊዜ ኅብረተሰቡ የሚያገላቸው ከመሆኑም ሌላ ዓይነ ስውር ያልሆኑ ሰዎች በቀላሉ የሚያከናውኗቸውን የተለመዱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ለማከናወን የሚያስችል እገዛ አይደረግላቸውም። ለምሳሌ ያህል ገበያ ሄዶ ምግብ መሸመት፣ አውቶብስ መሳፈር እንዲሁም ገንዘብ ቆጥሮ መስጠትና መቀበል አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል። ማንበብም ቢሆን ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። ብሬይል የማንበብ ችሎታ ያላቸው ሁሉም ዓይነ ስውራን አይደሉም። ብሬይል ማንበብ የሚችሉትም እንኳ በቋንቋቸው የተዘጋጁ ጽሑፎችን እንደ ልብ አያገኙ ይሆናል።

የይሖዋ ምሥክሮች ከ100 ለሚበልጡ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ዓይነ ስውር ለሆኑ ሰዎች ሲያዘጋጁ ቆይተዋል። በቅርቡ የይሖዋ ምሥክሮች በማላዊ በሚነገረው የቺቼዋ ቋንቋ የብሬይል ጽሑፎችን ለማዘጋጀት የሚያስችሉ የብሬይል ማተሚያዎችንና መጠረዣ መሣሪያዎችን ከኔዘርላንድስ ወደ ማላዊ እንዲላኩ አድርገዋል።

የብሬይል ጽሑፎችን በማዘጋጀት ረገድ ተሞክሮ ያካበተ ሌዮ የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር በብራዚል ካለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ወደ ማላዊ ሄዶ ነበር። ሌዮ የመሣሪያዎቹንና ጽሑፎችን ወደ ብሬይል ለመቀየር የሚረዳውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ የኮምፒውተር ፕሮግራም አጠቃቀምን አስመልክቶ በዚያ ለሚገኝ አምስት አባላት ያሉት አንድ ቡድን ሥልጠና ሰጥቶ ነበር። የኮምፒውተር ፕሮግራሙ ጽሑፎችን ወደ ቺቼዋ ብሬይል ለመቀየር ያስችላል። ፕሮግራሙ ይህን ማድረግ እንዲችል የዋናውን ጽሑፍ ፊደላትና የብሬይል ፊደላቱን የያዘ በቺቼዋ ቋንቋ የተዘጋጀ የመለወጫ ሠንጠረዥ ኮምፒውተሩ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ፕሮግራሙ ጽሑፉን ወደ ብሬይል መቀየር የሚችል ከመሆኑም በላይ ጽሑፉ ዓይነ ስውራኑ በቀላሉ ሊያነቡት በሚችሉት መንገድ እንዲቀመጥ ያደርጋል። በማላዊ የሚኖሩ አንዳንድ ዓይነ ስውራን ስለተዘጋጁላቸው የብሬይል ጽሑፎች ምን እንዳሉ ተመልከት።

ሙንያራድዚ ዓይነ ስውር የሆነች ወጣት ስትሆን በሳምንት ውስጥ ለተወሰነ ሰዓት የምታቀርበው የራሷ የሬዲዮ ፕሮግራም አላት። በተጨማሪም ሰዎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በማስተማር በየወሩ 70 ሰዓት ታሳልፋለች። ሙንያራድዚ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥታለች፦ “ከዚህ ቀደም የማገኘው በእንግሊዝኛ የተዘጋጁ የብሬይል ጽሑፎችን ነበር፤ ሆኖም በአፍ መፍቻ ቋንቋዬ ማንበብ መቻሌ ልቤን በጥልቅ ነክቶታል። የእምነት አጋሮቼ የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የብሬይል ጽሑፎችን በቋንቋችን እንድናገኝ ሲሉ ለሚያደርጉት ጥረትና የገንዘብ መዋጮ እጅግ አመስጋኝ ነኝ። እንዳልተረሳንና ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱን እንድገነዘብ ረድቶኛል።”

ፍራንሲስ በሰሜን ማላዊ የሚኖር የይሖዋ ምሥክር ነው። ዓይነ ስውር ስለሆነ ጽሑፎችን የሚያነብቡለት ሌሎች ሰዎች ነበሩ። በቺቼዋ ቋንቋ የተዘጋጀው ጽሑፍ ለመጀመሪያ ጊዜ እጁ ሲገባ “በሕልሜ ነው በእውኔ? ይህ በጣም ያስደንቃል!” በማለት አድናቆቱን ገልጿል።

ሎይስ ዓይነ ስውር ስትሆን የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ነች። ሎይስ 52 ሰዎች በሕይወታቸው ላይ በጎ ለውጥ እንዲያደርጉ ረድታለች። ይህን ማድረግ የቻለችው እንዴት ነው? እሷ የብሬይል ጽሑፎችን ተጠቅማ ስታስተምር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቿ ደግሞ በወረቀት ላይ የታተሙ ጽሑፎችን ይዘው ይከታተሏታል፤ ሁሉም ጽሑፎች የተዘጋጁት በይሖዋ ምሥክሮች ነው።

ሎይስ መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ከብራዚል የመጣው ሌዮ የተባለው አሠልጣኝ እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች በብሬይል የተዘጋጁ ጽሑፎች ሲደርሷቸውና ጽሑፎቹ በገዛ ቋንቋቸው የተዘጋጁ መሆናቸውን ሲያውቁ የሚሰማቸውን ስሜት ማየት ይህ ነው የማይባል እርካታ ይሰጠኛል። ብዙዎቹ ለይሖዋ ያላቸውን አመስጋኝነት የሚገልጹ ከመሆኑም ሌላ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና ለስብከቱ ያለማንም እገዛ መዘጋጀት መቻላቸው ደስታቸውን እንደጨመረላቸው ይናገራሉ። ከእንግዲህ ሌላ ሰው እንዲያነብላቸው አይጠብቁም። አሁን የግል ጥናታቸው በእርግጥም የግላቸው ሆኗል። አሁን ቤተሰባቸው በመንፈሳዊ እንዲያድግ ከበፊቱ በተሻለ መርዳት ይችላሉ። እነዚህ ጽሑፎች ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ ረድተዋቸዋል።”