በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በብዙ ቋንቋዎች የሚቀርብ የውዳሴ መዝሙር

በብዙ ቋንቋዎች የሚቀርብ የውዳሴ መዝሙር

አንድን መዝሙር ወደ ሌላ ቋንቋ መተርጎም በጣም ተፈታታኝ ነው። ከዚህ አንጻር 135 መዝሙሮችን የያዘ የመዝሙር መጽሐፍ መተርጎም ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም።

የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ዓይነቱን ተፈታታኝ ሥራ በብቃት በመወጣት ለይሖዋ ዘምሩ የተባለውን አዲስ የመዝሙር መጽሐፋቸውን በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በ116 ቋንቋዎች መተርጎም ችለዋል። በ55 ቋንቋዎች ደግሞ 55 መዝሙሮችን ብቻ ያያዘ የመዝሙር መጽሐፍ ወጥቷል። ከዚህም በተጨማሪ ይህ የመዝሙር መጽሐፍ በበርካታ ቋንቋዎች በመተርጎም ላይ ይገኛል።

ትርጉም እና ግጥም

በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን 600 በሚያክሉ ቋንቋዎች እያዘጋጁ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በ400 ቋንቋዎች ገደማ የሚዘጋጁትን ጽሑፎች ኢንተርኔት ላይ ማግኘት ይቻላል። ያም ሆኖ መዝሙሮችን መተርጎም የራሱ የሆኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉት። ለምን? ምክንያቱም ለይሖዋ ዘምሩ በተባለው መጽሐፍ ላይ ያሉት መዝሙሮች ግጥም በ171 ቋንቋዎች ቢተረጎምም የመዝሙሮቹ ዜማ ግን በሁሉም ቋንቋዎች ተመሳሳይ ነው።

የግጥም ስንኞችን መተርጎም አንድን መጽሔት ከመተርጎም ፈጽሞ የተለየ ነው። ለምሳሌ ያህል ተርጓሚዎች መጠበቂያ ግንብ ሲተረጉሙ በዋናው ጽሑፍ ላይ የሰፈረውን ሐሳብ አንድም ሳያስቀሩ በሌላ ቋንቋ ለማስቀመጥ ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ። መዝሙር መተርጎም ግን ከዚህ ይለያል።

የትርጉም ሥራው የሚከናወነው እንዴት ነው?

ተርጓሚዎች መዝሙሮቹን በሚተረጉሙበት ጊዜ ትንሽ ለየት ያለ ዘዴ ይጠቀማሉ፤ ምክንያቱም ስንኞቹ ትርጉም ያዘሉ፣ ማራኪና በቀላሉ የሚታወሱ መሆን አለባቸው።

የሚዘምሩት ሰዎች በውዳሴ መዝሙሩ ላይ ያሉትን ቃላት ትርጉምና የሚያስተላልፉትን መልእክት በቀላሉ መረዳት መቻል አለባቸው። በሁሉም ቋንቋዎች በሚዘጋጁት መዝሙሮች ላይ ግጥሙና ዜማው እርስ በርስ የሚጣጣምና ለዛ ያለው መሆን አለበት፤ የሚዘምረው ሰው በራሱ ቋንቋ የተገጠመ መዝሙር እንደሚዘምር ሆኖ ሊሰማው ይገባል።

ታዲያ ተርጓሚዎች ይህን ግብ ማሳካት የሚችሉት እንዴት ነው? በእንግሊዝኛ በተዘጋጀው ለይሖዋ ዘምሩ በተባለው የመዝሙር መጽሐፍ ላይ ያሉትን ስንኞች ቃል በቃል እየተረጎሙ ከማስቀመጥ ይልቅ መዝሙሩ ከሚያስተላልፈው ሐሳብ ሳይወጡ ግጥሙን በራሳቸው እንዲጽፉ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል። ተርጓሚዎቹ ከእያንዳንዱ መዝሙር በስተ ጀርባ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በጥብቅ የሚከተሉ ቢሆንም የቋንቋው ተናጋሪዎች በቀላሉ ሊረዷቸውና ሊያስታውሷቸው የሚችሉ የተለመዱ አገላለጾችን ይጠቀማሉ።

ተርጓሚዎቹ በቅድሚያ የእንግሊዝኛውን መዝሙር ቀጥተኛ ትርጉም ያስቀምጣሉ። ከዚያም ግጥም የመጻፍ ችሎታ ያለው አንድ የይሖዋ ምሥክር የተተረጎመውን ጽሑፍ ማራኪ የሆነና ስሜት የሚሰጥ ግጥም አድርጎ ይጽፈዋል። ከዚያም የትርጉም ቡድኑና የማጣሪያ ንባቡን የሚያደርጉት ሰዎች፣ ግጥሞቹ ሊተላለፍ ከተፈለገው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት አለመውጣታቸውን ለማጣራት በደንብ ያጤኗቸዋል።

በምድር ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አዲሱን የመዝሙር መጽሐፍ በማግኘታቸው እጅግ ተደስተዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ መዝሙሩ በቋንቋቸው ተዘጋጅቶ የሚወጣበትን ቀን በጉጉት እየተጠባበቁ ነው።