በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ዓለም አቀፉ የሕትመት ሥራ ሰዎች ስለ አምላክ እንዲያውቁ እየረዳ ነው

ዓለም አቀፉ የሕትመት ሥራ ሰዎች ስለ አምላክ እንዲያውቁ እየረዳ ነው

በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጇቸውን ጽሑፎች ያነባሉ። አሁን አንተ እያደረግክ እንዳለኸው ሁሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እነዚህን ጽሑፎች የሚያነቡት በኤሌክትሮኒክ መሣሪዎች ነው። ይሁንና ምን ያህል ጽሑፎች እንደሚታተሙ ስታውቅ ትገረም ይሆናል። ከ2013 ወዲህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን 700 ገደማ በሚሆኑ ቋንቋዎች ማዘጋጀት የጀመርን ሲሆን ጽሑፎቹ በ239 አገሮች ውስጥ እየተሰራጩ ነው።

ከ1920 በፊት ሁሉም ጽሑፎቻችን የሚታተሙት በንግድ ማተሚያ ቤቶች ውስጥ ነበር። በ1920 ግን በብሩክሊን ኒው ዮርክ የሚገኝ አንድ አነስተኛ ሕንፃ በመከራየት አንዳንድ መጽሔቶቻችንንና ቡክሌቶቻችንን ራሳችን ማተም ጀመርን። ከዚህ አነስተኛ ጅምር የተነሳው ይህ የኅትመት ሥራ በአሁኑ ጊዜ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ፣ በአፍሪካ፣ በእስያና በደቡብ አሜሪካ ውስጥ በሚገኙ 15 ማተሚያ ቤቶቻችን ውስጥ እየተከናወነ ይገኛል።

እጅግ ትልቅ ቦታ የምንሰጠው መጽሐፍ

ከምናትማቸው ጽሑፎች ሁሉ እጅግ ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ለመጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ የታወቀ ነው። መጀመሪያ ያተምነው መጽሐፍ ቅዱስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀው ኪንግ ጀምስ ቨርዥን ሲሆን ታትሞ የወጣው በ1942 ነው። ከ1961 አንስቶ የይሖዋ ምሥክሮች ሙሉውን የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም አዘጋጅተው በአንድ ጥራዝ ሲያትሙ ቆይተዋል። እስከ 2013 ባለው ጊዜ ውስጥ ይህን መጽሐፍ ቅዱስ በ121 ቋንቋዎች ከ184 ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ ማተም ችለናል።

ይህን የሕትመት ሥራ አስደናቂ የሚያደርገው የታተሙት መጽሐፍ ቅዱሶች ብዛት ብቻ አይደለም። የምናዘጋጃቸው መጽሐፍ ቅዱሶች ለረጅም ጊዜ ያገለግላሉ። ወረቀቶቹ ወደ ቢጫነት እንዲለወጡ ከሚያደርግ አሲድ ነፃ ከመሆናቸውም በላይ መጽሐፉ በጥሩ መንገድ የተጠረዘ ነው። በዚህም የተነሳ አንባቢዎች ይህን መጽሐፍ ቅዱስ በየዕለቱ ቢጠቀሙበት እንኳ ለብዙ ጊዜ ማገልገል ይችላል።

ሌሎች ጽሑፎች

ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት እንዲችሉ የሚያግዙ ሌሎች ጽሑፎችንም እናትማለን። ከ2013 ጀምሮ የታተሙትን ጽሑፎች አኃዝ ተመልከት፦

  • መጠበቂያ ግንብ በመባል የሚታወቀው ዋነኛ መጽሔታችን ከ210 በሚበልጡ ቋንቋዎች የሚዘጋጅ ሲሆን በዓለማችን ላይ በብዛት በመሰራጨት ረገድ ተወዳዳሪ የለውም። አሥራ ስድስት ገጾች ያሉት እያንዳንዱ እትም ወደ 45,000,000 በሚያህል ቅጂዎች ይታተማል።

  • ንቁ! ከመጠበቂያ ግንብ ጋር አብሮ የሚታተም መጽሔት ሲሆን በስፋት በመሰራጨት ረገድ ሁለተኛውን ደረጃ ይይዛል፤ ይህ መጽሔት በ99 ቋንቋዎች ይዘጋጃል። እንዲሁም እያንዳንዱ እትም ወደ 44,000,000 ያህል ቅጂ ይታተማል።

  • ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው ባለ 224 ገጽ መጽሐፍ፣ ለስላሳ ሽፋን ያለው ሲሆን አንባቢው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች እንዲገነዘብ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ከ2005 ወዲህ ይህ መጽሐፍ ከ214 ሚሊዮን በሚበልጡ ቅጂዎችና ከ240 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች ታትሟል።

  • አምላክን ስማ የተባለው ባለ 32 ገጽ ብሮሹር የንባብ ችሎታቸው ውስን የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በብሮሹሩ ላይ የሚገኙት ማራኪ ሥዕሎችና አጠር ያሉት የሥዕሎቹ መግለጫዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ቀላል በሆነ መንገድ ያስጨብጣሉ። ብሮሹሩ ከ400 በሚበልጡ ቋንቋዎች ከ42 ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ ታትሟል።

ከእነዚህ ጽሑፎች በተጨማሪ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎቻቸው መልስ እንዲያገኙ፣ በሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዲፈቱና ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖራቸው የሚረዱ የተለያዩ መጻሕፍትን፣ ብሮሹሮችንና ትራክቶችን አትመዋል። በ2012 የይሖዋ ምሥክሮች በራሳቸው ማተሚያ ቤቶች ውስጥ ከ1.3 ቢሊዮን የሚበልጡ መጽሔቶችን እንዲሁም ከ80 ሚሊዮን በላይ መጻሕፍትንና መጽሐፍ ቅዱሶችን አትመዋል።

በ2012 የይሖዋ ምሥክሮች በራሳቸው ማተሚያ ቤቶች ውስጥ ከ1.3 ቢሊዮን የሚበልጡ መጽሔቶችን እንዲሁም ከ80 ሚሊዮን በላይ መጻሕፍትንና መጽሐፍ ቅዱሶችን አትመዋል

ማተሚያ ቤቶቻችንን የሚጎበኙ ሰዎች ብዙውን ጊዜ በዚያ የሚሠሩትን ታታሪ ሠራተኞች ሲመለከቱ ይገረማሉ። ሥራውን የሚያከናውኑት ወንዶችና ሴቶች በሙሉ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በፈቃደኝነት ይሰጣሉ። አብዛኞቹ ወደ ቤቴል (“የአምላክ ቤት” ማለት ነው) በመጡበት ወቅት ስለ ሕትመት ሥራ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ይሁን እንጂ ቤቴል ውስጥ የተሰጣቸው ሥልጠና በቤቴል ካለው ምቹ የሥራ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውኑ አስችሏቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በሰዓት 200,000 ባለ 16 ገጽ መጽሔቶችን የማተም ችሎታ ያለውን እጅግ ፈጣን የሕትመት መሣሪያ ሲያንቀሳቅሱ ማየት የተለመደ ነገር ነው።

ታዲያ ለዚህ ሁሉ የሚውለው ገንዘብ የሚገኘው ከየት ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የሚያከናውኑት ሥራ የሚደገፈው በፈቃደኝነት በሚሰጥ የገንዘብ መዋጮ ነው። በአሁኑ ጊዜ መጠበቂያ ግንብ በመባል የሚታወቀው የጽዮን መጠበቂያ ግንብ በነሐሴ 1879 እትሙ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “‘የጽዮን መጠበቂያ ግንብ’ ደጋፊ ይሖዋ ራሱ እንደሆነ እናምናለን። ይህ በመሆኑም ከሰዎች ድጋፍ ለማግኘት በፍጹም አይለምንም ወይም አይማጠንም።” ዛሬም ብንሆን የሚሰማን እንደዚሁ ነው።

ይህን ሥራ ለማከናወን ይህን ያህል ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት የምናፈስሰው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ግባችን እያንዳንዱ ሰው ወደ አምላክ ይበልጥ እንዲቀርብ መርዳት ነው፤ በሚሊዮን በሚቆጠር ቅጂ የምናሳትማቸው መጽሐፍ ቅዱሶች፣ ጽሑፎችና በኢንተርኔት ላይ የሚወጡት ርዕሶች በዚህ ረገድ አንተን ይረዱሃል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።