በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኢስቶኒያ ለአንድ “ታላቅ ሥራ” እውቅና ሰጠች

ኢስቶኒያ ለአንድ “ታላቅ ሥራ” እውቅና ሰጠች

በኢስቶኒያኛ የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ፣ በ2014 በኢስቶኒያ በተዘጋጀው ላንጉዌጅ ዲድ ኦቭ ዘ ይር አዋርድ ላይ በዕጩ ተሸላሚነት ቀርቦ ነበር፤ ይህ ሽልማት የሚሰጠው ኢስቶኒያኛን በማስተዋወቅ፣ በማስተማርና ቋንቋው ተጠብቆ እንዲቆይ በማድረግ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ነው። በዕጩ ተሸላሚነት ከቀረቡት 18 ሥራዎች መካከል አዲስ ዓለም ትርጉም ሦስተኛውን ደረጃ ይዟል።

በነሐሴ 8, 2014 የወጣው ይህ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለዕጩነት እንዲቀርብ ያደረጉት ክሪስቲና ሮዝ የተባሉ የኢስቶኒያኛ የቋንቋ ተቋም ምሁር ናቸው። እኚህ የቋንቋ ምሁር አዲስ ዓለም ትርጉም “ቀላልና ለማንበብ ደስ የሚል” እንደሆነ ገልጸዋል፤ አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ይህን መጽሐፍ ቅዱስ የማዘጋጀቱ ሥራ፣ በኢስቶኒያኛ የሚከናወነውን ትርጉም በማሻሻል ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።” የኢስቶኒያኛ የሥነ ጽሑፍና የባሕል ፕሮፌሰር የሆኑት ሬን ቬዴማን ይህን አዲስ ትርጉም “ታላቅ ሥራ” ብለው ጠርተውታል።

የመጀመሪያው የኢስቶኒያኛ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ የተዘጋጀው በ1739 ሲሆን ከዚያ ወዲህ ሌሎች ትርጉሞችም ወጥተዋል። ታዲያ አዲስ ዓለም ትርጉም “ታላቅ ሥራ” የተባለው ለምንድን ነው?

ትክክለኛነት። በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀውና በ1988 የወጣው የኢስቶኒያኛ መጽሐፍ ቅዱስ፣ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት (ብሉይ ኪዳን) ውስጥ የአምላክን ስም ከ6,800 ጊዜ በላይ “ዬሖቫ” (ይሖዋ) ብሎ በማስቀመጥ የሚደነቅ ሥራ አከናውኗል። a በኢስቶኒያኛ የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም የአምላክን ስም ያስገባው በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ብቻ አይደለም። አዲስ ዓለም ትርጉም መለኮታዊውን ስም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት (አዲስ ኪዳን) ውስጥም አስገብቷል፤ ይህን ያደረገው በበቂ ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ነው።

ግልጽነት። አዲስ ዓለም ትርጉም የተዘጋጀው ትክክለኛ ሆኖም ለማንበብ ቀላል በሆነ መንገድ ነው? ቶማስ ፖል የተባሉ የተከበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ፣ ኤስቲ ኪሪክ (የኢስቶኒያ ቤተ ክርስቲያን) በተባለ ጋዜጣ ላይ እንደገለጹት አዲስ ዓለም ትርጉም “መልእክቱን በቀላሉ በሚገባ ኢስቶኒያኛ በማስቀመጥ ረገድ ተሳክቶለታል።” እኚህ ሰው አክለውም “እዚህ ግብ ላይ የደረሰው የመጀመሪያው ትርጉም ይህ እንደሆነ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ” ብለዋል።

ከኢስቶኒያኛ መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅም ማግኘት

የኢስቶኒያ ሕዝብ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስን የተቀበለበት መንገድ አስደናቂ ነው። አንድ ብሔራዊ የሬዲዮ ጣቢያ ስለ አዲሱ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወሳ የ40 ደቂቃ ፕሮግራም አቅርቧል። ቀሳውስትም ሆኑ ምዕመናን፣ የይሖዋ ምሥክሮች አዲሱን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል። በታሊን የሚገኝ አንድ ታዋቂ ትምህርት ቤት ለማስተማሪያነት የሚጠቀምበት 20 የአዲስ ዓለም ትርጉም ቅጂዎች ጠይቋል። ኢስቶኒያውያን ማንበብ ይወዳሉ፤ የይሖዋ ምሥክሮችም ከሁሉ የላቀውን መጽሐፍ ትክክለኛና ግልጽ በሆነ መንገድ መተርጎም በመቻላቸው ደስተኞች ናቸው።

a በታርቱ ዩኒቨርሲቲ የአዲስ ኪዳን ጥናት ሊቀ መንበር የሆኑት አይን ሪስታን፣ ኢስቶኒያውያን መለኮታዊውን ስም “ዬሖቫ” ብለው መጥራት የጀመሩት እንዴት እንደሆነ ከተረኩ በኋላ ሐሳባቸውን ሲደመድሙ እንደሚከተለው ብለዋል፦ “ዬሖቫ ለዘመናችን በጣም ተስማሚ ይመስለኛል። ይህ አጠራር የመጣበት መንገድ ምንም ይሁን ምን፣ . . . ለብዙ ዘመናት ትልቅ ቦታና ትርጉም ተሰጥቶት ቆይቷል፤ ዬሖቫ የሰው ዘርን ለመቤዠት ልጁን የላከው አምላክ ስም ነው።”