በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በሥዕል የሚያስተምር ዓለም አቀፋዊ ብሮሹር

በሥዕል የሚያስተምር ዓለም አቀፋዊ ብሮሹር

ኦድቫል የምትኖረው በሞንጎሊያ ነው። ዕድሜዋን በእርግጠኝነት ባታውቀውም በ1921 አንደተወለደች ታስባለች። ልጅ ሳለች የወላጆቿን ከብቶች ታግድ የነበረ ሲሆን ትምህርት ቤት የመግባት ዕድል ያገኘችው ለአንድ ዓመት ብቻ ነበር። ማንበብ አትችልም። ይሁንና በቅርቡ የደረሳት ማራኪ ሥዕሎች ያሉት አንድ ብሮሹር አምላክን እንድታውቅና እሱን የሚታዘዙ ሰዎች ስላላቸው ብሩህ የሆነ የወደፊት ተስፋ እንድትገነዘብ ረድቷታል። ይህን በማወቋም ልቧ በጥልቅ ተነክቷል።

በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው ይህ ብሮሹር የታተመው በ2011 ሲሆን በሁለት ዓይነት መንገድ የቀረበ ነው። ሁለቱም ብሮሹሮች ማራኪ ሥዕሎችን ይዘዋል፤ ይሁን እንጂ አንደኛው ብሮሹር የያዘው ጽሑፍ ከሌላኛው ትንሽ በዛ የሚል በመሆኑ መጠነኛ ልዩነት አላቸው።

አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ የተባለው ትንሽ በዛ ያለ ጽሑፍ የያዘው ብሮሹር በቅርቡ በ583 ቋንቋዎች እንደሚዘጋጅ ይጠበቃል፤ አምላክን ስማ የሚል ርዕስ ያለው ሌላኛው ብሮሹር ደግሞ በ483 ቋንቋዎች ይዘጋጃል። ለማነጻጸር ያህል፣ የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ እስከ ጥቅምት 2013 ድረስ የተተረጎመው በ413 ቋንቋዎች ነው። በተጨማሪም የእነዚህ ሁለት ብሮሹሮች ስርጭት ወደ 80 ሚሊዮን ቅጂዎች ይጠጋል።

በብራዚል የሚኖሩ አንዲት አረጋዊት አምላክን ስማ የተባለውን ብሮሹር በደስታ ከተቀበሉ በኋላ እንዲህ ብለዋል፦ “እንደ እኔ ላሉ ሰዎች የሚያስቡ ሰዎች መኖራቸውን ማወቅ በጣም ያጽናናል። ማንበብ ስለማልችል ከዚህ ቀደም መጽሔቶቻችሁን ተቀብዬ አላውቅም ነበር። ይህን ብሮሹር ግን የራሴ ማድረግ እፈልጋለሁ።”

በፈረንሳይ የምትኖረውና ማንበብም ሆነ መጻፍ የማትችለው ብሪዢት “በብሮሹሩ ላይ ያሉትን ሥዕሎች በየዕለቱ አያቸዋለሁ” ብላለች።

በደቡብ አፍሪካ የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የቻይንኛ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በቀላሉ ለማስተማር የሚረዳ ከዚህ የተሻለ ብሮሹር አላገኘሁም። የተለያየ የትምህርት ደረጃ ካላቸው ሰዎች ጋር ይኸውም በጣም ጎበዝ ከሆኑ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንም ሆነ ማንበብ ከሚቸግራቸው ሰዎች ጋር የተጨዋወትኩባቸው ጊዜያት አሉ። ያም ሆኖ አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ የተባለው ብሮሹር፣ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማስተማር አስችሎኛል። ግማሽ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጥሩ መሠረት መጣል ችያለሁ።”

በጀርመን የሚኖሩ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች የተማሩ ከሆኑ አንድ ባልና ሚስት ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ ነበር። ባልየው ብሮሹሩን ሲያይ በጣም በመደነቅ “ይህን ብሮሹር ቀደም ብላችሁ ያልሰጣችሁኝ ለምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ ክንውኖችንና አገላለጾችን በቀላሉ እንድረዳ ያስችለኛል” ብሏል።

በአውስትራሊያ የምትኖር መስማት የተሳናት አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ለብዙ ዓመታት የኖርኩት በሴቶች ገዳም ውስጥ ካሉ መነኮሳት ጋር ነው። ከቤተ ክርስቲያኗ መሪዎች ጋር ከማንኛውም ሰው የተሻለ ቅርበት ነበረኝ። ይሁን እንጂ አንዳቸውም የአምላክ መንግሥት ምን እንደሆነ ነግረውኝ አያውቁም። በብሮሹሩ ላይ ያሉት ሥዕሎች የማቴዎስ 6:10ን ትርጉም ለመረዳት አስችለውኛል።”

በካናዳ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “በዚህ የሚኖሩ በርካታ የሴራሊዮን ተወላጆች በክሪዮ ቋንቋ የተተረጎመውን አምላክን ስማ የተባለውን ብሮሹር ሲመለከቱ የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሰዎች ለማድረስ ምን ያህል ጠንክረው እየሠሩ እንዳሉ ለመናገር ተገፋፍተዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ‘ብዙዎች የእኛ ጉዳይ ግድ ባይሰጣቸውም እናንተ ግን ታስቡልናላችሁ’ ብለዋል።”