በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በሜክሲኮና በመካከለኛው አሜሪካ እየተካሄደ ያለው የትርጉም ሥራ

በሜክሲኮና በመካከለኛው አሜሪካ እየተካሄደ ያለው የትርጉም ሥራ

በሜክሲኮና በመካከለኛው አሜሪካ በሚገኙ ስድስት አገሮች ውስጥ የሚኖሩ 290 ገደማ የሚሆኑ ተርጓሚዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ከ60 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይተረጉማሉ። እንዲህ ያለ ጥረት የሚደረገው ለምንድን ነው? ሰዎች በቀላሉ ሊረዱት በሚችሉት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ሲያነብቡ ልባቸው ይበልጥ ስለሚነካ ነው።​—1 ቆሮንቶስ 14:9

የትርጉም ሥራው ይበልጥ ጥራት ያለው እንዲሆን ለማድረግ ሲባል በሜክሲኮ ሲቲ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ አንዳንድ ተርጓሚዎች የሚተረጉሙበት ቋንቋ በሚነገርበት አካባቢ ወዳለ የትርጉም ቢሮ እንዲዛወሩ ተደርጓል። ይህ መደረጉ ምን ጥቅም አስገኝቷል? ተርጓሚዎቹ፣ ጽሑፎቹን በሚተረጉሙበት ቋንቋ አፋቸውን ከፈቱ የአገሬው ተወላጆች ጋር ይበልጥ የመገናኘት አጋጣሚ የተከፈተላቸው ሲሆን ይህም ለመረዳት ቀላል በሆነ መንገድ እንዲተረጉሙ አስችሏቸዋል።

ተርጓሚዎቹ ስለተደረገው ለውጥ ምን ይሰማቸዋል? የጉዌሬሮ ናዋትል ቋንቋ ተርጓሚ የሆነው ፌዴሪኮ እንዲህ ብሏል፦ “በሜክሲኮ ሲቲ በቆየሁባቸው ወደ አሥር የሚጠጉ ዓመታት ውስጥ ያገኘሁት የእኔን ቋንቋ የሚናገር ቤተሰብ አንድ ብቻ ነበር። አሁን የትርጉም ቢሮው ባለበት አካባቢ ያሉ መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ግን ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል የዚህ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው!”

የሜክሲኮ ግዛት በሆነችው በቺዋዋ በሚገኘው የትርጉም ቢሮ ውስጥ ሎ ጀርመን የተባለው ቋንቋ ተርጓሚ የሆነችው ካረን እንዲህ ብላለች፦ “በአካባቢው ካሉት ሜኖናውያን ጋር አብሬ መኖሬ የሚናገሩትን ቋንቋ ጠንቅቄ እንዳውቅ አስችሎኛል። የምንኖረውም ሆነ የምንሠራው በትንሽ ከተማ ውስጥ ነው፤ መስኮቴን ከፍቼ ስመለከት እዚህ በምናከናውነው የትርጉም ሥራ ሊጠቀሙ የሚችሉ ብዙ ሰዎችን አያለሁ።”

ሜክሲኮ ውስጥ በሜረዳ ከተማ በሚገኘው የትርጉም ቢሮ የምትኖረው ኒፊ እንዲህ ብላለች፦ “በማያ ቋንቋ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠና ለመረዳት አስቸጋሪ የሚሆኑባቸውን አንዳንድ አገላለጾች ማስተዋል እንችላለን። በመሆኑም እነዚህን አገላለጾች የአካባቢውን ሰዎች ግራ በማያጋባ መንገድ ለመተርጎም ጥረት እናደርጋለን።”

በዚህ መንገድ የተተረጎሙት ጽሑፎች የሚደርሷቸው ሰዎችስ ምን ጥቅም አግኝተዋል? እስቲ አንድ ምሳሌ ብቻ እንመልከት፦ በታልፓኔክ ቋንቋ አፏን የፈታችው ኤለና ለ40 ዓመታት ያህል በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ አዘውትራ ትገኝ ነበር። ይሁንና ስብሰባው የሚካሄደው በስፓንኛ ስለነበር የሚነገረውን ነገር መረዳት አትችልም ነበር። ኤለና “ስብሰባዎች ላይ የምገኘው እንዲሁ በዚያ መገኘት እፈልግ ስለነበር ነው” ብላለች። ኤለና፣ በታልፓኔክ ቋንቋ በተዘጋጁ ብሮሹሮች አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ካጠናች በኋላ ግን ለአምላክ ያላት ፍቅር ያደገ ሲሆን በ2013 ራሷን ለአምላክ ወስና ለመጠመቅ በቃች። ኤለና “መጽሐፍ ቅዱስን እንድረዳ ስላስቻለኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ” ብላለች።